1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ግኝቱ አፍሪካ የዘመኑ ሰው ዝርያ ምንጭ መሆኑን አጠናክሯል

ረቡዕ፣ መስከረም 24 2010

አሁን ያለውን የሰው ልጅ አመጣጥ ሂደት በዝርዝር ለመገንዘብ ተመራማሪዎች የሚያደርጉት ጥናት በተለያየ ጊዜ የተለያየ ግኝት እያሳየ ነዉ። ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገ ግኝት የዛሬ 42 ዓመት በኢትዮጵያ በኦሞ ሸለቆ የተገኘ ቅሪተ አካል ካመላከተው በተለየ የዘመኑ ሰው ዝርያ እድሜ ከ200 ሺህ ዓመት የላቀ ነው ይላል ፡፡

https://p.dw.com/p/2lDz6
Experten vom Middle Awash Research-Team bei Ausgrabungen in Afar Äthiopien
ምስል DW/A. T. Hahn

የሰው ዘር አመጣጥ አዲስ ግኝት

ባለፈው ሳምንት ለንባብ የበቃው “ሳይንስ” የተሰኘው ዕውቁ የሳይንስ መጽሔት (ጆርናል) በስዊዲን እና ደቡብ አፍሪካ ተመራማሪዎች በጋራ ሲካሄድ የቆየን የምርምር ውጤት አትሟል፡፡የግኝቱ ጨመቅ የዛሬው ዘመን ሰው ዝርያ ዕድሜ ከ260 ሺህ እስከ 350 ሺህ ይገመታል የሚል ነው፡፡ ዜናውን ለዓለም ካጋሩ የዜና ተቋማት አንዱ አሶሴትድ ፕሬስ “እርጅና ተሰማዎት?” ሲል ጠይቋል፡፡ ሮይተርስ በበኩሉ “መልካም የ350 ሺህ ዓመት የልደት በዓል” ሲል የብዙ ሰዎች ጉጉት የሆነውን ረጅም ዕድሜ መኖር ይፋ ከተደረገው ምርምር ውጤት ጋር አሰናስሎታል፡፡ እርስዎ ያን ያህል ባይታደሉ በእርስዎ የዘር ግንድ ያለፉ ሰዎች ግን ከዚያ ሁሉ ዓመት በፊት ነበሩ እንደማለት፡፡ 

Symbolbild Homo Sapiens Schädel eines Menschen
ምስል picture-alliance/dpa/J. Kalaene

ተመራማሪዎቹ ጥናት ያደረጉባቸው እና ለዚህ ድምዳሜ እንዲበቁ ያደረጓቸው ቅሪተ አካላትም ዕድሜያቸው የዋዛ አይደለም፡፡ በደቡብ አፍሪካ ኩዋዙሉ ናታል ጠቅላይ ግዛት ከተገኙት ቅሪተ አካላት የሶስቱ ዕድሜ 2 ሺህ ዓመት ይገመታል፡፡ እነዚህኝዎቹ አድኖ በዪዎች ነበሩ፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ ቅሪተ አካላት ደግሞ ከ300 አሊያም ከ500 ዓመት በፊት በምድር ላይ ይመላለሱ የነበሩ ገበሬዎች ናቸው፡፡ ተመራማሪዎቹ የእነዚህን ቅሪተ አጽሞች ዘረ መል (DNA) በመውሰድ ነበር ጥናታቸውን ሲያካሄዱ የቆዩት፡፡ ከምርምሩ ፊት አውራሪዎች አንዱ የሆኑት የስዊዲኑ ኡፕስላ ዩኒቨርስቲ መምህር ማቲያስ ጃኮብሰን ማብራሪያ አላቸው፡፡ 

“ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት የኖሩ ህዝቦችን አጽም በወስድንበት ጊዜ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ወደ ደቡብ አፍሪካ ከፍ ያለ ፍልሰት እንደነበር ተረድተናል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ የእረኞች ፍልሰት ነበር፡፡ ከምዕራብ አፍሪካ የፈለሱት ደግሞ የብረት ስራ ዘዴዎችን እና ሌሎችንም ይዘው ነው የመጡት፡፡ ይህ በደቡባዊ አፍሪካ የሚኖሩት ላይ በሙሉ ተጽእኖውን አሳርፏል፡፡ ከአዲስ መጤዎቹ ጋር ተዳቅለዋል፡፡ ይህ ማለት ከዚህ ቀደም የነበሩ የቁጥር መላምቶች በሙሉ ዝቅ ያሉ ግምቶች ነበሩ፡፡ በድንጋይ ዘመን ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ይኖር በነበረው ታዳጊ ላይ ከዚህ ቀደም የነበረውን ትንተና እንደገና በመመልከት በአሁኑ የሰው ዘር መካከል ያለውን የመለያየት ጥልቀት ስንፈትሽ ግምቱ 300 ሺህ ዓመት ወደ ኋላ አስጉዞናል፡፡ በአሁኑ የሰው ዘር መካከል ያለው የመለያየት ጥልቀት አገኘን ማለት ማለት የዛሬ ዘመን ሰው የተለወጠው ክፍለ ጊዜ በፊት ነበር ማለት ነው” ይላሉ የኡፕስላ ዩኒቨርስቲው መምህር፡፡

ዶ/ር ብርሃኔ አስፋው የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ አጥኚ ናቸው፡፡ በዘርፉም ላለፉት 37 ዓመታት ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ስለአዲሱ የምርምር ውጤት ግኝት ጠቄያቸው ነበር፡፡ “እነዚህ ሰዎች በእነዚህ ዘረ መል የምንላቸው (DNA) የእያንዳንዳችን ጸባይ፣ መልክ፣ ቅርጽ የሚይዙ፣ የዘር ባህሪያችንን የሚይዙትን ነገሮች ካጠኑ በኋላ ያገኙት ነገር ምንድነው? ሌሎችም ቀደም ብለው እንዳዩት አፍሪካ ያሉት ህዝቦች በተለይ ከኢትዮጵያ እስከ ታንዛንያ ባሉት የህዝቦች ውስጥ የተጠኑት ጥናቶች ቀደም ብለው እንዳመለከቱት ሰፊ የዘረ መል ስፋት ያለበት እና ረጅም ዕድሜ የሚያስቆጥሩት ዘረ መሎች የሚገኙት በእነዚህ አካባቢ ነው ብለው አጥንተው ነበር፡፡ እነርሱ በጣም ውስን በሆኑ፣ ደቡባዊ አፍሪካ ውስጥ ባሉ ብሔረሰቦች ውስጥ የዘረ መል ጥናቶች ካደረጉ በኋላ የእነዚያ የዘረ መሎች ስር በጣም ከሌላው ሁሉ ጥልቀት ያለው ረጅም ጊዜ ሊያስቆጥር የሚችል እንደሆነ አረጋገጡ፡፡ እርሱ በጣም ጥሩ ውጤት ነው” ብለዋል፡፡

Experten vom Middle Awash Research-Team bei Ausgrabungen in Afar Äthiopien
ምስል DW/A. T. Hahn

ዶ/ር ብርሃኔ የምርምር ውጤቱን ጥሩ ነው ያሉት የዘሮችን የአመጣጥ ቅደም ተከተል ለማሳየት መቻሉን አድንቀው ነው፡፡ ሆኖም የዘር ባህሪያትን በሚመለከት በሚደረግ ጥናት “ይሄኛው ዘር ከዚያኛው ቀድሞ በዚህ ዓመት ነው የመጣው” የሚል የዕድሜ ግምት አንድ ሊያሟላው የሚገባ ነገር እንዳለ ያስረዳሉ፡፡ ግምቱ ስዊዲናውያኑ ተመራማሪዎች እንዳደረጉት በመላምት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን አሻሚ ያልሆኑ የዕድሜ መለኪያዎች መንገድ መጠቀም ይገባዋል ይላሉ፡፡ ለዚህም ዕድሜያቸው በዕድሜ መለኪያ ዘዴዎች የተመረመረ ቅሪተ አካላት ያስፈልጋሉ ባይ ናቸው፡፡ 

