1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2005

በሳምንቱ ማብቂያ ላይ የተከናወኑ ዓበይት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች በተለይም የእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ዋነኛ ትኩረታችን ይሆናል። እሁድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስላደረገው የወዳጅነት ጨዋታ፣ እንዲሁም ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ለመጀመሪያ ግዜ ብቅ ስላለችው ኬፕ ቬርዴ አጠር ያለ ዘገባ ይኖረናል።

https://p.dw.com/p/17BjF
ምስል picture-alliance/dpa

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ዜናዎችንም አካተናል። ቆይታችሁ ከኛ ጋር ይሁን። በሳምንቱ ማብቂያ ላይ በእንግሊዝ በተከናወኑ የፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ዋነኞቹ ተፎካካሪ ቡድኖች በአጠቃላይ ድል ተቀዳጅተዋል። በዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑልም የጎርጎሮሳውያኑን አዲስ ዓመት ለመቀበል ሁለት ቀን ሲቀረው ደጋፊዎቹ አዲሱን ዓመት በተስፋ እንዲቀበሉ በሚያደርግ ሁናቴ ነጥብ ይዞ ወጥቷል። ኢትዮጵያ ለወዳጅነት እሁድከኒጀር ጋር ተጋጥማ አሸንፋለች። የሰባት ጊዜያት የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ባለድሉ ላንስ አርምስትሮንግ ለዓመታት እስከዛሬ ያሰባሰባቸው ውጤቶቹ በአጠቃላይ ተሰርዘውበታል። ሌሎች ስፖርት ነክ አጫጭር ዘገባዎችንም አካተናል፤ ዝርዝሩን እንደየቅደም ተከተሉ ከቀጣዩ የእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ትንታኔ በኋላ ይዘንላችሁ እንቀርባለን።

በእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ በደረጃ ሠንጠረዡ ሶስተኛ ሆኖ ላይ የሚገኘው ቸልሲ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው ኤቨርተንን እሁድ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፏል። ሆኖም ኤቨርተኖች ትናንት ዕድል ጠማባቸው ነበር ማለትም ይቻላል። ድንቅ በሆነ አጀማመር ኳሷን ወደፊት የገፉት ኤቨርተኖች በ62ኛው ሰከንድ ገደማ ነበር በስቲቨን ፒናር በመጀመሪያ ግብ ያስቆጠሩት። በ8ኛው ደቂቃ ገደማ ኒኪቺ የሌቪች አክርሮ የመታት ኳስ እንዲሁም፣ በ68ኛው ደቂቃ ይኸው ኒኪቺ በጭንቅላት ገጭቶ ማዕዘን የመለሰበት ሙከራ ኤቨርተንን የሶስት ግቦች ባለቤት ባደረጉት ነበር። ይሁንና ቸልሲዎች በ41ኛው ደቂቃ ላይ ራሚሬዝ የላካትን ኳስ ፍራንክ ላምፓርድ በጭንቅላቱ ገጭቶ ከመረብ በማሳረፉ ከገቡበት ውጥረት ተንፈስ ሊሉ ችለዋል። በ71ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ላምፓርድ ኳሷን ከመረብ በመቀላቀል ቸልሲዎችን ከጭንቀት አውጥቶ እንዲፈነጩ አድርጓል።

የቸልሲው ፍራንክ ላምፓርድ
የቸልሲው ፍራንክ ላምፓርድምስል Reuters

በነገራችን ላይ ላምፓርድ በ11 ዓመታት የቸልሲ ቆይታው ከ500 ጊዜያት በላይ የተሰለፈ ቢሆንም ከቸልሲ ጋር ያለው ቁርኝት ግን ሊበጠስ የቀረው ጥቂት ይመስላል። ለቸልሲ የገባው ውል በዚህ የውድድር ወቅት የሚጠናቀቅ ሲሆን እድሳት አልተደረገለትም። ይህንኑ አስመልክቶ የቸልሲው ባለውለታ አንጋፋው ተጫዋች ላምፓርድ «ባለፉት ሳምንታት ስለ አዲስ ውል ምንም የተነጋገርነው ነገር የለም። እናም ዋነኛው ትኩረቴ ጨዋታው ላይ ነው። መጫወቴ በቂ ርካታ ይሰጠኛል፤ የሚሆነው በራሱ ጊዜ ይሆናል» ሲል ተደምጧል።

