1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የሲሚንቶ ግብይቱን መረጋጋት የነሳው ምንድነው?

ረቡዕ፣ ሰኔ 15 2014

የኢትዮጵያ መንግሥት አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎችን ከሲሚንቶ ግብይት ለማስወጣት ወስኗል። ገበያውን የሚያውቁ ውሳኔው እጥረትና የዋጋ ንረት ለበረታበት የሲሚንቶ አቅርቦት ዘላቂ መፍትሔ ለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው። በግብይቱ ይሳተፉ የነበሩ ነጋዴ "የባለሥልጣን ሚስቶችና ዘመዶች አከፋፋይ ሆነዋል። ሥርጭቱን ያበላሸው እሱ ነው" የሚል ብርቱ ወቀሳ ያቀርባሉ።

https://p.dw.com/p/4D5Ly
Äthiopien Addis Abeba im Bau
ምስል DW/E. Bekele

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የሲሚንቶ ግብይቱን መረጋጋት የነሳው ምንድነው?

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የሸክላ ምርት ማምረቻ አክሲዮን ማህበር በሥሩ ሁለት የብሎኬት ፋብሪካዎች ይገኛሉ። ፋብሪካዎቹ ከኩባንያው በርከት ያሉ የግንባታ ግብዓቶች ማምረቻዎች መካከል ናቸው። የኩባንያው ኃላፊ አቶ ወርቁ ጌታሁን "በመንግስት እውቅና የተሰጣቸው ሲሚንቶ አከፋፋዮች አሉ። ከእነሱ ነበር የምናገኘው። የሲሚንቶ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመሩም በላይ እንደ ልብ የማይገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ሲሚንቶ እንደልብ ባለመገኘቱ አሁን ባለው ሁኔታ የማምረት ሥራችንን አቁመናል ማለት ይቻላል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ወርቁ እንደሚሉት በገበያው በሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ ላይ የሚታየውን ለውጥ ድርጅታቸው በሚያመርታቸው ብሎኬቶች ላይ በማከል ልዩነቱን ወደ ደንበኞቻቸው ማሻገር አዋጪ ሆኖ ስላልተገኘ ወዳለመስራቱ አዘንብለዋል። "ለዋጋው መጨመር ዋናው ምክንያት የአቅርቦቱ እና የፍላጎቱ አለመመጣጠን ነው። በአገሪቱ ከፍተኛ የግንባታ ፍላጎት አለ። ከፍተኛ ሲሚንቶ የሚፈልጉ የመንግሥት እና የግል ፕሮጀክቶች አሉ። አገር ውስጥ ያሉ የማምረቻ ተቋማት ምርታቸው የደንበኛውን ፍላጎት የሚያሟላ ባለመሆኑ የተነሳ የተገኘውን ሲሚንቶ ስለምንሻማ የሲሚንቶ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል" ሲሉ አቶ ወርቁ ተናግረዋል።

መረጋጋት የራቀው የኢትዮጵያ የሲሚንቶ ገበያ ይፈትን የያዘው ግን እንዲህ የግንባታ ግብዓቶች አምራቾችን ብቻ አይደለም። የሎራት ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ ሉታሮ  "የሲሚንቶ እጥረት አልፎ አልፎ ይከሰት ነበር። እንዲያው በጣም ውድ ነው የሚባለው ባለፉት ጊዜያት ከ500 ብር ወጥቶ አያውቅም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው ግን በጣም የተለየ ነው" ሲሉ በአሁኑ ወቅት በገበያው የታየው ችግር የበረታ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

የግብይቱ ጠባይ "በብዛት በየጊዜው ይለዋወጣል" የሚሉት አቶ አበራ "ለምሳሌ እኔ የከፈልኩበት አመት ያለፈው አለ። ኮንትራክተሮች ከፍለው ይውሰዱ ተብሎ የተከፈለ ሲሚንቶ አንድ አመት ያለፈው አለ" በማለት የገጠማቸውን አብራርተዋል።

Äthiopien Oromia | Zementfabrik
የኢትዮጵያ ንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ባለፈው ሣምንት ከ13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 12ቱ የሚያመርቱት ከ50 በመቶ በታች በሆነ አቅማቸው መሆኑን ገልጿል። ምስል Seyoum Getu/DW

"አሁን እየተጠቀሙ ያሉት ፋብሪካ ያሉ ሰዎች እና አከፋፋዮች ናቸው። ባለኝ ልምድ ኮንትራክተሩ በራሱ ሔዶ ቢከፍልም ሲሚንቶ የማግኘት ዕድል የለውም" የሚሉት አቶ አበራ የግብይት አካሔዱ በፍጥነት መለዋወጥ ኹነኛ ፈተና እንደሆነ ገልጸዋል። "በአከፋፋይ ግዙ ይባላል። በአከፋፋይ መግዛት ስትጀምር ደግሞ `እሱ ቆሟል ከዚህ በኋላ ቀጥታ ራሳችሁ ግዙ´ ይባላል። ሕጉ ተመሳሳይ አይደለም። በዚህ በአራት አመት ውስጥ አራት አምስት ጊዜ አልተቀየረም ብለህ ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ። "አንዴ የሲሚንቶ ግብይቱን የሚቆጣጠረው አካል የማዕድን ሚኒስቴር ይሆናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ይሆናል" ሲሉ ይተቻሉ።

