1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ-25-2007 ዓ.ም

ሰኞ፣ ነሐሴ 25 2007

ቤጂንግ ውስጥ በተካሄደው የሴቶች የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1-3 ተከታትለው በመግባት ድል አስመዝግበዋል። አትሌት አልማዝ አያና ተፎካካሪዎቿን በረዥም ርቀት በመቅደም 14 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሩጫውን በአንደኝነት አጠናቃለች።

https://p.dw.com/p/1GOjK
China Leichtathletik WM in Peking Akmaz Ayana besondere WM-Momente
ምስል Reuters/L. Nicholson

ሁለተኛ ሰንበሬ ተፈሪ ሦስተኛ ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ በመግባት የውድድሩ አሸናፊዎች ሆነዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ሩጫ በፊትም ሌላ አስደሳች ድል ተቀዳጅታለች። በሴቶች የማራቶን ውድድር ማሬ ዲባባ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ 2ኛውን ወርቅ አስመዝግባ ነበር።

የብሪታንያው አትሌት ሞ ፋራህ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አይበገሬ መሆኑን በቤጂንጉ ዉድድር ላይ በድጋሚ አስመስክሮአል። ቤጂንግ ውስጥ በተከናወነው የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ሞ ፋራህ ወርቁን ሲወስድ በኦሎምፒክ አልያም በዓለም አቀፍ ፉክክር በ5 ሺህ እና በ10ሺህ ሜትር በተከታታይ 7ኛ ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል። ሞ ፋራህ በ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የዓለም ሻምፒዮና ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ የወርቅ ተሸላሚ በመሆን ታሪክ ሠርቷል።

China Kathrina Molitor bei der Leichtathletik-WM in Peking
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የ32 ዓመቱ ትውልደ-ሶማሊያ የብሪታንያ ዜጋ ሞ ፋራህ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 በዴጉ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር በኢትዮጵያዊው አትሌት ኢብራሒም ጄላን ከተሸነፈ ወዲህ በዘርፉ የሚረታው አልተገኘም። በቤጂንጉ የወንዶች የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ሐጎስ ገብረሕይወት ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል። በዚህ ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው የኬንያው አትሌት ካሌብ ምዋንጋኚ ንዲኩ ነው። አትሌት ዮሚፍ አጄልቻ በአራተኛነት አጠናቋል። ሌላኛው አትሌት ኢማነ መርጋ በ13ኛነት ውድድሩን ጨርሷል። በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄደዉን የስፖርት እንቅስቃሴ በተመለከተ የለንደንዋ ወኪላችን ያጠናቀረችዉን ሙሉ የድምፅ ዘገባ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

ሀና ደምሴ

አዜብ ታደሰ