የቸልሲው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ በበኩላቸው «የእኔ ተግባር ላምፓርድ ብቁ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው።» ሲሉ አጠር አድርገው ገልፀዋል። አያይዘውም ቡድናቸው ለዋንጫ የሚያደርገው ግስጋሴ ላይ እንጂ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ማን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው እንደማያሳስባቸው ጠቅሰዋል። ቤኒቴዝ «የእኛ ሀሳብ እያንዳንዱን ጨዋታ በነጠላ እያተኮርንበት ውድድሩን መቅረብ ነው። የደረጃ ሠንጠረዡ ላይ ዝም ብለን አናፈጥም» ብለዋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረውና በሊቨርፑል የቀድሞው አሰልጣኝ የሚመራው ቸልሲ ከማንቸስተር ዩናይትድ በ11 ነጥብ ርቀት ይገኛል።

በሌላኛው የእሁድ ግጥሚያ ሊቨርፑል በዓመቱ መገባደጃ የማታ ማታ ቀንቶት በደረጃው ሠንጠረዥ ወለል ላይ ተጋድሞ እንቅልፉን የሚያጣጥመው ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን በሜዳው ሶስት ግብ አስታቅፎ ሆድ ቁርጠት ለቆበታል። በዕለቱ ግጥሚያ የሊቨርፑሉ ሱዋሬዝ ብቃቱን በማሳየት ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ኡራጉያዊው በሶስት ተከላካዮች መካከል አፍተልትሎ የመጀመሪያዋን ግብ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ፣ በ16ኛው ደቂቃ ደግሞ የሬንጀርሱ በረኛ የተፋትን ኳስ ተረጋግቶ ከመረብ አሳርፏል። ለሊቨርፑል በ28ኛው ደቂቃ ግድም ሶስተኛውን ግብ ያስቆጠረው ዳንኤል አጋር ነበር።

ቅዳሜ ዕለት ስምንት ግጥሚያዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ አርሰናል ኒውካስልን የጎል ጎተራ አድርጎ የሸኘበት ግጥሚያ አነጋጋሪ ሆኖዋል። አርሰናል ተፎካካሪውን 7 ለ3 በማርበድበድ ነበር የረታው። በዚሁ ፍልሚያ ለአርሰናል ዋልኮት በ20ኛው፣ 73ኛውና 90ኛው ደቂቃዎች ላይ ግብ በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል። ኦክስላዴ ቻምበርላይን በ50ኛው፣ ፖዶልስኪ በ64ኛው፣ ጂሮድ በ84ኛውና በ87ኛው ዲቂቃ ላይ ለአርሰናል ግብ አስቆጥረዋል። ለኒውካስል በ43ኛውና 69ኛው ደቂቃዎች ላይ ሴኔጋላዊው ዴምባ ባ አንደኛዋንና ሶስተኛዋን ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ፣ ማርቬክስም ለቡድኑ በ59ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ አስመዝግቧል።