“አንዱ ካንዱ መቼ ነው እየተለያያ ነው የሚሄደው የሚለውን (order of divergence) ማለት አያቱ፣ ቅድመ አያቱ ከዚያ በኋላ ልጁ፣ የልጅ ልጁ እያለ መቼ እንደተለያየ ቅድመ ተከተላቸውን ለማሳየት ይችላል፡፡ ለዚያ ልዩነት ግን ዕድሜ፣ ቁጥር ለማስቀመጥ ሁልጊዜ ከቅሪተ አካላት ጋር ከሚገኙ ቁጥሮች ነው፡፡ እና እነሱ በሆነ መንገድ ያንን ቁጥር ሲያመለክቱ እነርሱ የመረጡት ቁጥር ‘አሁን ከሰሜን አፍሪካ ከተገኘው ጋራ ይቀራረባል፣ የዛሬ ሶስት መቶ ሺህ ዓመት ሊሆን ይችላል የሚለው ከእኛ ግምት ጋር ሊሄድ ይችላል’ የሚል ነገር ነው እንግዲህ በሳይንስ [መጽሔት] ላይ ታትሞ የወጣው፡፡ እና እንግዲህ ጥሩ መላምት ነው፡፡ ግን ይህ መላምት፤ መላምት እንጂ እውነት አይደለም፡፡ እውነት ሊሆን የሚችለው የሚሆነው ቅሪተ አካል፣ ተጨባጭ መረጃ ስናገኝለት ነው” ይላሉ ኢትዮጵያዊው የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ አጥኚው፡፡ 

ዶ/ር ብርሃኔ የጠቀሱት የሰሜን አፍሪካው ግኝት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ይፋ የተደረገ ነው፡፡ ጀበል ኢራድ ከተሰኘው የሞሮኮ አካባቢ የተገኘ ቅሪተ አካል ላይ ምርምር ያደረጉት አጥኚዎች አሁን በምድር ላይ የሚመላለሰው ሰው ዝርያ ከ300 ሺህ ዓመት በፊት በዚያ ይኖር እንደነበር አረጋግጠናል ብለው ነበር፡፡ ስለ ግኝቱ በወቅቱ ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ብርሃኔ ተመራማሪዎቹ የተጠቀሙበትን የዕድሜ አለካክ ዘዴ ጥያቄ ውስጥ ከትተውት ነበር፡፡ 

Experten vom Middle Awash Research-Team bei Ausgrabungen in Afar Äthiopien
ምስል DW/A. T. Hahn

ተመራማሪዎቹ የተጠቀሙበት ቴርሞሚኔነሰንስ (thermoluminescence) በሰው ዘር ጥናት መስክ ባሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አለማግኘቱን አስረድተው ነበር፡፡ አሁን ይፋ የተደረገው የስዊዲንያኑ ዘዴም ተመሳሳይ ጉድለት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪ የዕድሜ መለኪያ ዘዴ ካልተረጋገጠ በስተቀር ልኬቱ አጠራጣሪ ነው ይላሉ፡፡ ዶ/ር ብርሃኔ ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው ግኝት ግምት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡ 

“ትክክል ነው፡፡ ሁላችንም እንገምታለን፡፡ አሁን እኛ በኢትዮጵያ ያገኘናቸው ቅሪተ አካላት ትልቅ የቅድመ የአሁኑ ዘር መረጃዎች አንደኛው ከደቡብ ኦሞ የተገኘው የኦሞ 1 እና የኦሞ 2 የሚባሉት የአሁን ሰው ዘር ቅሪተ አካላት ናቸው፡፡ እነሱም ዕድሜያቸው 195 ሺህ ዓመት ይደርሳል፡፡ እንግዲህ ወደ 200 ሺህ ዓመት የሚጠጉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የተሟላ ሙሉ አካል፣ ሙሉ ፊቱን እና ቅርጹን የሚያሳየው ያገኘነው ከአፋር ሂርቶ እየተባለ ከሚጠራው ቦታ እኔ እና የእኔ ቡድኖች ያገኘነው ‘ሂርቶማን’ እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ያ ደግሞ 160 ሺህ ዓመት ገደማ ነው ዕድሜ ያለው፡፡ አሁን ይሄ የሚያመለክተው በተጨባጭ ያለን መረጃ ከ160 ሺህ እስከ 200 ሺህ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የአሁኑ የሰው ዘር ለመኖሩ አመላካች ነው፡፡ ይሄ  ደግሞ የእድሜ አለካኩ ዘዴ ምንም የማያጠራጥር ‘ፖታሺየም አርገን’ ወይም ‘አርገን አርገን’ እየተባለ የሚጠራው የዕድሜ መለኪያ ዘዴ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በምንም ዓይነት ያልተደረገ እና ማንም ያልተጠራጠረው እና ሁሉም ዓለም የተቀበለው የዕድሜ መለኪያ ነው ያለው” ሲሉ በኢትዮጵያ በተገኙ ቅሪተ አካላት ላይ ከተደረገ ጥናት ጋር ያነጻጻራሉ፡፡ 

