1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 14 2001

ሣምንቱ በዓለም ዙሪያ ከእግር ኳስ እስከ ቡጢ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር።

https://p.dw.com/p/HHvi
ሣሚ ከዲራ ለሽቱትጋርት ጎል ሲያገባ
ሣሚ ከዲራ ለሽቱትጋርት ጎል ሲያገባምስል picture-alliance/ dpa

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ዲቪዚዮኖች የእግር ኳስ ውድድር ሰንበቱ በተለይም በእንግሊዝና በጀርመን የሻምፒዮናው ፉክክር ይበልጥ የጠበበት ነበር። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምቱ ማንቼስተር ዩናይትድ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በመሽነፉ አመራሩ በአንዲት ነጥብ ብቻ ሊወሰን በቅቷል። ቡድኑ በፉልሃም 2-0 ሲረታ ሰንበቱ በአጠቃላይ ለማኒዩ የቀና እልነበረም። ዳኛው ከአንድም ሁለት ዋና ዋና ተጫዋቾቹን ፓውል ስኮልስንና ዌይን ሩኒይን ቀድሞ ከሜዳ በማሰናበቱ ጨዋታውን በጎዶሎ መፈጸሙ ግድ ነው የሆነበት። በነገራችን ላይ ፉልሃም በሜዳው ማንቼስተር ዩናይትድን ሲያሸንፍ ከ 45 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ይህም ራሱን የቻለ ታሪክ ይሆናል።

በሌላ በኩል የሣምንቱ ተጠቃሚ ትናንት ኤስተን ቪላን 5-0 የሸኘው ሊቨርፑል ነበር። ስቲቭን ዤራርድ ሶሥቱን ጎሎች በጨዋታ ሲያስቆጥር የተቀሩት ሁለት ግቦች የተገኙት ደግሞ በፍጹም ቅጣት ምት ነው። በፕሬሚየር ሊጉ ውስጥ ሰንበቱን ከተካሄዱት 30ኛ ግጥሚያዎች በኋላ ማንቼስተር ዩናይትድ አንድ ጨዋታ ጎሎት በ 65 ነጥቦች ይመራል። ሊቨርፑል አንዲት ነጥብ ብቻ ወረድ ብሎ በ 64 ሁለተኛ ነው። እንደ ማኒዩ ሁሉ ሣምንቱ ያልቀናው ሌላው ቀደምት ቡድን ቼልሢይ ነበር። ቼልሢይ በቶተንሃም ሆትስፐር 1-0 ሲረታ በ 61 ነጥቦች መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። አርሰናል ኒውካስል ዩናይትድን 3-1 ሲያሸንፍ በ 55 ነጥቦች አራተኛ ነው። የፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ ስምንት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ የቀደምቱ ክለቦች ፉክክር የጦፈ ሆኖ የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

በጀርመን ቡንደስሊጋም ሁኔታው ብዙም የተለየ አይደለም። አራቱ የሊጋው ቀደምት ቡድኖች ከሰንበቱ ግጥሚያዎች ወዲህ ይበልጡን ነው የተቀራረቡት። እርግጥ ሄርታ በርሊን በሽቱትጋርት 2-0 ተሸንፎ ምንም እንኳ የአራት ነጥብ ቅድሚያውን ቢያጣም በ 49 ነጥቦች በሻምፒዮንነት ሕልሙ እንደቀጠለ ነው። ሆኖም አሁን የሚመራው በአንዲት ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው። የሽቱትጋርት ድል ደግሞ በጥሩ ጨዋታ እንጂ በዕድል የተገኘ አልነበረም። ይህም አሠልጣኙን ማርኩስ ባልልን በጣሙን ነው ያስደሰተው።

