1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን መንግስት ለፍርድ የሚቆመዉ ሄግ ወይስ ዳሬሰላም

ማክሰኞ፣ ጥር 24 1997

የሱዳን መንግስት ዳርፉር ላይ ስላደረሰዉ ጥቃት የተባበሩት መንግስታት ባቀረበዉ ዘገባ መሰረት በስፍራዉ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ከመፈፀም ባሻገር የጅምላ ግድያ አለመፈፀሙን አረጋገጠ። እንደ መንግስታቱ ድርጅት አገላለፅ የሱዳን መንግስት ሄግ በሚገኘዉ አለም አቀፍ የወንጀል ችሎት ይቅረብ የሚለዉን ወሳኔ ይዞ የሰዉ ዘር አጥፍቷል በሚል ወንጀል ለመጠየቅ የሚያስችል በቂ ደጋፊ ተግባር ይጎለዋል።

https://p.dw.com/p/E0kU

ያም ሆነ ይህ ግን ጉዳዩ መታየት ያለበት በአለም አቀፍ የወንጀል ችሎት መሆን አለበት የሚለዉ የተለያዩ አካላት ግፊት ቀጥሏል።
ባለፈዉ ሰሞን የሱዳን መንግስት በአገሪቱ የፈፀማቸዉን አስከፊ ተግባራት በመመርመር በተለይ በዳርፉር በተፈፀመዉ ኢሰብዓዊ ድርጊት ግንባር ቀደም ተጠያቂ በመሆኑ በሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀል በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ይጠየቅ የሚለዉን ሃሳብ የአሜሪካ መንግስት መቃወሙ ይታወሳል።
አምስት አባላት ያሉትና በዋና ፀሃፊዉ በኮፊ አናን አማካኝነት የተቋቋመዉ ይህ አጣሪ ኮሚሽን ዘገባ እንደሚያትተዉ ድርጊቱን በሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈረጅ የሚጎሉት ነገሮች አሉ።
ኮሚሽኑ የሱዳንን መንግስት ኃይሎችንና ሚሊሻዎችን ተጠያቂ ያደረገዉ ማንንም ሳይለይ ለፈፀሙት ጥቃት ማለትም ሲቪሉ ህብረተሰብ ላይ ለፈፀሙት የግድያ፤ የማሰቃየት፤ በግዳጅ ሰዎችን የመሰወር፤ መንደሮችን የማዉደም፤ አስገድዶ የመድፈርና በአገሪቱ ባጠቃላይ የግዳጅ መፈናቀልን ተግባር ነዉ።
ምንም እንኳን እነዚህ ተግባራት የጦር ወንጀል ቢባሉም ዘርን፤ ጎሳን፤ ብሄርን ወይም ሃይማኖትን መነሻ በማድረግ የተፈፀሙ ተግባራት ባለመሆናቸዉ የክሱን ይዘት የሰዉ ዘር ማጥፋት ሊያሰኙት አይችሉም ባይ ነዉ ኮሚሽኑ።
ያም ቢሆን ግን ምናልባት ይህንኑ መንገድ በመጠቀም የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ አንዳንድ ግለሰቦች የሰዉ ዘር የማጥፋት ወንጀል ፈፅመዉ ይሆናል በማለት ዘገባዉ ያብራራና የተፈፀመዉ ወንጀል ይህ ቢሆንም እንኳን ጉዳዩን የሚመለከተዉ የፍትህ አካል ሊያየዉ ይገባል በማለት ያጠቃልላል።
ቀደም ብላ ዋሽንግተን በዳርፉር የተፈፀመዉን ተግባር የሰዉ ዘር የማጥፋት ወንጀል ነዉ በማለት የካርቱም መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት ስታደርግ ነበር።
ሆኖም በአለም ዙሪያ ያሰማራቻቸዉን ዲፕሎማቶቿንና ሰራዊቷን አስመልክቶ ሌላ መዘዝ ይከተላል ብላ በመስጋት ለአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት እዉቅና በመስጠት ጉዳዩ ወደዚያ እንዲያመራ አልፈለገችም።
በምትኩ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የዳርፉር ጉዳይ ታንዛንያ ዉስጥ የሩዋንዳን የሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጣሪዎች ክስ ወደሚያየዉ አለም አቀፍ የወንጀል ችሎት እንዲቀርብ ጥረት እያደረገ ነዉ።
በቅርቡ ዳርፉር ዉስጥ የተቀሰቀሰዉ ግጭት አይነተኛ ምክንያት የካርቱም መንግስት ዳርፉርን ችላ ብሏል በሚል መነሻ አማፅያን ያካሄዱት የተቃዉሞ ተግባር ሲሆን ከመንግስት የተሰጠዉን ምላሽ ተከትሎ ወደ 70,000 የሚጠጉ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
የተባበሩት መንግስታት ኮሚሽን ዘገባ በአፅንኦት የገለፀዉ ችግሩን ለመፍታት የሱዳን መንግስት የወሰደዉ እርምጃ አጥጋቢ አለመሆኑንና የሱዳን የህግ አሰራር ለዚህ የማያመች እስከሆነ ድረስ በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት መታየት እንደሚኖርበት ነዉ።
ኮሚሽኑ አያይዞ በወቅቱ የተፈፀመዉን ኢሰብአዊ ድርጊት እያወቁ ከማስቆም ይልቅ በቸልታ ያለፉ የታወቁ የመንግስት ባለስልጣናትና የጦር ኃይሉ ኮማንደሮችንም ማንነት እንደደረሰበት ገልጿል።
የካርቱም መንግስትም በበኩሉ በዳርፉር የተፈፀመዉ አሰቃቂ ተግባር ከአማፅያን ለተሰነዘረዉ ጥቃት አፀፋ ምላሽ ነዉ ቢልም ኮሚሽኑ ማስተባበዩን ዉድቅ በማድረግ ድርጊቱ የሲቪሉን ህብረተሰብ እንኳን ያለየ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ነዉ ብሎታል።
በተጨማሪም ከመንግስት ኃይሎች ሌላ ከአማፅያኑም ሆነ በስፍራዉ ከሚገኙት የዉጪ ጦር አባላት መካከል ጥቂቱ ሆን ብለዉ በጥፋቱ መሳተፋቸዉን የኮሚሽኑ ዘገባ ይፋ በማድረግ ጉዳዩ አለም አቀፍ ዳኝነት እንደሚያስፈልገዉ አሳይቷል።
የኮሚሽኑን ዘገባም ተከትሎ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ጉዳዩ በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት መታየት አለበት የሚለዉን ሃሳብ እንደሚደግፍ አስታዉቋል።
በመሆኑም የተፈፀመዉ ድርጊት የሰዉ ዘር ማጥፋት ሊባል ቢችልም ባይችልም ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባዉ ይብዛም ይነስ በሰዉ ልጆች ህይወት ላይ ከፍተኛ ወንጀል መፈፀሙ ነዉና አለም አቀፍ ዳኝነት ይፈልጋል።
ምንም እንኳን ሱዳን በቅርቡ ሰላም በአገሪቱ ለማስፈን የስምምነት ዉል ከአማፅያኑ ጋር ቢፈራረምም ዉሉን ተከትሎ የተደረገ ለዉጥ ባለመኖሩ የዳርፉር ጉዳይ ገና አለየለትም።