1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰርቢያ ምክር ቤት ዉሳኔና የስሬብሬኒሳ ጭፍጨፋ

ሰኞ፣ መጋቢት 27 2002

የስሬብሬኒሳን ሕዝብ ከጥቃት እንደሚከላከሉት ቃል የገቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር አዛዥ ጄኔራል ፊሊፕሊ ሞርሊዮ-ጭፍጨፋዉ በሚፈፀምበት መሐል ሕዝቡን ከማዳን ይልቅ-የሰርብ ጦር ያገታቸዉን ፈረንሳዉያንን ለማስለቀቅ ከጨፍጫፊዉ ጦር አዛዥ ከራትኮ ምላዲች ጋር ይደራደሩ ነበር

https://p.dw.com/p/MneQ
ከስሬብሬኒሳ ጅምላ ቀብሮች-አንዱምስል DW / Sekulic


05 04 10

የቤልግሬድ ፖለቲከኞች የቀድሞ ጦራቸዉ የፈፀመዉን ጭፍጨፋ ባስራ-አምስተኛ አመታቸዉ ዘንድሮ አምነዉ-የተጨፍጫፊ ዘመድ-ወዳጆችን ባለፈዉ ሳምንት ይቅርታ መጠየቃቸዉ አንዳድ የብራስልስ፣ ኒዮርክ ፖለቲከኞች እንደመሠከሩት ቤልግሬዶች እዉነቱን ለመቀበል የመፈለጋቸዉ የሩቅ ደሞም ትንሽ-ግን ጥሩ ምልክት ነዉ።ጥሩዉ ምልክት ከሩቅ-ትንሽነቱ ጋር በገሚስነቱ መደብዘዙ፣የተጨፍጫፊ ወገኖችን ቂም ለማለዘብ፣ የገዳይ-ሟቾች ዉልዶችን ለማስማማት፣ ሰርቢያን ከአለም፣ሠርቦችን-ከራሳቸዉ ለማስታራቅ-የተስፋ ነቁጣ-እንኳን አለማሳየቱ እንጂ-ቅጭቱ።የሰርቢያ ምክር ቤት ዉሳኔ-መነሻችን፣ የስሬብሬኒሳ ጭፍጨፋ ማጠቀሻ፣የዉሳኔዉ እንድምታ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

«በዚሕ አዋጅ መሠረት እኛ ያልነዉ አዎ፥ ስሬብሬኒሳ ላይ ዘግናኝ ወንጀል ተፈፅሟል ነዉ።በዚሕ አዋጅ የንፁሐን ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል-ነዉ ያልነዉ። ለዚሕ ደግሞ ይቅርታ ነዉ-የጠየቅ ነዉ።»

ናዳ-ኮሉንዲዚች።በጣም ለዘብተኛ የሚባለዉ የሰርቢያ ዴምክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴ ናቸዉ።የሰርቢያ ፕሬዝዳንት ቦሪስ ታዲችም በምክር ቤታቸዉ ዉሳኔ ተደስተዋል።ለብዙ ጊዜ ብዙ የታገልኩለት ተፈፀመ-አይነት አሉ በቀደም።
«1990ዎቹን ከጀርበችን ትተን ማለፍ እንፈልጋለን።እናም የሌሎች ሥቃይ-ሰቆቃ ሊሰማን ይገባል። ለዚሕም ነዉ ዛሬ ሳይሆን ከዛሬ በፊት ብዙ ቀደም ብዬ የስሬብሬኒሳ (ግድያ) ጉዳይ ዉሳኔ እንዲሰጥበት አበክሬ የጣርኩት።ምክንያቱም ዉሳኔዉ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠዉ፥ ዲሞክራሲያዊ ደንብ ነዉና፥ ዉሳኔዉ የወገንን ሰለቦች ብቻ ሳይሆን የባዕዳንን ሰለቦችንም ማሰብና ማስታወሰን የሚያካትት በመሆኑ የማሕበረሰብ ደንብ ነዉ።»