“ዛሬ የቡድናችንን ግሩም፤ እጅግ ግሩም ጨዋታ ነው ያየነው። ቡድኑ ባለፈው ሣምንት በብሬመን 4-0 ከተሸነፈ በኋላ ብርቱ ንቃት አሣይቷል። በኔ የአመራር ወቅት ድንቅ ጨዋታው ሲሆን እኔም በዚሁ በጣም ነው የረካሁት”

ባየርን ሙንሺን፣ ቮልፍስቡርግና ሃምቡርግ ሶሥቱም እኩል ነጥብ ይዘው በርሊንን በቅርብ ይከተላሉ። በሌላ በኩል እንደ ብሬመን ሁሉ ማቆልቆል የያዘው የአንዴ ጠንካራ ቡድን ሻልከ በገዛ ሜዳው በሃምቡርግ 2-1 ሲሸነፍ አሠልጣኙ ፍሬድ ሩተን ብዙም የሚያማርርበት ምክንያት አላገኘም ነበር።

“ቡድኑ በከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ እንዳልተጫወተ የተሰወረ ነገር አይደለም። ዛሬ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ሁኔታው ይህ ነበር”
በተረፈ ከቀደምቱ ቡድኖች መካከል ባየርን ሙንሺን ካርልስሩኸን በመከራም ቢሆን 1-0 ሲረታ በሌላ በኩል ቮልፍስቡርግ ቢለፌልድን 3-0 በማሸነፍ ፍጹም ልዕልና ነበር ያሳየው። ይሄው የወቅቱ ጠንካራ ቡድን በውድድሩ መጀመሪያ ወቅት በዚህ መጠን ቀደምት ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም። ቮልፍስቡርግ ሣምንት የባየርን ሙንሺን ተጋጣሚ ሲሆን የዚሁ ጨዋታ ውጤት ምናልባትም ለአንዱ ወይም ለሌላው ቡድን የወደፊት ዕርምጃ ወሣኝ ሊሆን የሚችል ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በአንጻሩ በሣምንቱ ብዙም የተለወጠ ነገር የለም። ባርሤሎና ማላጋን 6-0 አከናንቦ በመሸኘት በስድሥት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል ተከታዩ ሬያል ማድሪድም አልሜይራን 3-0 አሸንፏል። ከቀደምቱ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ አራት ክለቦች የተቀሩት ሁለቱም ሤቪያ ቫላዶሊድን 4-1፤ ቪላርሬያልም አትሌቲክ ቢልባኦን 2-0 በመርታት በስኬት ነው ሰንበቱን ያሳለፉት። ከ 28 ግጥሚያዎች በኋላ ባርሤሎና በ 69 ነጥቦች አንደኛ ነው፤ ሬያል በ 63 ነጥቦች ይከተላል። ሶሥተኛ ሤቪያ፣ አራተኛ ቪላርሬያል፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ አምሥተኛ ነው።

በኢጣሊያ ሊጋም እንዲሁ ቀደምቱ ኢንተር ሚላን ሬጂናን 3-0 በመርታት የሰባት ነጥብ ልዩነቱን እንደጠበቀ ለመቀጠል ችሏል። ጁቬንቱስም ሮማን 4-1 በማሸነፍ ሁለተኝነቱን እንደያዘ ሲሆን የሰንበቱ ግጥሚያ ያልተዋጣለት ከናፖሊ ጋር ባዶ-ለባዶ የተለያየው ኤ.ሢ.ሚላን ነበር። ከዚህ ውጤት በኋላ ኤ.ሢ.ሚላንን ከኢንተር የሚለየው ነጥብ ወደ 14 ከፍ ሲል ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉ ሳያከትምለት የቀረ አይመስልም።

