1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 1995

አራት ሚልዮን የርዋንዳ ዜጎች በዛሬው ዕለት አዲስ ፕሬዚደንት ይመርጣሉ። ርዋንዳ ከቤልዢክ ቅኝ አገዛዝ ነፃነትዋን ካገኝች ወዲህ ነፃ ምርጫ ስታካሂድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው። በዚሁ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ወቅታዊው ርዕሰ ብሔር ፖል ካጋሜ ከፍተኛ የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው ይገመታል። እአአ በ 1994 ዓም በሁቱና በቱትሲ ጎሣ መካከል በተከሰተው ውዝግብ አንድ ሚልዮን የቱትሲ ጎሣ እና ለዘብተኛ ሑቱዎች በተጨፈጨፉባት ርዋንዳ ውስጥ የሚደረገው የመጀመሪያ ምርጫ

https://p.dw.com/p/E0lV

ምን ይመስላል?


የመምረጥ መብት ያላቸው አራቱ ሚልዮን ርዋንዳውያን ዛሬ አዲስ ፕሬዚደንት፡ የፊታችን መስከረም አሥራ ዘጠኝ ደግሞ አዲስ ምክር ቤት በሚመርጡበት ሂደት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ገሀድ ያደርጋሉ። ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ አራት ዕጩዎች በተወዳዳሪነት ቀርበዋል። ይሁንና፡ በዚሁ ምርጫ ላይ በርካታ ተወዳዳሪዎች በዕጩነት መቅረባቸው ብቻ ሳይሆን፡ በርዋንዳ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከተፈፀመውና በአፍሪቃ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ ከሆነው ደም አፋሳሽ ጭፍጨፋ በኋላ ሀገሪቱ ለምርጫ መብቃትዋ ነው እንደ ትልቅ ርምጃ የተቆጠረው።

ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እአአ ሐምሌ 1994 ዓም የሀገሪቱን አመራር ከተረከቡ ወዲህ የጎሣ ግጭት ያዳቀቃትን ርዋንዳ ብሔራዊው አንድነት ለማስገኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከአሰቃቂው የጎሣ ጭፍጨፋ ትዝታ ለመላቀቅ ብርቱ ሙከራ በያዘችው ርዋንዳ ውስጥ የጎሣ ልዩነትን ለማጉላት የሚደረግ ሙከራ እንደ ከባድ የፖለቲካ ጥፋት የሚታይ ወንጀል ሆኖ ይታያል። በመሆኑም፡ የጎሣ ፖለቲካን የሚያንፀባርቅ ማንኛውም ፖሊሲ ከርዋንዳ ፖለቲካ መወገድ እንዳለበትም ነው አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት የሀገሪቱ መሪዎች የሚናገሩት።

ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እርቀ ሰላም ለማስገኘትም ሲሉ አንድ የአስቸኳይ ጊዜ መንግሥት ማቋቋማቸው የሚታወቅ ነው፤ በዚሁ መንግሥት ውስጥ የሚጠቃለሉት ሕጋዊ ፓርቲዎች ግን አባላት እንዲኖሩዋቸው መቀስቀስም ሆነ ስብሰባ ማዘጋጀት አይፈቀድላቸውም። ብዙ የተለያዩ ሂደቶች ከተከናወኑ፡ ለምሳሌም፡ አዲሱ የርዋንዳ ሕገ መንግሥት ከወጣ በኋላ ነው የአሁኑ ፕሬዚደናዊ ምርጫ ሊደረግ የበቃው። እንደሚታወሰው፡ የርዋንዳን አንድነት ያጎላው አዲሱ ሕገ መንግሥት ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ በርዋንዳ በተካሄደው ሬፈረንደም ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶዋል። በዚሁ ፌፈረንደም ላይ ከተሳተፈው ሰማንያ ሰባት ከመቶ መራጭ ሕዝብ መካከል ዘጠና ሦስት ከመቶው ሕገ መንግሥቱን ደግፎ ድምፁን መስጠቱ የርዋንዳ ሕዝብ የጎሣ ጭፍጨፋ ርዕዮትን ለማስወገድ ያለውን ፅኑ ፍላጎት በግልፅ አሳይቶዋል።

የርዋንዳን አንድነት ለመጠበቅ የሚደረገው ሙከራ ግን የሕዝቡን የአስተሳሰብ ነፃነት እና በመንግሥቱ አንፃር ሒስ የመሰንዘር መብትን ለማፈኛ ሰበብ እንዳይሆን ብዙ አሥግቶዋል። ርዋንዳ ውስጥ ሐቀኛ የተቃውሞ ፓርቲ የለም። የፓርቲዎች ፖለቲካዊ አሠራርም፡ ፓርቲዎች በሕግ እንዲታገዱ ሀሳብ ሊያቀርብ በሚችለው የፖለቲካ መድረክ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግበታል። ርዋንዳ ውስጥ ከፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የርዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ጎን ሌላው ዋነኛ ፓርቲ የሑቱ ጎሣ ተፅዕኖ የበዛበት፡ በምሕፃሩ ኤም ዲ ኤር የሚሰኘው የሬፑብሊካውያኑ እንቅስቃሴ ነው፤ ይሁንና፡ ኤም ዲ ኤር አሁን በሕግ ታግዶዋል። ከዚህ ሌላ ደግሞ ዋነኛው የፖል ካጋሜ ተቀናቃኝ የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ፎስተ ቱዋጊራሙንጉ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዘመቻ ላይ ብርቱ እክል ነበር የተደቀነባቸው። ይህ ሁሉ ገዢው ወገን የርዋንዳን አንድነት ለመጠበቅ የጎላውን አሠራር የተቀናቃኞቹን አንደበት ለማፈን ይጠቀምበታል የሚለውን ወቀሳ አሰንዝሮበታል።

ባጠቃላይ ካለእርሳቸው አመራር ርዋንዳ ምሥቅልቅሉ ሁኔታ ላይ እንደምትወድቅ፡ እንዲሁም በሀገሪቱ ፖለቲካዊውን እና ኤኮኖሚያዊው መረጋጋት እንደማይኖር ወቅታዊው ርዕሰ ብሔር ፖል ካጋሜ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዘመቻ ወቅት ያጎሉት መልዕክት በብዙዎቹ መራጮች ዘንድ ሰሚ ጆሮ ያገኘ መስሎ ነው የሚታየው። ፖል ካጋሜ በዋነኛው ተቀናቃኛቸው ፎስተ ትዋጊራሙንጉ አንፃር የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል፤ በተለይም፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ትዋጊራሙንጉ በወሳኞቹ ስምንት የርዋንዳ መልሶ ግንባታ ዓመታት ውስጥ በግዞት በቤልዢክ የተቀመጡበት ድርጊት ባንድ በኩል፡ የተቃውሞው ወገን የተከፋፈለበት ሁኔታ በሌላ በኩል የፕሬዚደንት ካጋሜን መልሶ መመረጥ ዕድል ያማረ አስመስሎታል።