1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 14 2002

በአውሮፓ እስካሁን አቻ ባልታየለት ሁኔታ የውርርድ ማፊያ ቡድኖች በጨዋታ ውጤቶች ላይ ተጽዕኖ በማድረግ የሚፈጽሙት ወንጀል መጋለጥ የሣምንቱ ዓበይት ዜና ሲሆን የተወዳጁን ስፖርት ገጽታ ጥላሸት መቀባቱ በጣሙን አሳዝኗል።

https://p.dw.com/p/Kde5
ምስል picture-alliance / Sven Simon

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ መጠናቀቅ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከመንፈቅ በኋላ ለሚከፈተው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሲካሄድ የቆየው ማጣሪያና የማጣሪያ-ማጣሪያ ጉዞ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ማብቃቱ ይታወቃል። ታዲያ ሁሌም እንደተለመደው ዳዊት ጎልያድን ያንበረከከበት ሁኔታ ዘንድሮም ባይታጣም ከሁሉም በላይ ግን በማግሥቱ መነጋገሪያ የሆነው አየርላንድ በዳኛ ስህተት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ዕድሏን ማጣቷ፤ እንዲሁም አልጄሪያ ግብጽን ማስቀረቷ ያስከተለው የፖለቲካ ውዝግብ ነው። በመደበኛው ማጣሪያ ውድድር ማለፍ ተስኗት ከውርደት አፋፍ ላይ ደርሳ የነበረችው ፈረንሣይ አጥቂዋ ቲየሪ ኦንሪ በዕጁ ባስቆጠራት ጎል የደቡብ አፍሪቃ ቲኬቷን ስትቆርጥ ለአየርላንድ የተረፈው ግን ምናልባትም ለረጅም ጊዜ የማይረሣ መጥፎ ትውስትና ቁጭት ነው። የዳናው ውሣኔ ስህተት ቢሆንም በወቅቱ ባለው የአሠራር ዘይቤ የማይሻር በመሆኑ የአየርላንድ ፌደሬሺን እንኳ አቤቱታውን መልሶ ከመሳብ ሌላ ምርጫ አልታየውም።
ይህን መሰሉ ስህተት እርግጥ ያልተለመደ ነገር ባይሆንም የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ወደፊት ቢቀር እንዲህ ወሣኝ ለሆኑ ጨዋታዎች ወዲያው ጣልቃ የሚገባ ተጨማሪ ዳኛ ቢያስቀምጥ ተገቢ የሚሆን ነው። ሃሣቡ ቀደም ሲል በያጋጣሚው የተነሣ ቢሆንም የጨዋታን ሂደት በየጊዜው በማሰናከል የስፖርቱን ውበት ያበላሻል ወይም የዳኞችን ሥልጣን ሊቀንስ ይችላል በሚሉ ምክንያቶች ሲታለፍ ነው የቆየው። ሆኖም ግን ከፈረንሣይና ከአየርላንድ ግጥሚያ ሂደት በኋላ እንደገና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በውድድሩ ጠንካራ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ፖርቱጋልም ቦስናን አልፋ የማታ ማታ ለፍጻሜው ስትበቃ ግሪክም በገዛ ሜዳዋ በአቴን ኦሎምፒክ ስታዲዮም ከኡክራኒያ ጋር ብርክ ይዟት ባዶ-ለባዶ ከተለያየች በኋላ በመልሱ ጨዋታ 1-0 በማሸነፍ እንደገና ለዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በቅታለች። በዚህ በአውሮፓ ከሁሉም በላይ ያልተጠበቀው ሩሢያ በስሎቬኒያ በተመሳሳይ ውጤት ተሸንፋ መቅረቷ ነው። ለሩሢያ ክስረት በተለይም በሜዳዋ 2-0 ስትመራ ከቆየች በኋላ በመጨረሻ አንድ ጎል መልቀቋ ወሣኝነት ነበረው። ስሎቬኒያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ያበቃችውም ይህችው በውጭ የተቆጠረች ግብ ነበረች።