የሰርብ ፖለቲከኞች ያዉም ለዘብተኛ የሚባሉት አስራ-አምስት አመት የፈጁት ከዚሕ ለመድረስ ነበር።አስራ-አምስት አመት ተጠብቀዉም፥ ያዉም ለዘብተኛ የሚባሉት የጭፍጨፋዉን ትክክለኛ ገፅታ በሚገባዉ ቋንቋ አልገለጡትም።ጭፍጨፋዉን እንደ ጥፋት የቆጠሩ-ይቅርታ የጠየቁትም ከሁለት መቶ ሐምሳዉ የምክር ቤት እንደራሴዎች አንድ-መቶ ሃያ-ሰባቱ ብቻ ናቸዉ።

አሳፋሪ-አሉት የስሬብሬንስታ-እናቶች ማሕበር ሊቀመንበር ሙኒራ ዙባዚች፥-

«አሳፋሪ ነዉ።የሰርቢያ ምክር ቤት አባላት ከአስራ-አምስት አመት በሕዋላም ጅምላ ግድያዉን ወንጀል ከማለት ባለፍ «ታሪኩን) በትክክል መፃፍ አልቻሉም።»

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ከመዉረሩ ከአስራ-አንድ አመት በፊት በሐያሉ አለም ግፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የክሮኤሽ እና የቦሲኒያ ሕዝብን ከሰርቦች ጥቃት የሚከላከል ጦር አስፍሮ ነበር።1992-ዘመኑ በሙሉ እንደጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።አለም አቀፉ ጦር ከመስፈሩ ከጥቂት ወራት በፊት ጥቅምት 1991 የሳራዬቮ ፖለቲከኞች ቦሲኒያ-ሔርዞ ጎቪኒያ ሪፐብሊክ ከቤልግሬድ ማዕከላዊ አገዛዝ ተግንጥላ ነፃ መንግሥት መመስርቷን አወጁ።

Bosnien gedenkt der Opfer des Srebrenica Massaker Gräber trauernde Frau
መታሰቢያዉምስል picture-alliance/ dpa

የአዉሮጳ ማሕበረሰብ ይባል የነበረዉ የዛሬዉ የአዉሮጳ ሕብረት የሳርዬቮ ፖለቲከኞችን አዋጅ ተቀብሎ ለቦስኒያ እና ሔርሶ ጎቪና ሪፐብሊክ የነፃ ሐገርነት እዉቅና ለመስጠት ከመንፈቅ በላይ አልጠበቀም።ለአዲሲቱን አዉሮጳዊት ሪፐብሊክ የነፃ መንግሥትነት እዉቅና ሰጠ።ሚያዚያ ስድስት 1992።ነገ-አስራ ስምንት አመቱ።

የአዉሮጳ ማሕበረሰብ ዉሳኔ በተነገረ በማግስቱ ዩናዩትድ ስቴትስም የአትላንቲክ ወዲሕ ማዶ ወዳጆችዋን ፈለግ ተከተለች።የብራስልስ-ዋሽንግተን መሪዎች ለስሎቬኒያ፥ ለክሮኤሽያ እንዳደረጉት ሁሉ ለቦሲያንያ-ሄርሶ ጎቢያናም እዉቅና ለመስጠት የተጣደፉት ቀዝቃዛዉን ጦርነት በአስተማማኝ ድል ለመወጣት ካላቸዉ ፍላጎትና-ጉጉት መሆኑ ብዙ አላነጋገረም።

የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ወዳጆች የቦሲኒያ ሔርሶ ጎቪናን ነፃ ሐገርነት ሲደግፉ የቤልግሬድ መሪዎች እጃቸዉን አጣጥፈዉ እንደማይጠብቁ በርግጥ አልዘነጉትም ነበር።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት UNPROFOR ያለዉን ጦር እንዲያዘምት ግፊት ያደረጉትም የቤልግሬዶችን አፀፋ ስለሚገምቱ ነበር። ምዕራባዉያኑ ሐገራት መሪዎች ከድርድር ዉይይት ይልቅ በሐይል፥ ከእኩልነት ይበልጥ-በማን አሕሎኝነት የሚታበዩትን የስሎቮዳን ሜሎሶቪች፥ የራዶቫን ካራጂችን፥የራትኮ ምላጂችንና እና የብጤዎቻቸዉን አለማ-እቅድ በቅጡ አዉቀዉታል ማለት ግን ያሳስታል።

ፈረንሳዊዉ የዩኒፕሮፎር ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል ፊሊፕ ሞርሊዮ መጋቢት 1993 ስሬበሬኒሳ ሲገቡ የሰርቦች ጦር ከተማይቱን ከአካባቢዉ ጋር የሚያገናኘዉን መስመሮች በሙሉ ዘግቶ፥ከአካባቢዉ የተሰደደዉም ነባሩም ነዋሪ ሕዝብ በእሕል ዉሐ እጦት፥ በመብራት-መጠለያ ችግር እየተሰቃየ ነበር።ጄኔራሉ የስሬብሬኒሳ ሕዝብን ከጥቃት እንደሚከላከሉ ቃል በገቡ በሰወስተኛዉ ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቁጥር 819 ያለዉን ዉሳኔዉን አሳለፈ።

ዉሳኔዉ ከተማይቱ ከማንኛዉን ተፋላሚ ሐይል ነፃ እንድትሆን ይደነግጋል።የምክር ቤቱን ዉሳኔ የጄኔራሉን ቃል የሚያስከብረዉ፥ የሚሰቃየዉን ሕዝብ ከከፋ ጥቃት ይከላከላል የተባለዉም ባካባቢዉ የሰፈረዉ የኔዘርላንድስ ጦር ነበር።የአለም አቀፉ ድርጅት ዉሳኔ፥ የአለም አቀፉ ጦር አዛዦች ቃል-የጦሩ እዚያ መስፈርም በሶሎቫዳን ሜሎሶቪች ሙሉ ድጋፍ ሪፐብሊካ ሰርፕስካ የሚል ሐገር ላወጁት ለዶክተር ራዶቫን ካራጂች፥ ለስርፕስካ ጦር-አዛዥ ጄኔራል ለራድኮ ሚላዲች እና ለተባባሪዎቻቸዉ ከቁብ የሚገባ አልነበረም።

ካራጂች-እስከዚያ ጊዜ ድረስ በየአካባቢዉ የሚያስፈፅሙትን መርሐቸዉን መመሪያ ቁጥር ሰባት ባሉት አዋጅ ለጦራቸዉ በሰጡት ትዕዛዝ ስሬብሬኒሳ ሊደግሞት ግልፅ-አደረጉ።

«በቅጡ በተጠናና በታቀደ የጥቃት ዘመቻ የስሬብሬኒሳ ነዋሪ ጨርሶ ለመዳን ወይም በሕወይት ለመትረፍ ምንም አይነት ተስፋ የማይኖረዉ ሁኔታ መፍጠር (አለባችሁ።)» ይላል የትዕዛዙ አንድ አንቀፅ።መጋቢት 1995።የሪፑብሊካ ሰርፕስካ ጦር-አዛዥ ጄኔራል ራድኮ ምላዲች የፕሬዝዳንታቸዉን ትዕዛዝ ለማስፈፀም-አላመነቱም።የአይን ምስክሮች እንደሚሉት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሴቶች፥ ከባል፥ ከአባት ወንድሞቻቸዉ እየተነጠሉ ይደፈሩ፥ ይጋዙ፥ ይታገሩ ጀመር።ወንዱ በመደዳ ይረሸን ያዘ።ሐምሌ-ላይ ትልቁ ተፈፀመ።በትንሽ ግምት ስምንት-ሺሕ ሙስሊሞች ተጨፈጨፉ።1995

