1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ኅዳር 20 2010

የሳዑዲ አረብያ መንግሥት በአገሪቱ ሕጋዊ የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸዉ የዉጭ ዜጎችን ወደየሀገራቸዉ መመለስ መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/2oURo
Saudi Arabien Arbeiter kehren nach Äthiopien zurück
ምስል DW/S. Shiberu

Undocumented Ethiopian in Saudi Arabia - MP3-Stereo

መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ/ም የሰዑዲ አረብያ መንግሥት በአገሪቱ ሕጋዊ የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸዉ የዉጭ ዜጎች በ90 ቀን ዉስጥ ወደየሀገራቸዉ እንዲመለሱ ማሳሰቡ ይታወሳል። ይህ የግዜ ገደብ ሁለቴ ተራዝሞ የመጨረሻዉ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ/ም ማብቃቱ ተነግሯል። ያለ ሕጋዊ የመኖርያ ፍቃድ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ወደ 400,000 ገደማ መሆናቸዉ ቢነገርም እስካሁን ወደሀገር ቤት 70,000ዎቹ መመለሳቸዉን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ኢድርስ ሙሃመድ ሕጋዊ የመኖርያ ፍቃድ ከሌላቸዉ አንዱ ነዉ። ኢድርስ ከሳዑዲ አረብያ ዋና ከተማ ከሆነችዉ ርያድ ወደ 450 ክሎ ሜትር ርቃ በምትገኛዉ ሀፍፍ ተብለ የምትጠራ አንድ መጠነኛ ከተማ እንደሚኖር ይናገራል። በአካባቢዉ ያለዉ ገጠር ዉስጥ እሱና ሌሎች ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ከመጡ 40 ሰዎች ጋር በግብርና ስራ ላይ እንደተሰማራም ጠቅሷል። ይሁን እንጅ በትላንትናዉ ዕለት ከኢትዮጵያ ከመጡት 23፣ ከሱዳን አምስት ሰዎች በሳዑዲ የፀጥታ አካል መያዛቸዉን በዋትስአፕ የላከልን መልክት ያመለክታል።

ኢድሪስ የኔም ዕጣ ፋናታ ተይዞ መመለስ ቢሆንም ሄጄ ለሳዑዲ መንግስት ያዙኝ ብዬ እጅ አልሰጥም ይላል።

Saudi Arabien Äthiopien Rückkehrer
ወደ ኢትዮጵያ ተመላሾች በርያድ ምስል DW/S. Shiberu

ይህን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘዉ በሳዑዲ የሚኖረዉ ባልደረባየ ስለሺ ሽብሩ ነዉ።

የሳዑድ መንግሥት አዋጅ ማዉጣት እንጅ መፈፀም አይችልም ፣ አገር ቤት ገብተን ምን እናደርጋለን፤ የባሰ አይደለም ወይ የሚል አቋም የያዙ መመለስ እንደማይፈልጉ መረዳት መቻሉን ስለሺ ይናገራል።  የምህረት ግዜ በተደጋጋሚ በመራዘሙ ምክንያትም ወደ ኢትዮጵያ በአዉሮጵላን የሄዱት በባህር ተመልሰዉ  እየመጡ እንደሆነም ታዝቤያለሁም ብሏል። ይሁን እንጅ አሁን የሳዑድ መንግሥት የያዘዉ አቋም ለሌሎች ይቅርና የራሱንም ዜጎች እንደማይምር ስለሺ ስጋት አለዉ።

ኢድሪስ ከአራት ዓመት በፊት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በፍቃዳቸዉ ቢመለሱም ብዙም ሳይቆዩ ተመልሰዉ መምጣታቸዉን ይናገራል። ለዚህም ምክንያት የሆነዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል የገባዉ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ድጎማ እዉን ባለመሆኑ እንደሆነም ይገልጻል።

ከመንግሥት አካላት በኩል በጉዳዩ ላይ ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነዉ ሙከራ ለዛሬ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