"አንድ ሰው ሲሚንቶ ማግኘት የሚችለው በአስረኛ ዙር ተሽከርክሮ ነው። ድሮ ተለምኖ ነው የሚሸጠው። በቂ ፋብሪካዎች አሉ፤ ነገር ግን እያመረቱ አይደለም። ለምን አያመርቱም? ለእኔም ጥያቄ ነው" የሚሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሲሚንቶ አከፋፋይ የግብይት ሒደቱን የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጣቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ገበያው ለገጠመው ቀውስ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ከአቶ አበራ ጋር ይስማማሉ።

"አስመጪውም እዚያ ላይ ገብቷል፤ ላኪውም እዚያ ላይ ገብቷል። ባለሥልጣኑም ገብቷል፤ ብዙ ሰው ገብቶበታል። መጀመሪያ ላይ ሒደቱን ያበላሸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቀጥሎ ንግድ ሚኒስቴር ነው ያበላሸው። ከንግድ ሚኒስቴር ደግሞ ማዕድን ሚኒስቴር ነው ሒደቱን ያበላሸው" በማለት የሲሚንቶ አከፋፋይ ሆነው የሰሩት ነጋዴ በተለይ ሶስቱን ተቋማት ይወቅሳሉ። ለ20 አመታት በአከፋፋይነት የሰሩት ግለሰብ እንደሚሉት ለገበያው መበላሸት ሙስናም ተጽዕኖ አሳድሯል። "አሁን የሲሚንቶ ፋብሪካ የሽያጭ ክፍል ሰራተኛ እና ዘበኛው ሳይቀር ነጋዴ ሆኗል፤ አከፋፋይ ሆኗል። የባለሥልጣን ሚስቶች እና ዘመድ አዝማዶች አከፋፋይ ሆነዋል። ሥርጭቱን ያበላሸው እሱ ነው" የሚል ብርቱ ወቀሳ ያቀርባሉ።

ዶይቼ ቬለ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች በተመለከተ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። የኢትዮጵያ ንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ባለፈው ሣምንት ከ13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 12ቱ የሚያመርቱት ከ50 በመቶ በታች በሆነ አቅማቸው መሆኑን ገልጿል። መሥሪያ ቤቱ እንደሚለው "የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን፣ የመለዋወጫ እጥረት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመሟት" ለገበያ የሚቀርበው ምርት ዝቅተኛ እንዲሆን አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

አቶ አበራ ሉታሮ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የሲሚንቶ አከፋፋይ ያነሷቸው ችግሮች በግብይቱ ውስጥ መኖራቸውን በከፊልም ቢሆን የኢትዮጵያ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ባለፈው ሣምንት አረጋግጠዋል። ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ "ከፍተኛ የሆነ የፋብሪካዎች እና የአከፋፋዮች ትሥሥር አለ። የተወሰኑ የበለጠ ግብይቱን በብቸኝነት የሚይዙበት ሌሎች ደግሞ አከፋፋይም ሆነው ሲሚንቶ ለአመታት የማያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ሲሉ ተደምጠዋል።

Äthiopien Dire Dawa Zementfabrik
በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ ግብይቱን የሚያምሰው የእጥረት እና የዋጋ ጉዳይ መፍትሔ ካልተበጀለት በርካታ የግንባታ ዕቅዶች ከማዘግየት ባሻገር የግሉ ዘርፍ ፈተናን እንደሚፈታተን የዘርፉ ባለሙያዎች ሥጋት ገብቷቸዋል።ምስል Mesay Tekilu/DW

በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ ግብይቱን የሚያምሰው የእጥረት እና የዋጋ ጉዳይ መፍትሔ ካልተበጀለት በርካታ የግንባታ ዕቅዶች ከማዘግየት ባሻገር የግሉ ዘርፍ ፈተናን እንደሚፈታተን የዘርፉ ባለሙያዎች ሥጋት ገብቷቸዋል። ይኸ ሥጋት ከተጫናቸው መካከል አቶ ወርቁ አንዱ ናቸው። "ሲሚንቶ ገዝቶ ሥራ ለመስራትም የሚያስቸግር ነገር አለ። እያንዳንዱ ፕሮጀክት በበጀት ነው የሚተዳደረው። ፋብሪካ እሰራለሁ ያለ አንድ ተቋም ለሲሚንቶ የመደበውን በግማሽ የሚያጣ ከሆነ በጣም የሚቸገርበት ሁኔታ ነው ያለው። አብዛኛው ባለሐብት ደግሞ የተወሰነ ገንዘብ ይይዛል ነገር ግን በብድር ነው ሥራዎች የሚሰራው። ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ምርት ካልገቡ በአምራቹም ላይ በተበዳሪውም ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም" ሲሉ ተናግረዋል።

የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ ለኮስንትራክሽን ኩባንያዎች በግንባታ ዕቃዎች መናር ላይ የታከለ ተግዳሮት ነው። ይኸ ግን አቶ አበራ እንደሚሉት በአገሪቱ ዘርፈ ብዙ የግንባታ ዕቅዶች ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርለት አይደለም። ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የክልል መስተዳድሮች ለያዟቸው የግንባታ ዕቅዶች በሲሚንቶ ግብይቱ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በቀጥታ ከፋብሪካ እንዲገዙ መወሰኑን የኢትዮጵያ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይኸ ግን ችግሩን ለተወሰነ ጊዜ ከማስተንፈስ ባለፈ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል አቶ ወርቁ ጌታሁን ተናግረዋል። አቶ አበራ በበኩላቸው ሲሚንቶ በፋብሪካ ተመርቶ ለተጠቃሚው እስኪደርስ ባለው የግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ተዋንያንን መቀነስ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሆን እምነታቸው ነው።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