1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ 20ኛ መታሰቢያ ዓመት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 30 2006

ርዋንዳ ከ20 ዓመት በፊት በሀገሩ አክራሪ ሁቱዎች ለሦስት ወራት ባካሄዱት የጅምላ ጭፍጨፋ የተገደሉትን ከ800,000 የሚበልጡ የቱትስ እና የለዘብተኛ ሁቱ ጎሣ አባላትን፣ ከጭፍጨፋው የተረፉ ብዙዎች እና በርካታ የውጭ እንግዶች በተገኙበት በመዲናይቱ ኪጋሊ በሚገኘው አማሆሮ ስቴድየም በተካሄደው ልዩ ሥነ ሥርዓት አስባ ዋለች።

https://p.dw.com/p/1BcGu
ምስል Reuters

አንድ ሳምንት የሚቆየው የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት በይፋ የተጀመረው ከ100 ቀናት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የለኮሱት ችቦ በመላይቱ ሀገር መዘዋወር በጀመረበት ጊዜ ሲሆን፣ አሁን ችቦው በኪጋሊ ለጭፍጨፋው ሰለባዎች ወደተሰራው እና ወደ 250,000 የሚጠጉ ሰለባዎች አፅም ወዳረፈበት ማዕከል ደርሶዋል። የተመድ በዚሁ ከ20 ዓመት በፊት በተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ አንፃር ያኔ አስፈላጊውን ርምጃ ባለመውሰዱ አሁንም ትልቅ ሀፍረት እንደሚሰማው የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ኪ ሙን በመታሰቢያው ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል። የተመድ በርዋንዳ አሰማርቶት የነበረውን ጦሩን በዚያን ጊዜ ማስወጣቱ የሚታወስ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ፣ ፈረንሳይ እና ቤልጅየም በጅምላው ጭፍጨፋ ዝግጅት ላይ እና ባንዳንዱ ግድያም ላይ ተሳታፊ ነበሩ በሚል የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለአንድ የፈረንሳይ ሳምንታዊ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደዲስ ወቀሳ በመሰንዘራቸው እና በርዋንዳ የፈረንሳይ አምባሳደር በመታሰቢያው ሥነ ሥርዓት እንዳይሳተፉ በተደረገበት ምክንያት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማቲካዊ ንትርክ ተፈጥሮዋል።b#

Ruanda Genozid Gedenken 07.04.2014 Ban Ki Moon
ምስል Reuters

በርዋንዳ የጎሣው ጭፍጨፋ የተጀመረው የሁቱ ተወላጅ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚደንት ጁቨናይል ሀቢያሪማና ይጓዙበት የነበረው አይሮፕላን እአአ ሚያዝያ ስድስት : 1994 ዓም መዲናዋ ኪጋሊ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ላይ በሮኬት ተመቶ ሲወድቅ በሞቱበት ጊዜ ነበር። ለዚሁ የሮኬት ጥቃት በዚያን ጊዜ የቱትስ ዓማፅያን ቡድን መሪ የነበሩት የወቅቱ የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜን እና የቅርብ ረዳቶቻቸውን ተጠያቂ ናቸው ሲሉ አንድ የፈረንሳይ ዳኛ ቢከሱም፣ ካጋሜ ጥቃቱ አክራሪ ሁቱዎች ውሁዳኑን ቱትሲዎች ለመጨፍጨፍ አስቀድመው ያዘጋጁትን ዕቅድ ተግባራዊ ይሆናቸው ዘንድ ያካሄዱት ስራ ነው በሚል ክሱን አጣጥለውታል። ጥቃቱን ይኸኛው ወይም ያኛው ወገን ከጣለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከመዲናይቱ የተጀመረው ጭፍጨፋ መላይቱን ሀገር አዳርሶ ለተከተሉት ሦስት ወራት ቀጥሎዋል። በአፍሪቃ ለተካሄደው ትልቁ የጎሣ ጭፍጨፋ ግን የፕሬዚደንት ሀቢያሪማን ሞት ብቸኛው ምክንያት አይደለም። በሁለቱ ጎሣዎች መካከል ውጥረቱ ከቅኝ አገዛዙ ዘመን ጀምሮ ያለ ነው።

Symbolbild Völkermord in Ruanda
የጅምላው ጭፍጨፋ ሰለባዎችምስል picture-alliance/dpa

በመዲናይቱ ኪጋሊ በሚገኝ አንድ ኮረብታማ ቦታ የጊሶዚ መታሰቢያ ማዕከል ይታያል። ማዕከሉ እአአ በ 2004 ዓም ከተከፈተ ወዲህ ማንኛውም ርዋንዳን የሚጎበኝ ሰው፣ ቱሪስት ሆነ ርዕሰ ብሔር ይህንኑ መታሰቢያ ማዕከል ሳይጎበኝ አይሄድም። በዚሁ ማዕከል 259,000 የጎሣው ጭፍጨፋ ሰለባዎች አፅም ይገኛል።

