1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጦሩ ተቃውሞውን ይቀላቀል ይኾን?

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2 2011

በሱዳን የተቀጣጠለው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም ሃገራት የሱዳን መንግሥት ተጨባጭ ፖለቲካዊ ለውጥ ያምጣ ሲሉ ጠይቀዋል። የሱዳን ጦር ሰላማዊ ሰልፈኞችን እንዳይጋፈጥ መመሪያ ተላልፏል። እናስ የሱዳኑን የረዥም ዘመን ፕሬዚዳንት ለሥልጣን ያበቃው የሀገሪቱ ጦር ከፕሬዚደንቱ ወይንስ ከሕዝቡ ጎን ይሰለፋል?

https://p.dw.com/p/3GWOI
Sudan Proteste gegen Staatschef Al-Baschir in Khartum
ምስል Getty Images/AFP

«ለሕዝባዊው ጥያቄ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት አኹኑኑ መልስ ሊሰጡ ይገባል»

ላለፉት አራት ወራት በሱዳን የተቀጣጠለው የመንግሥት ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ማክሰኞ እለት ብቻ መዲናይቱ ካርቱም በሚገኘው የሀገሪቱ ጦር እዝ ማዕከል ፊት ለፊት በመቀመጥ ተቃውሞ ያደረጉ ሱዳናውያን ላይ ጦሩ ተኩስ ከፍቶ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።  ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ የተገደሉት ሰዎች ቊጥር እስከ ማክሰኞ ድረስ 15 ተጠግቷል።

በአንድ ወገን ጦሩ ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር እንዳይጋፈጥ ትእዛዝ መተላለፉ ይሰማል። በሌላ ወገን ግድያው እንደቀጠለ ነው።  ያም ኾኖ ጦሩ ከተቃዋሚዎች ጋር ኅብረት መፍጠር መጀመሩን የሚያመላክቱ ዘገባዎች በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭተዋል።  የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኙ፦ ቶቢያስ ሲሞንም ይኽንኑ ነው የሚናገሩት።

«ዘገባዎቹ እውን የሚኾኑ ከኾነ ሰልፈኛውን የሚደበድበው ጦር በእርግጥም ጨዋታ ቀያሪ ሊኾን ይችላል።»

ባለፈው እሁድ ሱዳናውያን በጦሩ እዝ ማዕከል ፊት ለፊት ተገኝተው ፕሬዚዳንት ዖማር ኧል በሽር ከሥልጣናቸው ይውረዱ ሲሉ ከጦሩ ግልጽ ድጋፍ መታየቱ ተዘግቧል። በተለይ የቅዳሜ እለቱ ተቃውሞ በሱዳን ታሪክ ልዩ ሥፍራ አለው። ከ34 ዓመታት በፊት ቅዳሜ፤ መጋቢት 28 ቀን  የያኔው ፕሬዚደንት ጃፋር ኧል ኒሜሪ በሀገሪቱ ጦር ሊወገዱ ተቃውሞ የተቀጣጠለበት ወቅት ነበር። ከ16 ዓመታት በፊት እርሳቸውን በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣኑ ማማ ላይ ያወጣቸው ጦሩ ነበር አውርዶ የከሰከሳቸው። የሱዳን ጦር አንዴ ከመመንግሥት መልሶ ደግሞ ከሕዝቡ ጎን ሲቆም  በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል። የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኙም በዚህ ይስማማሉ።

«ሱዳን ውስጥ በሕዝባዊ አመጽ ለኹለት ጊዜያት መንግሥት ተቀይሯል፤ በ1964 እና 1985። ያኔ ታዲያ በተለይ ተቃዋሚ ሰልፈኛውን ሲደበድቡ የነበሩ ወጣት መኮንኖች መንግሥት ወደ መቀየሩ ለመሸጋገር ቀናትም አልፈጀባቸውም ነበር። እናም አኹን የትኛው የጦሩ ክፍል ከሰልፈኛው ጎን እንደሚቆም ዐናውቅም።»

የሱዳን የፀጥታ ኃይላት ልባቸው ወደየት እንዳደላ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሰኞ እለት አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎችን ለመበተን የሀገሪቱ የደኅንነት አባላት እና ፖሊሶች አስለቃሽ ጢስ ተኩሰዋል። እንደ ዐይን እማኖች ከኾነ ደግሞ ከሰልፈኞቹ ፊት የነበሩ የጸጥታ አስከባሪዎች የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከፍተዋል።

Omar al-Bashir
ተቃውሞ የጠናባቸው የሱዳኑ ፕሬዚደንት ዖማር ኧል በሽርምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ammar

እድሜያቸው በ20 እና በ30ዎቹ መካከል የሚገኙ የሱዳን ወታደሮች ከአንድ ሰው ውጪ ሌላ ይኼ ነው የሚባል ፖለቲከኛ በሥልጣኑ ማማ ላይ ዐይተው አያውቁም። ያ ሰው ሱዳንን ከሦስት ዐሥርተ-ዓመት በላይ የመሩት ፕሬዚዳንት ዖማር ኧል በሽር ናቸው።

ምዕራቡ ዓለም የሱዳን ባለሥልጣናት «ለፖለቲካ ሽግግር ግልጽ እቅዳቸውን ያስቀምጡ» ሲሉ አሳስበዋል። በሱዳን ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ በተጠናከረበት በአኹኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ እና ኖርዌይ «ለሕዝባዊው ጥያቄ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት አኹኑኑ መልስ ሊሰጡ ይገባል» ሲሉ አሳስበዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ነጋሽ መሐመድ