ሌላው የተቀራረበ ፍክክር የሚታይበት የአውሮፓ ሊጋ የፈረንሣዩ አንደኛ ዲቪዚዮን ነው። የሰባት ጊዜው ሻምፖዮን ኦላምፒክ ሊዮን ሶሾን 2-0 በማሸነፍ አመራሩን እንደያዘ ቢቀጥልም ናንትን በተመሳሳይ ውጤት የረታው ኦላምፒክ ማርሤይ የሚከተለው በአንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ነው። ሊዮን 56 ነጥቦች ሲኖሩት ቦርዶ፣ ቱሉዝ፣ ሊልና ፓሪስ-ሣንት-ዣርማንም በአራት ነጥቦች ርቀት ሻምፒዮን የመሆን ዕድላቸውን እንደጠበቁ ይቀጥላሉ። የሊጋው ውድድር ሊያበቃ የቀሩት ዘጠኝ ግጥሚያዎች ናቸው።

በተቀረ የአውሮፓ እግር ኳስ በመጪው ወር በክለቦች ሻምፒዮና ሊጋው ውድድር ደምቆ ይቀጥላል። በሣምንቱ መጨረሻ በወጣው ዕጣ መሠረት በሻምፒዮናው ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ቪላርሬያል ከአርሰናል፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ከፖርቶ፤ ሊቨርፑል ከቼልሢይ፤ እንዲሁም ባርሤሎና ከባየርን ሙንሺን ይገናኛሉ። ግጥሚያዎቹ የሚካሄዱት በፊታችን መጋቢት 29 እና 30 ነው። ዕጣዎቹ በሙሉ እጅግ የጠነከሩ ሲሆኑ የሁለቱ ቀደምት የእንግሊዝ ክለቦች የሊቨርፑልና የቼልሢይ ከወዲሁ መገናኘት ያሳዝናል ለአንዱ መሰናበቻው መሆኑ ላይቀር ነው። ቢሆንም ከተቀሩት ሶሥት ክለቦች ሁለቱ በድል በመቀጠል እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ሻምፒዮናውን በራሳቸው መካከል ለመወሰን ይችላሉ።

በዩኤፋ ዋንጫ ውድድር የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ደግሞ ሁለቱ የጀርመን ቡድኖች ብሬመን ከኢጣሊያው ኡዲኔዘ ካልቾ፤ ሃምቡርግ ከአንግሊዙ ማንቼስተር ሢቲይ የሚገናኙ ሲሆን የተቀሩት ተጋጣሚዎች ፓሪስ-ሣንት-ዣርማን ከዲናሞ ኪየቭና ዶኔትስክ ከኦላምፒክ ማርሤይ ናቸው። ግጥሚያዎቹ የሚካሄዱት በሚያዚያ አምሥትና ስድሥት ምሽቶች ነው።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ኢጣሊያ ውስጥ በተካሄደው በ 15ኛው የሮማ ማራቶን ሩጫ ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪፕቶ አሸናፊ ሆኗል። ኪፕቶ ወደ ሰላሣ ኪሎሜትር ገደማ እንደተቃረበ ተፎካካሪዎቹን ጥሎ በማምለጥ ከግቡ ሲደርስ የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ 7 ከ 17 ሤኮንድ ነው። ሁለተኛ ፓውል ኪሩዊ፤ ሶሥተኛ ፌስቱስ ኪፕሮቲች ሁሉም ከኬንያ። በሴቶች ኢትዮጵያዊቱ ፍሬሕይወት ዳዶ አሸናፊ ሆናለች። በሌላ በኩል በግሩም የጸደይ አየር የታጀበው የሮማው ማራቶን ሃዘን የጋረደውም ነበር። ለዚህም ምክንያት የሆነው በውድድሩ የተሳተፈው የ 46 ዓመት የኢጣሊያ ዜጋ ማርኮ ፍራንሶሲ በልብ ድካም መሞቱ ነው።
በማራቶን ሩጫ ጥሩ ልምድ እንደነበረው የተነገረለት የፓርማ ነዋሪ ሩጫውን ከፈጸመ ከአንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ በኋላ ከሆቴሉ አጠገብ መንገድ ላይ ወድቆ መገኘቱ ነው የተነገረው። በተረፈ ኬንያ በትናንቱ የቶኪዮ ማራቶንም ቢቀር በወንዶች ቀደምቷ ነበረች። ሣሊም ኪፕሣንግ ሁለት የጃፓን ተፎካካሪዎቹን አስከትሎ በመግባት ሲያሸንፍ እርግጥ ከሁለት ሰዓት ከአሥር ደቂቃ በላይ የሆነ ጊዜው ሃያል የሚያሰኝ አልነበረም። የሆነው ሆኖ በሴቶች ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትሎ በመግባት ያሸነፉት ጃፓናውያን ናቸው።