በተቀረ ኡሩጉዋይ ኮስታ ሪካን በመልሱም ግጥሚያ በመርታት ስታልፍ ኒውዚላንድም እንዲሁ ባህሬይንን በማሸነፍ ከአውስትራሊያ ጎን ሁለተኛዋ የኦሺኒያ ክፍለ-ዓለም ወኪል ሆናለች። እርግጥ በሣምንቱ አጋማሽ የማጣሪያ ሂደት ይበልጥ ትኩረት የሳበው ከስፖርት አልፎ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ሽኩቻን ያስከተለው የግብጽና የአልጄሪያ ግጥሚያ ውጤት ነው። ማጣሪያው ውድድር እጅግ ከባድ በነበረባት በአፍሪቃ ሁለቱ አገሮች ምድባቸው ውስጥ በነጥብም በጎልም እኩል ሆነው በመገኘታቸው ካርቱም ላይ መለያ ግጥሚያ ማድረግ ነበረባቸው። በዚሁ ግጥሚያ የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን 1-0 ሲረታ ለነገሩ ከስፖርት አንጻር የሚያጠያይቅ ነገር አልታየም። ይሁንና በሁለቱ አገሮች በየኤምባሲው አጠገብና በአደባባይ የታየው ቁጣ የመንግሥታቱ መጠቀሚያ እስከመሆን ነው የደረሰው። ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ እንዲያውም ቁጣውን ጨቋኝ የሚላቸውን ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሊጠቀሙበት ሳይከጅሉ አልቀረም። እርግጥ የስድሥት ጊዜዋ የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት ግብጽ ተሰናክላ መቅረቷ ተመልካቿን ማስከፋቱ አያሰደንቅም። ሊዚያውም በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ አለመድረስ በተለይ ከሁለት ተከታታይ የአፍሪቃ ሻምፒዮንነት በኋላ ብዙ የሚቆረቁር ነው። ሆኖም ግን ስፖርት ጦርነት አይደለም። ግብጽም ሽንፈትን በክብር መቀበል መቻል ይኖርባታል።

የውርርድ ማፊያ ተጽዕኖና የአውሮፓ እግር ኳስ ዝና

ግን የሣምንቱ ጉድ ይህ ብቻ አልነበረም። በዚህ በአውሮፓ የውርርድ ማፊያ ቡድኖች ከሶሥተኛ ዲቪዚዮን አንስቶ እስከ ቀደምት ክለቦችና እስከ ሻምፒዮና ሊጋው ውድድር ጭምር ከሁለት መቶ በሚበልጡ ግጥሚያዎች ውጤት ላይ ተጽዕኖ ማድረጋቸው መታወቁም በሣምንቱ አሳዛኙ ብቻ ሣይሆን አስደንጋጩ ዜና ሆኖ ነው የሰነበተው። እርግጥ ይህን መሰሉ ድርጊት ሲፈጸም ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። የወቅቱን አስደንጋጭ የሚያደርገው ጥልቀትና መጠኑ በአውሮፓ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እስካሁን አቻ ያልታየለት ሊሆን መቻሉ ነው። በዚሁ ቢቀር ዘጠኝ አገሮችን ባዳረሰው የማፊያ ወንጀል በጀርመን እንኳ ቢያንስ 32 ጨዋታዎች ተጭበርብረዋል። እስካሁን መርማሪዎች በደረሱበት መረጃ በስድሥት የአውሮፓ አገሮች በአንደኛ ዲቪዚዮን ግጥሚያዎች ላይ ተጽዕኖ ሲደረግ ሶሥት የክለቦች ሻምፒዮናና የአውሮፓ ሊጋ ጨዋታዎችም በማፊያው የውርርድ ቢሮዎች ወንጀል ሳይበረዙ አልቀሩም። ድርጊቱ አውሮፓን እስከ ቁንጮው ድረስ የበከለ ነጉዳይ ነው። ተጫዋቾችና ዳኞች ሳይቀር በግጥሚያ ውጤቶች ላይ ተጽዕኖ በማድረግ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስገቡት ወንጀለኛ የውርርድ ቢሮ አራማጆች መሣሪያ ሆነዋል። እጅግ የሚያሳዝነው በተለይ በዛሬው የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ወደየስታዲዮሙ እየጎረፈ መዓት ገንዘብ የሚያፈሰው ኳስ አፍቃሪ የውሸት ጨዋታ ተመልካች እንዲሆን መደርግ ነው። የአውሮፓ እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው ስፖርቱ ዝና እንዳይጎድፍ ቁርጠኛ ውሣኔ ማድረግ ይኖርበታል። አለበለዚያ በተለይ በያመቱ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቀው የሻምፒዮና ሊጋ ውድድሩ ግርማ-ሞገሱን ማጣቱ ነው።

ታላቁ ሩጫ በአትዮጵያ/የዓመቱ አትሌቶች ምርጫ በሞንቴ ካርሎ

በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደው የዓመቱ ታላቅ ሩጫ አሸናፊ ማንም ያልጠበቀው ወጣት አትሌት ጥላሁን ረጋሣ ሆኗል። የ 19 ዓመቱ ወጣት የአሥር ኪሎሜትሩን የመንገድ ሩጫ ያሸነፈው ለዚያውም የቀድሞውን ሬኮርድ በማሻሻል ነው። በሌላ የአትሌቲክስ ዜና ደግሞ የጃማይካው የአጭር ርቀት መንኮራኩር ዩሤይን ቦልትና የዚያው የጃማይካ ተወላጅ የሆነችው የአሜሪካ የአራት መቶ ሜትር ሯጭ ሣኒያ ሪቻርድስ ትናንት በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የዓመቱ ድንቅ አትሌቶች በመባል ሞንቴ ካርሎ ላይ ተመርጠዋል። ቦልት የመቶ፣ ሁለት መቶ ሜትርና የአራት ጊዜ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል ሩጫ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

MM/RTR/AFP

Negash Mohammed