የአርሰናሉ ቲዎ ዋልኮት (በግራ)
የአርሰናሉ ቲዎ ዋልኮት (በግራ)ምስል picture-alliance/dpa

በዚሁ በቅዳሜው ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ ዌስትሃም ብሮምዊችን ሁለት ለዜሮ አሸንፏል። 9ኛው ደቂቃ ላይ አሽሌ ያንግ በግራ በኩል ወደ ግብ የላካትን ኳስ የዌስት ብሮሚቹ ተከላካይ ጋሪክ ማክአሌ በስህተት ጨርፎ በራሱ መረብ ላይ እንድታርፍ አድርጓል። በ32ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ያንግ አክርሮ የመታትን ኳስ ቤን ፎስተር ከግቡ አግዳሚ ጋር አጋጭቶ አውጥቷታል። 89ኛው ደቂቃ ላይም እንዲሁ የዌስት ብሮሚቹ ግብ ጠባቂ ቤን ፎስተር ዳኒ ዌል ቤክ የመታትን ኳስ ማዳኑ ይጠቀሳል። ለማንቸስተር ሁለተኛዋንና የመጨረሻዋን ግብ በ90ኛው ደቂቃ ቫን ፔርሲ አስቆጥሯል። ቅዳሜ፥ ዊጋን አትሌቲክ አስቶን ቪላን 3 ለባዶ፣ ስዋንሲ ሲቲ ፉልሃምን 2 ለ1፣ ማንቸስተር ሲቲ ኖርዊች ሲቲን 4 ለ3፣ ቶትንሃም ሰንደርላንድን 2 ለ1፣ ሪዲንግ ዌስትሃም ዩናይትድን 1 ለምንም ሲያሸንፉ፤ ሳውዝ ሃምፕተንና ስቶክ ሲቲ 3 ለ 3 ተለያይተዋል።

በዚህም መሰረት የደረጃ ሰንጠረዡን ማን ዩናይትድ በ49 ነጥብ ሲመራ፣ ማንቸስተር ሲቲ 42 ነጥብ ይዞ ይከተለዋል። ቸልሲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ38 ነጥብ ሶስተኛ፣ ቶትንሃም በ36 ነጥብ 4ኛ፣ አርሰናል ከቶትንሃም በ3 ነጥብ ዝቅ ብሎ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሊቨርፑል በ28 ነጥብ ከማንቸስተር ዩናይትድ በ21 ነጥቦች ዝቅ ብሎ 9ኛ ደረጃን ይዟል። ትናንት በሊቨርፑል የተሸነፈው ኪው ፒ አር በወራጅ ቀጣናው የመጨረሻው አውራ ሆኖ ሰፍሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንምስል Getty Images/AFP

የኢትዮጲያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ላይ ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ የኒጀር አቻውን 1 ለባዶ አሸንፏል። በ38ኛው ደቂቃ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለፈው የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት ከሆነችው ዛምቢያ ጋር የመጀመሪያውን ግጥሚያ ለማድረግ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ ይጠብቀዋል። ጨዋታውን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን እንዲነግሩን ከብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር ቀጠሮ ይዘን የነበረ ቢሆንም፤ ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ሳይሳካልን ቀርቷል።

አድማጮች የአፍሪቃ ዋንጫ ከተነሳ አይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውድድሩ ስለገባችው ኬፕ ቬርዴ ቡድን አጠር ያለ ዘገባ እናቅርብላችሁ። ኬፕ ቬርዴ በምዕራባዊ አፍሪቃ 570 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በማዕከላዊ አትላንቲክ ውቅያኖስ ስትገኝ፤ 10 ደሴቶች አሏት። ብሔራዊ ቡድኗ «ሠማያዊ ሻርኮቹ» ይሰኛል። ሀገሪቱ በምትገኝበት ውቅያኖስ እንዳሻቸው የሚንፏለሉትን ሻርኮች በማስመልከት የተሰጠ ስያሜ ነው። ታዲያ እነዚህ የባህር ላይ ሻርኮች ከዚህ ቀደም አንበሶችን ሰልቅጠው ያውቁ እንደሆን የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ግን «ሠማያዊ ሻርኮቹ» የሚል ስያሜ የተሰጠው የሀገሪቱ የእግር ኳስ ቡድን በእርግጥም «አንበሶቹ» የሚል ስያሜ ያለውን ሃያሉን የካሜሩን የእግር ኳስ ቡድን ጭጭ ነው ያደረገው። 2 ለ ባዶ በማሸነፍና 2 ለ 1 በመሸነፍ ቡድኑ ካሜሩንን ከአፍሪቃ ዋንጫ ወድድር ውጪ አድርጓታል። የቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪቃ ዋንጫ ተሰላፊ መሆኑን አስመልክቶ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ድጋፋቸውን በዚህ መልኩ ገልዋል። «ይህ ስኬት መላ የኬፕ ቬርዴን ነዋሪ የሚያስተሳስር ነው ብዬ አስባለሁ። በእርግጥም ይህን ታላቅ ዋጋ ያለው ውጤት በማጣጣም በዚሁ ለአፍሪቃ ዋንጫ የመጨረሻ ጉዞ እንዘጋጃለን።»