የሰርቢያ ምክር ቤት ትልቁ ጭፍጨፋ በተፈፀመ በአስራ-አምስተኛ አመቱ በቀደም ያሳለፈዉን ዉሳኔ ያልተቀበሉት አዉሮጳ ሕብረት የምክር ቤት እንደራሴ ዶሪክ ፓክ-እንደሚሉት የጭፍጨፋዉ ሐቅነት መካድ የለበትም።

«የስሬብሬኒሳዉ የዘር-ማጥፋት ሐቅ ነዉ።ከሌላ ጋር መቀየጥ-ማመሳሰልም አይቻልም።የዘር-ማጥፋት መፈፀሙ እዉነት ነዉ።ይሕ ደግሞ በስሙ-ነዉ መሰየም ያለበት። አሁን በተደረገበት ሁኔታ ከሆነ ግን ይቅርታዉን ማመን አትችልም።»

ሌላም ሐቅ ነበር።የስሬብሬኒሳን ሕዝብ ከጥቃት እንደሚከላከሉት ቃል የገቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር አዛዥ ጄኔራል ፊሊፕሊ ሞርሊዮ-ጭፍጨፋዉ በሚፈፀምበት መሐል ሕዝቡን ከማዳን ይልቅ-የሰርብ ጦር ያገታቸዉን ፈረንሳዉያንን ለማስለቀቅ ከጨፍጫፊዉ ጦር አዛዥ ከራትኮ ምላዲች ጋር ይደራደሩ ነበር።የኔዘርላንዱ ጦር አዛዥ ሌፍትናንት ኮሎኔል ቶማስ ካርሜንስ ከሚላዲች ጋር ብርጭቆ ያጋጬ ነበር።

የባግዳድ ገዢዎች፣ በጀምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ አምራችነት፣ በአለም አቀፍ ሕግ ጣሺነት፣ በሰላማዊ ሰዎች ገዳይነት ከመወንጀላቸዉ፣ ኢራቅ ከመደብደቧ ከብዙ አመታት በፊት የቤልግሬድ ገዢዎች በሕዝብ ጨፍጫፊነት፣ በአለም ሕግ አፍራሽነት ተወንጅለዉ የሚገዟት ሐገርም ተደብድባ ነበር።

ጠንካራዉ ጦር ባግዳድን ለመቆጣጠር፣ ሳዳም ሁሴንን ከቤተ-መንግሥት አሽቀንጥሮ-ጉርጓድ ለመዶል አንድ ወር በቂዉ ነበር።ኢራቅ ከመወረሯ ከአራት አመት በፊት ሰርቢያ ላይ የዘመተዉ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት (ኔቶ) ጦርም የሰርቢያን ጦር ለማሽመድመድ የወር እድሜ አልጠየቀዉም ነበር።ቤልግሬድን ግን እንደ ባግዳድ አልተቆጣጠራም።ከሳዳም ሁሴን በፊት የተወነጀሉ፣የተወገዙትን ስሎቮዳን ሜሎሶቪች አልታሰሩም።

ሳዳም ሁሴይንን ከተሸሸጉበት ጉርጓድ አዉጥቶ-ባግዳድ አደባባይ ለማንጠልጠል ሰወስት አመት ከበቂ በላይ ነበር።የኔቶ ጦር ሰርቢያ ከዘመተበት ስሎቮዳን ሜሎሶቪችን ከቤልግሬድ ቤተ-መንግሥት አዉጥቶ ከዘሔግ እስር ቤት ለመዶል ሰወት አመት ፈጅቷል። በሜሎሶቪች ሙሉ ድጋፍ የስሬብሬኒሳዉን ጭፍጨፋን ያዘዙት ራዶቫን ካራጂች የተያዙት ጭፍጨፋዉ በተፈፀመ በአስራ-ሰወስተኛዉ አመት ሐቻምና ነዉ።የጨፍጫፊዉ ጦር አዛዥ ጄኔራል ራትኮ ምላዲች ዛሬም አልተያዙ።አስራ አምስት አመት።ምናልባት እንዳለቆቻቸዉ ቤልግሬድ መሽገዉ ይሆን-ይሆናል።

