1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 2 ቀን 2007 ዓ.ም.

ሰኞ፣ የካቲት 2 2007

30ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ «ዝሆኖቹ» በመባል የሚታወቁት ኮትዲቯሮች እጅ ገብቷል። እሁድ የካቲት 1 ቀን 2007 ዓም ጋናውያን በእንባ ታጥበዋል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸንፎ ከወራጅ ቃጣናው ወጥቷል። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ እየገሰገሰ ነው።

https://p.dw.com/p/1EYif
Elfenbeinküste gewinnt den Afrika-Cup
ምስል Reuters

ዝሆኖቹ የሚሰኙት ግዙፎቹ ኮትዲቯሮች በአፍሪቃ ዋንጫ ፍልሚያ በእርግጥም ግዙፍ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ዋንጫውን የጨበጠው ያያ ቱሬ ከወንድሙ ኮሌ ቱሬ እና ከዝሆኖቹ ጋር ጮቤ ሲረግጥ፤ የጥቋቁር ከዋክብቱ ወንድማማቾች አንድሬ እና ጆርዳን አየው ግን እንባ ተራጭተዋል። የአባታቸው የአቢዲ ፔሌ አየውን የሽንፈት እና የስኬት ዘመን እያስታወሱ አቀርቅረዋል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የቀድሞው ኃያል የዘንድሮው ምስኪን ቦሩስያ ዶርትሙንድ የ3 ለባዶ ድሉ ከጉድ አውጥቶታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ተጋጣሚዎቹ አቻ ተለያይተዋል። ቸልሲ ከላይ እንደተኮፈሰ ነው። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ የ4 ለባዶ ከባድ ሽንፈት ቀምሷል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ባታ ስታዲየም ትናንት እምባ እና ሳቅ ተደባልቆባት፤ ጮቤ እና ሀዘን ተፈራርቆባት አምሽታለች። ጥቋቁር ከዋክብት በሚል ስያሜ ነጭ መለያ ለብሰው ሜዳው ውስጥ ያንፀባረቁት ጋናዎች በብርቱካናማ መለያ «ዝሆኖች» ነን ባሉት ኮትዲቯሮች የማታ ማታ ፍካታቸው ጸልሟል። እልህ ወኔያቸው በመጨረሻዋ ሠከንድ በእምባ ተውጧል። ያለምንም ግብ የተጠናቀቀው መደበኛ ሠዓት የባከነውም ተጨምሮበት በ120ኛው ደቂቃ ግብ አልባ ሆኖ አክትሟል። ጨዋታው ወደ መለያ ምት ሲያመራ የሁለቱ ሃገራት ግብ ጠባቂዎች እያንዳንዳቸው ለ11 ጊዜያት በጥቅሉ ሃያ ሁለቴ ወደ ግቡ ተመላልሰዋል። በስተመጨረሻ ኮትዲቯር ኹለት ስታ 9 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፋ ዋንጫውን በእጇ ለማስገባት ችላለች። 3 የሳተችው ጋና በ8 ግብ ተወስና ዋንጫው ህልም ሆኖባታል። አንድ የኮትዲቯር ደጋፊ ሀገሩ ዋንቻ በማግኘቷ ደስታውን እንዲህ ገልጧል።

«ዝሆኖቹ» በመባል የሚታወቁት የኮትዲቯር ተጨዋቾች
«ዝሆኖቹ» በመባል የሚታወቁት የኮትዲቯር ተጨዋቾችምስል REUTERS/Amr Abdallah Dalsh

«በጣምነው ደስ ያለኝ በፍፃሜ ጨዋታዎች በተደጋጋሚ ተሸንፈናል። ዛሬ ግን በአዲሱ ትውልድ በተገነባው ቡድን አሸንፈን ዋንጫውን አግኝተናል። በኮትዲቯራዊነቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ኩራት ይሰማኛል። ከግማሽ ፍፃሜው አንስቶ ለእዚህ ቡድን ትልቅ ግምት ሰጥቼው ነበር።»