የኬፕ ቬርዴ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የገንዘብ ችግር ያለበት ይመስላል። ቡድኑ የአፍሪቃ ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍን ያህል ታሪካዊ ድል አስመዝግቦ ለእያንዳንዱ ተጫዋች የደረሰው 1814 ዩሮ ብቻ ነው። በአጠቃላይ ቡድኑ 45 ሺህ ዩሮ ገደማ እንዳገኘም ታውቋል። ለደቡብ አፍሪቃው ፍልሚያ ለጉዞ የሚሆነውን በጀት ቡድኑ ከመንግስት የሚያገኝ ቢሆንም የኬፕቬርዴ ህዝብም ቡድኑን በገንዘብ እንደሚደግፍ ይጠበቃል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሉሲዎ አንቱኔስ «ዋነኛ ግባችን ሩብ ፍፃሜ ላይ መድረስ ነው። ሆኖም ማን ያውቃል ግማሽ ፍፃሜም ይሳካልን ይሆናል።» ሲሉ ለቡድናቸው ያላቸውን ምኞት ገልፀዋል። በእርግጥም አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃን፣ ሞሮኮንና አንጎላን የምትገጥመው ኬፕ ቬርዴ በአፍሪቃ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ ምን አይነት ውጤት ታመጣ እንደሆን ማን ያውቃል? «አንበሶቹ» የተሰኙት ካሜሮኖችን የሰለቀጠውን «ሠማያዊ ሻርክ» ቡድኗን ይዛ አይደል የምትሳተፈው?

የኬፕ ቬርዴ ሠንደቅ-ዓላማ
የኬፕ ቬርዴ ሠንደቅ-ዓላማ

ታዋቂው ቢስክሌተኛ ላንስ አርምስትሮንግ አበረታች መድሃኒት ወስደሃል በሚል እ ጎ አቆጣጠር ከ1998 አንስቶ በተከታታይ ለ7 ጊዜያት ያሰባሰበው ድል ውድቅ የተደረገበትን ክስ በተመለከተ ይግባኝ የሚያቀርብበት ጊዜ ማለፉ ታወቀ። አርምስትሮንግ እስከዛሬ ያገኛቸው ውጤቶቹ በአጠቃላይ ውድቅ የተደረጉት በዓለም አቀፍ የብስክሌት ኅብረት ነው። መቼም ቢሆን በውድድር ወቅት ሀይል ሰጪ መድሃኒት ተጠቅሞ እንደማያውቅ የሚገልፀው አርምስትሮንግ የዩናይትድ ስቴትስ ፀረ አደንዛዥ ዕጽ ኤጀንሲ ያቀረበበት ክስ ላይ የጀመረውን የህግ ክትትል ከወራት በፊት መተዉ ይታወቃል።

ላንስ አርምስትሮንግ
ላንስ አርምስትሮንግምስል Reuters

የግብፅ መንግስት ለአንድ ዓመት ግድም ያገደው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እንዲጀመር መወሰኑ ተነገረ። በፖርት ሳይድ ከተማ የታዋቂው አል አህሊ ቡድን ደጋፊዎች በአል ማስሪ ደጋፊዎች በተጠቁበት ወቅት በተከሰተው ግጭት 74 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነበር የግብፅ መንግስት ፕሪሚየር ሊጉን አግዶ የቆየው። ፕሪሚየር ሊጉ ከጥር 25 አንስቶ እንደሚጀምር ተገልጿል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