‘አርገን አርገን’ የሚባለውን የዕድሜ መለኪያ ዘዴ የሚጠቀሙ ተመራማሪዎች የጊዜ ርዝማኔውን የሚደርሱበት ከእሳተ ጎሞራ የወጡ የእሳት ወለድ ብናኞችን በመመርመር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቅሪተ አካላት የተገኙባቸው መካነ ቅርሶች የስምጥ ሸለቆን ተከትለው ያሉ በመሆናቸው በእሳተ ጎመራ የወጡ ማዕድናትን አብሮ ለማግኘት ቀላል ያደርገዋል፡፡ ከእነዚህ ማዕድናት መካከል አንዱ የሆነው ፖታሺየም ከጊዜ በኋላ ወደ አርገን ይቀየራል፡፡ ተመራማሪዎቹ አንድ የፖታሺየም ማዕድን ከስንት ዓመታት በኋላ ወደ አርገን እንደሚቀየር በምርምር ስለሚያውቁ በዚያ ላይ ተመስርተው የቅሪተ አካላቱን ዕድሜ ግምት ያስቀምጣሉ፡፡ 

Max Planck Institut - Homo sapiens älter als gedacht
ምስል picture-alliance/MPI EVA Leipzig/Philipp Gunz

ዶ/ር ብርሃኔ ባለፈው ግንቦት ሞሮኮ ዉስጥ ተገኘ የተባለውም ሆነ አሁን ስዊዲናውያኑ በደቡብ አፍሪካ ደረስንበት ያሉት ግኝት አፍሪካ በሰው ዘር አመጣጥ ላይ ያላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን መመስከራቸው በጎ ጎን እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የስዊዲኑ ጃኮብሰንም ግኝታቸው ይህንኑ የሚያጠናክር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የሰው ዘር መገኛ በተለያዩ ጥናቶች ከሚጠቀሰው ከምስራቅ አፍሪካም የሰፋ እንደሆነ ያመላክታል ባይ ናቸው፡፡

“የእኛ ግኝት የሚለው 300 ሺህ ዓመት ወደ ኋላ ስንመለስ ቀደም ሲል የነበሩ ክስተቶች ከዘመናዊው ሰው እድገት ጋር ሳይገናኙ አይቀርም ነው፡፡ ይህ በምስራቅ አፍሪካ አልተከናወነም አይልም፡፡ ነገር ግን በምስራቅም አፍሪካ እንደሆነው ሁሉ በሰሜን አፍሪካም ተከስቶ ሊሆን ይችላል ነው፡፡ አሊያም በደቡብ አፍሪካ፡፡ ምናልባትም በአፍሪካ አህጉር ባሉ በተለያዩ ክፍሎች ባሉ በእነዚህ ሶስት ቦታዎች በተመሳሳይ ጊዜ በፍልሰት እና መቀየጥ ተከስቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግኝታችን የሚለው ምስራቅ አፍሪካን ብቻ ከማሰብ ይልቅ በመላው አፍሪካ አህጉር ውስጥ ሰፊ ቦታን መመልከት አለብን ነው” ይላሉ ጃኮብሰን፡፡  ዶ/ር ብርሃኔም ከስዊዲኑ ተመራማሪ ጋር የሚመሳሰል ሀሳብ ያንጸባርቃሉ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