1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴ ካ ፋ ግጥሚያ እና ፖለቲካዊ መልዕክቱ

ረቡዕ፣ ሰኔ 19 2005

በእግሊዝኛ ምሕፃሩ ሴ ካ ፋ የሚባለዉ የእግር ኳስ ማሕበር የሚያስተናብራቸዉ 11 የምሥራቅ እና የማዕከላይ አፍሪቃ አገሮች የእግር ኳስ ቡድኖች በሱዳን የዳርፉር እና የደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች አመታዊ የዋንጫ ግጥሚያቸዉን ባለፈው ሣምንት ማክሰኞ፣ እአአ ሰኔ 18፣ 2013 ዓም ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/18x1u
በዩጋንዳና በሱዳን መካከል ግጥሚያው በካዱግሊ ሲከፈት 18-06-2013ምስል EBRAHIM HAMID/AFP/Getty Images

እንደሚታወቀው ግጥሚያዉን በሚያስተናግዱት በነዚህ ሁለት ግዛቶች የሚንቀሳቀሱ ዓማፅያን በሱዳን መንግሥት አንፃር በሚያካሂዱት ውጊያ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶዋል፣ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በሱዳን ሀገር ጎብኚዎች ካለስጋት ሊዘዋወሩባቸው የሚችሉ ከዳርፉርና ከደቡብ ኮርዶፋን የተሻሉ ሌሎች ቦታዎች አሉ። የጀርመን መንግሥት ዜጎቹ ራሳቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ባይጎበኙዋቸው ይሻላል በሚል በሚያወጣው የቦታዎች ዝርዝር ውስጥ ዳርፉርና ደቡብ ኮርዶፋን ይገኙባቸዋል።  ያም ቢሆን ግን፣ የእግር ኳሱ የዋንጫ ግጥሚያ የሚካሄደው በነዚህ ግዛቶች ነው። እነዚህ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር እንደሌላቸው ነው የሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር አህመድ ቢላል የሚያስረዱት።
« ውድድሩን ካዱግሊን እና ዳርፉርን በመሳሰሉ ቦታዎች ማካሄዱ ጥሩ ሀሳብ ነው። ምክንያቱም  ዳርፉር አስተማማኝ ቦታ አይደለም፣ በካዱግሊ የቦምብ ጥቃት ይካሄዳል የሚል ብዙ ወሬ ይናፈሳል፤ እኛ ግን አካባቢው ሰላማዊ መሆኑን እና አሸባሪዎቹ በጣም ርቀው እንደሚገኙ ነው በመንገር ላይ ያለነው። የግጥሚያውም ዋነኛ መልዕክት ይኸው ነው። »
የማስታወቂያ ሚንስትሩ «አሸባሪዎች » የሚሉዋቸው ዓማፅያን ግን፣ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ በካዱግሊ ግጥሚያው በተከፈተ ዕለት ከተማይቱን በቦምብ አጥቅተዋል። ሚንስትሩ ግን ጥቃቱ ከስቴድየሙ ርቆ እን,ደተጣለ ነው ያመለከቱት። የሱዳንን ፖለቲካ ጠንቅቀው የሚያውቁትን ሱዳናዊውን ምሁር ኤል ጊዙሊን የመሳሰሉ ጠበብት እንደሚያምኑት፣ የሱዳን መንግሥት፣ የፀጥታው ሁኔታ ግጥሚያው ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ውጭ አስተማማኝ እንዳልሆነ እያወቀ ነው ግጥሚያውን በነዚህ ግዛቶች እንዲካሄድ ያደረገው።
« በሌሎች የሱዳን አካባቢዎች ለሚኖሩት ሁሉ መንግሥት ሁኔታውን እንደተቆጣጠረ እና የውጭ ቡድኖች ወደአገሩ መጥተው መጫወት ይችሉ ዘንድ የቦምብ ጥቃት የሚያሰጋቸውን አካባቢዎችንም ፀጥታ ማስጠበቅ እንደሚችል ለማሳየት ያደረገው ነው። »
ኤል ጊዙሊ አክለው እንዳስረዱት፣ በሀገሩ ገፅታው እየተበላሸ የሄደው የሱዳን መንግሥት ጥንካሬውን ማሳየት ይፈልጋል።  ዓማፅያኑ ለወትሮው ብዙም በማይንቀሳቀሱበት በማዕከላይ የሱዳን የምትገኘውን የኡም ራዋባ ከተማን ባለፈው ሚያዝያ  ተቆጣጥረው እንደነበር አይዘነጋም። ምንም እንኳን ኻርቱም የሚገኘው የካርቱም መንግሥት ጦር ኃይል ከተማይቱን መልሶ ቢቆጣጠርም ጥቃቱ ለአገሪቱ መንግሥት ሳያስደነግጥ እንዳልቀረ ጠበብት ገልጸዋል።
ግጥሚያው በዳርፉር እና በደቡብ ኮርዶፋን እየተካሄደ ያለበት ድርጊት ከፖለቲካ ጋ ግንኙነት አለው በሚል የተሰማውን አነጋገር ሴ ካ ፋ አስተባብለዋል። ከዶይቸ ቬለ ጋ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የሴ ካ ፋ  ዋና ፀሐፊ ኒከላስ ሙሶነየ ማሕበራቸው የዋንጫውን ግጥሚያ ካሁን ቀደምም በበርካታ አፍሪቃውያት አገሮች መዲናዎች ውጭ አካሂዶዋል።  ሙሶንየ ውድድሩ ውዝግብ ያዳቀቃቸውን አካባቢዎች ያሉትን ነዋሪዎች ለማቀራረብ ይረዳል ባይ ናቸው።
« ወደ አል ፋሸር ብተመጣ ወይም ወደ ካዱግሊ ብትሄድ፣ ስዉ በኳስ ጨዋታው ሲደሰት ነው የምተመለከተው። ሕዝቡ ባንድነት ግጥሚያውን ይከታተላል፤ ይደሰታል። መዋጋት የሚፈልጉት እንኳን መዋጋት አይችሉም። የእግር ኳስ ሰላምን እና ወዳጅነትን ማስገኘት የሚያስችል መሣሪያ ነው፣ እና ልንጠቀምበት ይገባል። »
ይሁን እንጂ፣ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ውዝግቦችን የሚያበቃ አይመስልም። እርግጥ፣ በካዱግሊ እና በኤል ፋሸር ከተሞች ጨዋታው በሰላም እየተካሄደ ነው፣ ይሁንና፣ በከተሞቹ መጋቢያ የኃይሉ ተግባር እንደቀጠለ ነው። አንድ የደቡብ ዳርፉር ኃላፊ እንደገለጹት፣  ባለፈው ሣምንት እንኳን በጎሣዎች መካከል በተካሄደ ግጭት 11 ሰዎች ናቸው የተገደሉት። ይህ ግጭትም የመጨረሻው እንደማይሆን ነው ሁኔታዎች የጠቆሙት።

Flüchtlinge Kurdufan Sudan
የደቡድ ኮርዶፋን ስደተኞችምስል picture alliance/dpa
Darfur - JEM Kämpfer
የዳርፉር ዓማፅያንምስል Getty Images

ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