አንድ-አለም።አንድ ሕግ።ተመሳሳይ ወንጀል።ተቃራኒ-አፈፃፀም።ቤልግሬድ።ባግዳድ።የአንዷ አለም-አንድ ሕግ የቤልግሬድ-ባግዳድ የአፈፃፀም ትልቅ ልዩነት መሠረት-ምክንያት ብዙ አነጋግሯል።ያነጋግራልም።

የአዉሮጳ ሕብረት የምክር ቤት እንደራሴ ዶሪስ ፓክ እንደሚያምኑት ግን የሰርቢያ ምክር ቤት ዉሳኔ-በሰርቦች ጥፋት ይሁን በአለም ዘዋሪዎች ስሕተት አፈፃፀሙ የተዛባዉን የአለምን ፍትሕ ለማረቅ የሚበጅ አይደለም። የምክር ቤቱ የተፈፀመዉን ወንጀል በስሙ ሰይሞት ቢሆን ኖሮ-የሰርቢያ ሕዝብ በስሙ የተፈፀመበትን ወንጀል ባወቀዉ ነበር።

«ይሕ ዉሳኔ አለማዉን ስቷል።እኔ እንደሚመስለኝ ይሕ ዉሳኔ ለሰርቢያ ሕዝብ በሥሙ ስሎቮዳን ሜሌሶቪች፥ ሚላዲች የሰሩበትን የሚያመለክት (መሆን ነበረበት)የሰርቢያ ሕዝብ አይደለም የፈፀመዉ ግን በሰርብ ሕዝብ ስም ነዉ የተፈፀመዉ።ሥለዚሕ ዉሳኔዉ ለሰርብ ሕዝብ የተሳሳተ መልዕክት ነዉ-የሚያስተላልፈዉ።ዉሳኔዉ የተፈፀመዉን በትክክለኛ ሥሙ የዘር ማጥፋት ብሎት ቢሆን ኖሮ ሕዝቡ በኛ ስም የተፈፀመ ነዉ ብሎ ባለፈዉ ጊዜ ሥለተፈፀመዉ አዕምሮዉን ክፍት አድርጎ እንዲያስብ ይረዳ ነበር።»

Flash-Galerie Karadzic und Mladic - Schlüsselfiguren für Srebrenica Bosnien
ካራጂችና ምላዲችምስል picture-alliance/ dpa

በርግጥም ዉሳኔዉ የሰርቢያ ፖለቲከኞችን ከሕዝባቸዉ፥ ሰርቦችን ከአጎራባቾቻቸዉ ጋር የሚያስታርቅ አይነት አይደለም።የስሬብሬኒሳ ሰለቦች ወገኖችን ቂም ለመፋቅም አልፈየደም።

በሶቬት ሕብረት፥ በዩጎዝላቪያ መፈረካከስ ምዕራቡ አለም የቀዝቃዛዉን ጦርነት በአስተማማኝ ድል አጠናቅቆ ይሆናል።ለቀዝቃዛዉ ጦርነት ንረት በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ሚሊዮኖች መርገፍ-ሚሊዮኖች መሰቃየት እንደነበረባቸዉ ሁሉ ለቀዝቃዘዉ ጦርነት ፍፃሜም-አዉሮጳ ብቻ፥ የቦስኒያ፥የክሮኤሽያ፥የሰርቢያ የሌሎችም ሕዝብ ጭዳ መሆኑ ነዉ አሳዛኙ ፍፃሜ።አለም ዘንድሮም እንደ ጥንቱ ፍትሕ በጡንቻ እብጠት የሚተረጎምባት መሆንዋ ነዉ-ሰቀቀኑ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Dw,Agenturen,Wikipedia
Negash Mohammed