ኮትዲቯሮች ዋንጫ ብቻ አይደለም 1.5 ሚሊዮን ዶላርም ተሸልመዋል። 33 ዓመታት በትእግስት የጠበቀችው ጋና ዋንጫውን ለ5ኛ ጊዜ ለማግኘት አልታደለችም። የጋና ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ወንድማማቾቹ አንድሬ አየው እና ታናሹ ጆርዳን አየው የአባታቸው አቢዲ ፔሌ አየውን የዘመናት ሽንፈት ሳይበቀሉ ቀርተዋል።

አባታቸው አቢዲ ፔሌ አየው እጎአ በ1992 ሴኔጋል ውስጥ በተደረገው 18ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ፣ ቀይ ጃኬቱን እንደደረበ ቅያሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ የቡድኑን ሽንፈት የተመለከተበትን ክስተት ብዙዎች አንስተውታል። ያኔ የጋና ቡድንን ያሸነፈው ይኸው የኮትዲቯር ቡድን ሲሆን፤ ውጤቱም 11 ለ 10 ነበር።

በእርግጥ ጋና የዛሬ 33 ዓመት እጎአ በ1982 ዋንጫውን ሊቢያ ቤንጋዚ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ሲጨብጥ አባታቸው አቢዲ ፔሌ አየው ከቡድኑ ጋር ነበር። ያም ብቻ አይደለም ጋና 2 ለባዶ ስትመራ ቆይታ ተጋጣሚያዋ አልጄሪያን 3 ለ2 ማሸነፏም ልዩ ታሪክ ሆኖ በቤተሰቡ ውስጥ ሳይሰርጽ አይቀርም። አባታቸው አቢዲ ፔሌ አየው ለሦስት ጊዜያት የአፍሪቃ እግር ኳስ የዓመቱ ምርጥ ሆኖ መሸለሙ ይታወሳል። ይኽ ሁሉ ተደማምሮም ሳይሆን አይቀርም ጋና ስትሸነፍ የ25 ዓመቱ አንድሬ አየው ሜዳ ውስጥ የማንባቱ ምስጢር። ታናሽ ወንድሙም በእንባ ሲታጠብ የነበረው አንድሬን ሲያባብለው ታይቷል።

አንድሬ አየው ኳሷን ሲገፋ፥ ማክስ ግራዴል ሲከተለው
አንድሬ አየው ኳሷን ሲገፋ፥ ማክስ ግራዴል ሲከተለውምስል Khaled Desouki/AFP/Getty Images

የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ 9 ለ8 ተሸንፎ በእንባ ለታጠበው ቡድናቸው የማጽናኛ ደብዳቤ መላካቸውም ተዘግቧል። ፕሬዚዳንቱ በትዊተር መልእክታቸው እንዲህ ሲሉ ነው ማበረታቻ ያሰሙት። «ክብር ለጥቋቁር ከዋክብቱ። ምንም እንኳን ብንሸነፍም ድንቅ ጨዋታ ነበር። ከጠበቅነው በላይ ልቃችሁ ተገኛችሁ፤ ከዜሮ ተነስታችሁ ጀግንነታችሁን አሳያችሁ። ኮርቼባችኋለሁ» ብለዋል። በእርግጥም ጋና አጠቃላይ ጨዋታው ሲገመገም ኮትዲቨርን በልጣ ነበር።

የኮትዲቨር አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ እና የግብ ጠባቂው ቡባካር ባሪ ልዩ ብቃት ዝሆኖቹ በሚል የሚታወቁት ኮትዲቯሮች ዋንጫውን እንዲጨብጡ አስችሏል። በ28ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ዛምቢያን ይዘው ዋንጫ የጨበጡት አሠልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ጄርቪንሆን ይቀይሩታል። ጄርቪንሆ በዛምቢያው ግጥሚያ ወቅት ሁለቱን የመለያ ምቶች ከሳቱት ተጨዋቾች አንዱ ነበር። ግብጠባቂው የጋና ተጫዋቾች ላይ በሰውነት እንቅስቃሴ እና በቃላት የስነልቦና ተጽዕኖ ማድረሱም ኮትዲቯርሮች ለማሸነፋቸው አስተዋፅዖ አድርጓል።

በዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ አዘጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒን በመለያ ምት 4 ለ 2 ማሸነፍዋይታወሳል። የአስተናጋጇ ሀገር ደጋፊዎች የጋና ደጋፊዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ጨዋታው በመቋረጡ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ኢኳቶሪያል ጊኒን የ100 ሺህ ዶላር መቅጣቱ ይታወቃል። የዘንድሮውን የአፍሪቃ ዋንጫ በኢቦላ ተሐዋሲ ፍራቻ አላስተናግድም ያለችው ሞሮኮ በሚቀጥሉት ሁለት ተከታታይ የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ እንዳትሳተፍ ቅጣት ተበይኖባታል። በዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታ ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቀው የዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኪዲባ በ39 ዓመቱ በመጫወት በእድሜ ከሁሉም አንጋፋ መሆኑን አስመስክሯል።

አቤዲ ፔሌ ከፊት፤ ጀርመን ውስጥ በሚጫወትበት ጊዜ
አቤዲ ፔሌ ከፊት፤ ጀርመን ውስጥ በሚጫወትበት ጊዜምስል picture-alliance/dpa

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ ቸልሲ አስቶን ቪላን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 56 አድርሶ በአንደኛነት ይገኛል። ከሁል ሲቲ ጋር አንድ እኩል የተለያየው ማንቸስተር ሲቲ በ49 ነጥብ ይከተለዋል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሳውዝ ሐምፕተን በደረጃ ሠንጠረዡ መጨረሻ ከሚገኘው ላይስተር ከፍ ካለው ኪው ፒ አር ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥቡ 45 ነው። በ44 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስትሐም ዩናይትድ ጋር አንድ እኩል አቻ ተ ለያይቷል። አምሰተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሐም ሆትስፐር የሰሜን ለንደን ተቀናቃኙ አርሰናልን 2 ለ 1 አሸንፎ ስድስተኛ ደረጃ ላይ እንዲወሰን አድርጎታል። ቶትንሐም 43 ነጥብ ሲይዝ አርሰናል በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ 42 ነጥብ ሰብስቧል። 39 ነጥብ ያለው ሊቨርፑል አርሰናልን ተጠግቶ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሞት አፋፋ ደርሶ ለጊዜው መለስ ብሏል። ፍራይቡርግን 3 ለዜሮ ማሸነፍ የቻለው ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ ከሚገኝበት 18ኛ እና የመጨረሻ ደረጃ ከፍ ብሎ 16ኛ ለመሆን ችሏል። ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በአርየን ሮበን እና ዳቪድ አላባ ግቦች ሽቱትጋርትን 2 ለባዶ ረትቷል። ምድቡንም በ49 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሆፈንሃይምን በሜዳው 3 ለዜሮ ያሰናበተው ዎልፍስቡርግ በ41 ነጥብ ይከተላል። ሻልካ 34ነጥብ ይዞ ይሰልሳል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ
ቦሩስያ ዶርትሙንድምስል Reuters/A. Wiegmann

በስፔን ላሊጋ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ በአትሌቲኮ ማድሪድ 4 ለባዶ ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ከቅጣት የተመለሰው የዓለም ኮከቡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለቡድኑ ምንም ሊፈይድ አልቻለም። ሆኖም ሪያል ማድሪድ አሁንም ምድቡን በ54 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሊዮኔል ሜሲ ግብ ባስቆጠረበት ፍልሚያ ባርሴሎና አትሌቲኮ ቢልባዎን 5 ለ2 አሸንፏል። ባርሳ በ53 ነጥብ ሪያል ማድሪድን ተናንቆ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