በተቀረ የአትሌቲክስ ደምቦችን በተመለከተ ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የተሳሰተ የሩጫ ጅማሮን ያለፈ ታሪክ ለማድረግ ትናንት ድምጽ ሰጥቷል። በርሊን ላይ የተሰበሰበው ሸንጎ ያስተላለፈው ውሣኔ የሚጸናው እርግጥ በፊታችን ነሐሴ ወር በበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኳያ በሚያካሂደው ጉባዔ ነው። ውሣኔው ከጸና ከመጪው 2010 ዓ.ም. መጀመሪያ አንስቶ ጥይት ከመተኮሱ በፊት የሮጠ ማንኛውም አትሌት ያላንዳች ማስጠንቀቂያ ወዲያው በቀጥታ ይታገዳል። ከ 2003 ዓ.ም. ወዲህ አትሌቶች የሚታገዱት በመጀመሪያው ጥፋተኛ ሆኑ አልሆኑ ሁለት የአጀማመር ስህተት ከተሰራ በኋላ ነበር። የደምቡ መለወጥ ጥሩ ይሁን መጥፎ ጠብቆ መታዘቡ ነው ለጊዜው የሚመረጠው።

ቴኒስ

በካሊፎርኒያ የኢንዲያን ዌልስ የቴኒስ ዓለምአቀፍ ውድድር ፍጻሜ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ 1ኛውን ቦታ የያዘው የስፓኙ ራፋኤል ናዳል የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪይን በተለየ ልዕልና 6-1, 6-2 በሆነ ውጤት አሸንፏል። 80 ደቂቃዎች በፈጀው ግጥሚያ ኤንዲይ መሪይ የናዳልን ድል አደጋ ላይ የጣለበት አንድም ጊዜ አልነበረም። የሴቶቹም ፍጻሜ ግጥሚያ ተመልካችን ከመጠን በላይ ያስደሰተ ነበር። ሩሢያዊቱ ቬራ ዝቮናሬቫ የሰርቢያ ተጋጣሚዋን አና ኢቫኖቪችን እንዲሁ በሁለት ምድብ ጨዋታ ለማሸነፍ በቅታለች።አና ኢቫኖቫ ያለፈው ዓመት አሸናፊ ነበረች። ለዝቮናሬቫ የሰንበቱ ድል እስካሁን ታላቁ መሆኑ ነው። ደስታዋም በዚያኑ መጠን ከፍ ያለ ነበር።

ዘገባችንን በቡጢ ለማጠቃለል የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ቪታሊ ክሊችኮ በዚህ በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ በተካሄደ ግጥሚያ የኩባውን ተወላጅ ሁዋን-ካርሎስ-ጎሜስን በማሸነፍ ክብሩን ለማስጠበቅ በቅቷል። የኡክራኒያው ተወላጅ ክሊችኮ ያሽነፈው ተጋጣሚውን በዘጠነኛው ዙር በመዘረር ነው። ለክሊችኮ ያለፈው ቅዳሜ ድል 37ኛው ሲሆን በመዘረር ሲያሸንፍም ለ 36ኛ ጊዜ ነበር። ታናሽ ወንድሙ ቭላዲሚር ክሊችኮም የሶሥት የቦክስ ማሐበራት ሻምፖዮን መሆኑ ይታወቃል።

መሥፍን መኮንን