1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን አፍሪቃ ስደተኞችና የላምፓዱዛ ነዋሪዎች

ረቡዕ፣ መጋቢት 21 2003

የማግሬብ አገራትን የናጠው ህዝባዊ አመፅ በተለይ ደግሞ የሊቢያው ጦርነት የኢጣልያዋን ደሴት ላምፔዱዛንና የአካባቢውን ከተሞች በስደተኞች ማጨናነቁን ቀጥሏል ።

https://p.dw.com/p/RDzc
ላምፔዱዛ የደረሱ ሰደተኞችምስል picture alliance / dpa
ሰሞኑን እንኳን ከሊቢያው ጦርነት የሸሹ ወደ 800 መቶ የሚጠጉ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የኤርትራና የሶማሊያ ስደተኞች ላምፔዱዛ ገብተው በተለያዩ አጎራባች ከተሞች ወደ ሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ሰፈሮች ተወስደዋል ። የላምፔዱዛ ነዋሪዎችም ከቱኒዝያው አመፅ ወዲህ ወደ ደሴቲቱ የሚጎርፉ የመንግስት ድጋፍ የማያገኙ ስደተኞችን አቅማቸው በፈቀደው መጠን በሰብአዊነት በመርዳት ላይ ናቸው ። የሊቢያውን ጦርነት በመሸሽ በአደገኛ የጀልባ ጉዞ ተሳክቶላቸው በቅርቡ ኢጣልያ የገቡት ስደተኞች እንደሚሉት ሊቢያ ድንበር ላይ አሁን እንደ ቀድሞው ቁጥጥር የለም ።
Flash-Galerie Italien Lampedusa Flüchtlinge
ስደተኞች ጭና ላምፔዱዛ የደረሰች ጀልባምስል picture-alliance/dpa
በዚህም ምክንያት በህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ነፍሳቸውን ለማዳን ከሊቢያ እየወጡ ነው ። የብዙዎቹ ተስፋም የላምፔዱዛ ደሴት ናት ። ሊቢያ ከ ሶስት ዓመት በፊት ከኢጣልያ ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት ድንበሯን ስትዘጋ ወደ ደሴቲቱ የሚሰደዱት ቁጥር በ 94 በመቶ ቀንሶ የላምፔዱዛ የስደተኞች መጠለያም ተዘግቶ ነበር ። በቱኒዝያ አንድ ያለው የማግሬብ አገራት ህዝባዊ ንቅናቄ ወደ ግብፅ ብሎም ወደ ሊቢያ ሲሸጋገር ግን ላምፔዱዛ ቀድሞ ከነበረችበት ወደ ባሰ ሁኔታ ተሸጋገረች ። በአሁኑ ሰዓት ደሴቲቱ የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ከ 5,486 በላይ ነው ። 20 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ካላት ከላምፔዱዛ ነዋሪዎች በላይ ነው ቁጥራቸው ።
Italien Lampedusa Flüchtlinge Libyen Tunesien
ምስል dapd
ያም ሆኖ ነዋሪቿ ለነፍሳቸው አድረው የኢጣልያ መንግስት ለስደተኞቹ ማድረግ የተሳነውን እያከናወኑ ነው ። ስደተኞችን ከሚረዱትበበጎ ፈቃደኞች አንዱ ፓውሎ ዲ ቤኔዴቶ ናቸው ። ሶሶት ስደተኞችን አስጠግተዋል ። ግቢያቸውው ውስጥ ስደተኞች እንዲረዱም ፈቅደዋል ። « በእግዚአብሔር አምናለሁ ። ለዚህም ነው ይህን የማደርገው ። ክርስቲያን ሁሉ ይህን ማድረግ ይችላል ። ጥቂት ፍራሾችን መስጠት እችላለሁ ። ከግቢየ መናፈሻም የተወሰነውን ክፍል እንዲጠለሉበት ፈቅጃለሁ ። ንፁህ ነው ። ለህፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድንኳን መትከል ይቻላል ። » መንግስት ከአቅሜ በላይ ሆኗል ሲል ዞር ብሎ የማያያቸውን ስደተኞች ነዋሪዎች በቤተ ክርስቲያን በትምህርት ቤትና በልዩ ልዩ አዳራሾችም አስጠልለው እየታደጉዋቸው ነው ።
Italien Lampedusa Flüchtlinge Libyen Tunesien
የስደተኞች መጠለያምስል picture alliance / dpa
የአካባቢው ሰበካ ጉባኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በራሱ ማዕከል ውስጥ አስጠግቷል ። ቪካር ዶን ኣልዶ ራይና እንዳስረዱት ከበጎ ፈቃደኞች አልባሳትም በእርዳታ ይሰበስባሉ ። «ሰዎቹ እጅግ በጣም ተባባሪዎች ናቸው ። በእውነቱ ያልተጠበቀ ልገሳ ነው ያደረጉት ። በቅርቡ ነው ልብስ መሰብሰብ የጀመርነው ። ከአሁን በኃላ ለሚመጡት በተለይም መጠለያ አጥተው ውጭ ለሚያድሩት ልብስ መስጠት እንችላለን ። » እንደ ቪካር የስደተኞቹ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉንም እንደሚፈልጉት መርዳት አልቻሉም ። የሚመለከታቸው አካላት በአካል ወደ ስፍራ መጥተው ችግሩን በራሳቸው ቢገነዘቡ ነው የተሻለ ይሆናል እንደርሳቸው « ምናልባት እዚህ ስለ ሚሆነው መወሰን የሚችሉት ላምፔዱዛ ውስጥ የተወሰኑ ሰዓታት መቆየት ይኖርባቸዋል ። ያን ካደረጉ እዚህ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ በቀላሉ መረዳት በቻሉ ነበር ። » ስደተኞች በብዛት ይጎርፉብኛል የሚል ስጋት ያደረበት የኢጣልያ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ እርዳታ እየጠየቀ ነው ። የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ አገራቸው የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ እንደሚልኩ ዝተዋል ። ከቱኒዝያው ንቅናቄ አንስቶ እስካሁን ላምፔዱያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከአስራ ስምንት ሺህ በላይ ነው ። ሂሩት መለሰ ተክሌ የኋላ