1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲድኒው የእገታ ጥቃት ማብቃት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2007

በኦስትሬሊያ የሲድኒ ከተማ አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ዛሬ ንጋት ላይ በርካታ ሰዎችን ያገተበትን አንድ ቡና ቤት የከተማይቱ ፖሊስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ማጥቃቱ እና በዚሁ ጊዜም ሁለት ሰዎች፣ መገደላቸውን፣ እንዲሁም ፣ ሶስት በጠና መቁሰላቸው ተገለጸ። ከተገደሉት መካከል አንዱ አጋቹ ነው።

https://p.dw.com/p/1E5FW
Australien Geiselnahme in Sydney beendet
ምስል Getty Images/J. Martinson

የሲድኒ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ አንድሩ ስኪፒየን ቀደም ሲል እንዳስረዱት፣ ግለሰቡ ያገታቸው ሰዎች ቁጥር በግልጽ አልታወቀም ነበር።

« አንድ የጦር መሳሪያ የታጠቅ ግለሰብ በከተማይቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን አግቶዋል። ፖሊስ ስለእገታው እንደተነገረው ወዲያው በጥዋቱ በቦታው በመገኘት ሁኔታውን ተቆጣጥሮዋል። እገታው ሰላማዊ ፍፃሜ እንዲያገኝ በአሁኑ ጊዜ እየሰራን ነው። ይህ እገታ በሰላማዊ ዘዴ መፍትሔ እንዲያገኝ እንፈልጋለን፣ ይህንንም ለማረጋገጥ የሚቻለንን ሁሉ በማድረግ ላይ ነን። »

ታጋቾቹ ወደ 30 እንደሚጠጉ ይገመታል። አንድ ታጋቾች አንድ የእሥልምና እምነት የተጻፈበት ጥቁር ባንዴራ በቡና ቤቱ መስኮት እንዲይዙ መገደዳቸው በቴሌቪዥን የቀረበ ስዕል አሳይቶዋል። ይህም ከእገታው በስተጀርባ ፅንፈኛ ሙሥሊሞች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ስጋት መፍጠሩን ስለ አጋቹ ማንነት ወይም ዓላማ እስካሁን እንደማይታወቅ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቲም አቦት ገልጸዋል።

« የአጋቹን ዓላማ ገና አላወቅንም፣ መነሻው ፖለቲካዊ መሆን አለመሆኑንም አናውቅም፣ ምንም እንኳን ፖለቲካዊ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች ቢኖሩም። »

አጋቹ እስካሁን ያቀረበው ጥያቄ ስለመኖሩ መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ቡና ቤቱን ያጠቁት የፖሊስ ኃላፊ አንድሩ ስኪፒየን አመልክተዋል። በመጨረሻ በወጡ ዘገባዎች መሠረት፣ አጋቹ በኦስትሬሊያ ተግን አግኝቶ የሚኖር የሀምሳ ዓመት የኢራን ተወላጅ መሆኑ ተገልጾዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