1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርቱ የነገ ተስፋ

ዓርብ፣ ጥቅምት 23 2011

አትሌቲክሱ ውጤት እየራቀው መቷል። በተለይም የቤጅንግ ኦሎምፒክ ውጤት ሳይመጣ መቅረቱ ያኔ ለዚህ አካዳሚ መቋቋም የሀሳቡ ጥንስስ ነበር

https://p.dw.com/p/37YI4
Äthiopien Addis Abeba Jugendsport Akademie
ምስል Alamrew Mamo

ሳይንሳዊ የስፖርት ስልጠና ይሰጣቸዋል

ችሎታን የበለጠ በስልጠና ለማዳበር የስፖርት ማሰልጠኛ ተቋም ትልቅ እገዛ ያደርጋል። በዓለም አቀፍ የስፖርት ስልጠና አካዳሚ ወጣቶችን በማፍራቱ የተለመደ ነው። አገራት ወጣቶችን የሚያፈሩበት የስልጠና ማዕከል ከፍተው ለነገው ተስፋ ይኮተኩቷቸዋል። እንደፍላጎታቸው ወደ አካዳሚዉ በመግባት በስልጠና ይታገዛሉ።
ኢትዮጵያ በተለይም በአትሌቲክሱ ከዓለም በ5,000 እና 10,000 ሺህ ሜትር እንዲሁም በማራቶን ስሟ በቀዳሚነት ይነሳል። ዓለም የማይረሳቸው ታዋቂ የስፖርት ሰዎችንም አፍርታለች። በስልጠና ባልታገዙበት በዛን ዘመን፤ በፍላጎትና በአገር ፍቅር ለድል በቅተዋል። በስፖርቱ ዘርፍ በወጣቶች ተስፋ ሰንቆ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተቋቋመ።  አካዳሚው በ2005 ተመርቆ በ2006 ዓ.ም ስፖርተኞችን መልምሎ ስራውን ጀምሯል። ለሁለት ጊዜ ያህልም ሰልጣኞችን አስመርቋል። በአትሌቲክስ፣ በፓራ ኦሎምፒክ፣ በቮሊ ቮል፣ በእግር ኳስ፣ በውኃ ዋና፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በጠረንጴዛ ቴንስ፣ በቦክስና በብስክሌት የስፖርት አይነቶች ስልጠና ይሰጣል።
በ2002 ዓ.ም የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰላ ላይ የተከፈተ ሲሆን በአዋጅ የአዲስ አበባው ሲከፈት ከኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ጋር በአንድነት እንዲካተት ተደርጓል።
አቶ አላምረው ማሞ በአካዳሚው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው። የስልጠና ማዕከሉ በስፖርቱ ዘርፍ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት፣ ስልጠናዎችን በመስጠት እና ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ አላማው አድርጓል። ዛሬ ዛሬ አትሌቲክሱ ውጤት እየራቀው መቷል። በተለይም የቤጅንግ ኦሎምፒክ ውጤት ሳይመጣ መቅረቱ ያኔ ለዚህ አካዳሚ መቋቋም የሀሳቡ ጥንስስ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለ4 ዓመታት እዛው በግቢው ውስጥ ወጭያቸው ተሸፍኖ በስልጠና ይቆያሉ። በዚህ ጊዜ ስፖርታዊ ስልጠናዎችና የመደበኛ ትምህርታቸውን ይማራሉ። ሳይንሳዊ የስፖርት ስልጠና ይሰጣቸዋል።
ከዘልማዳዊ አሰራር ወቶ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በንድፈ ሀሳብ ላይ የተመረኮዘ፤ በአጋዥ የቪዲዮ ምስልም ይታገዛል።
አካዳሚው ከምልመላ መስፈርቶቹ አንዱ የዕድሜ ገደብ ነው። እድሜያቸው ከ 15 እንዲሁም ከ 17 ዓመት በታች የሆኑ ወንድና ሴት ይቀበላል። ሌላው መስፈርቱ ተሰጥኦ ያለው ሊሆን ይገባል ይላሉ አቶ አላምረው።
አንድ ሰልጣኝ በውድድር ተፈትሾ እንዲታይ ውድድሮች ላይ ይሳተፋል። በዚህም በክለቦችና በአሰልጣኞች እንዲመለመል ዕድል ይኖረዋል። በአሁኑ ጊዜ በጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስና ፓራ ኦሎምፒክ 189 ሲሆኑ በአዲስ አበባው አካዳሚ 259 ሰልጣኞች በ10 ስፖርት ዓይነቶች ይሰለጥናሉ። ወጣቶቹ ከሀገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እየሆኑ እንደሆነ አቶ አላምረው ይገልጻሉ። 
አቶ ተሾመ ከበደ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ናቸው። ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በጥሩነሽ ዲባባ ከዛም በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። በሀገራችን ከሚሰጡ ስልጠናዎች አካዳሚው በተሻለ መልኩ ሳይንሳዊ ስልጠናዎቹ የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ።  
አብርሃም ስሜቱፋ እና ጌትነት ዋለ በስልጠና ማዕከሉ ሰልጣኝ ናቸው። አብርሃም 17 ዓመቱ ሲሆን ከአሰላ በ2008 ዓ.ም በአትሌቲክስ ለማዕከሉ ተመልምሏል። የ 19 ዓመት ወጣቱ ጌትነት በ3,000 ሜትር መሰናክል ይሰለጥናል። ተመልምሎ የመጣው ከጎጃም ነው። 
አብርሃም ስልጠናው በሳይንስ የተደገፈ ነው ይላል። አካዳሚው መከፈቱ በተለይ በክልል ላሉ ስፖርተኞች ትልቅ ዕድል ነው ጌትነት እንዳለው።

Äthiopien Addis Abeba Jugendsport Akademie
ምስል Alamrew Mamo
Äthiopien Addis Abeba Jugendsport Akademie
ምስል Alamrew Mamo

ነጃት ኢብራሂም
አዜብ ታደሰ