በማዕከሉ የሚታዩት ፎቶዎች፣ ልብሶች እና የግል ቁሳቁሶች የጎሣው ጭፍጨፋ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ በተፈፀመው አስከፊ የግድያ ተግባር ሕይወታቸውን ያጡትን ሰለባዎችን ያስታውሳል።

የሕፃናት ክፍል በሚባለው ክፍል ውስጥ ትላልቅ ፎቶዎች ተሰቅለዋል። ከነዚሁ ፎቶዎች መካከል አንዱ ፈግግታ የሚታይባት የቆንጆዋ ፍራንሲን ፎቶ ነው። ፎቶው ፍራንሲን ደስታ የተመላበት የልጅነት ጊዜ ማሳለፏን ይጠቁማል። የጊሶዚ መታሰቢያ ማዕከል የጅምላው ጭፍጨፋን ግፉ የሚያስታውሰውን የማዕከሉን ክፍል የሚያስተዳድሩት የኤጊስ ተቋም ባልደረባ ኢቬት ዣላድ ስለ ፍራንሲን ሲያስታውሱ፣

Genozid-Gedenkstätte Gisozi
የጊሶዚ ማዕከልምስል picture-alliance/dpa

« የጎሣው ጭፍጨፋ በተካሄደበት ጊዜ ፍራንሲን የ12 ዓመት ልጅ ነበረች። መዋኘት ትወድ ነበር። እንቁላል እና የድንች ጥብስ መብላት፣ ወተት እና ፋንታ መጠጣትም ትወድ ነበር። የቅርብ ጓደኛዋ እህቷ ክሎዴት ነበረች። በቆንጨራ ነው የተገደለችው። »

ርዋንዳ ውስጥ የጎሣው ጭፍጨፋ በተካሄደባቸው ሦስት ወራት በጣም ብዙ አስከሬን በየመንገዱ ተትረፍርፎ ይታይ ነበር። በዚያን ጊዜ በሀገሪቱ ሥልጣኑን ይዞ የነበረው በፕሬዚደንት ሀቢያሪማና የተመራው መንግሥት ውሁዳኑን የቱትሲ ጎሣ አባላትን የማጥፋት ዓለማ ይዞ ከመነሳቱ ጎን ፣ የቱትሲ ጎሣ አባላትን እንዲያጠፉ ብዙኃኑን የሁቱ ጎሣ አባላት ቀስቅሶዋል። ከ800, 000 የሚበልጥ ሕዝብ የተገደለበት የጅምላው ጭፍጨፋ ፣ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ በዚህ አንፃር አንድም ርምጃ ሳይወስድ እስከ እአአ ሰኔ አራት ፣ 1994 ዓም ነበር የቀጠለው። እንደ ኢቬት ዣላድ ገለጻ፣ የጊሶዚ መታሰቢያ ማዕከል በጎሣ ጭፍጨፋ ለተገደሉት ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉት ሰዎች በያመቱ ልዩ ክብር በመስጠት አስቦት ይውላል።

20. Jahrestag des Völkermordes in Ruanda Überlebender D’Artagnan Habintwali
ዳታኞ ሀቢንትዋሊምስል DW/A. Le Touzé

« አንዳንዴ ቁጥሩ የጎሣ ጭፍጨፋ በትክክል ምን መሆኑን መረዳትን አዳጋች ያደርግብናል። ይህን ለመረዳት አንድ ሰው ከጎሣው ጭፍጨፋ ከተረፈ ሰው ጋ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ይኖርበታል። 100 ውን ቀን በፍርሀት ተውጦ እና በረሀብ ተሰቃይቶ እንዴት እንዳሳለፈው ደቂቃ በደቂቃ እንዲያስረዳ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። መኖሪያ ቡቱ በእሳት ጋይቶ እና ተዘርፎ፣ ቤተሰቡም በጠቅላላ ተገድሎ ማግኘት ማለት ምን እንደሆን እንዲያብራራ ጊዜ መስጠት ይገባል። የጎሣ ጭፍጨፋ ማለት ይህ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሰው የገጠመው ነው። »

ዳርታኞ ሀቢንትዋሊ ከተረፉት መካከል አንዱ ነው። የጅምላው ጭፍጨፋ በደቡባዊ ርዋንዳ በምትገኘው የትውልድ ከተማው ቡታሬ ሲካሄድ የአምስት ዓመት ሕፃን ነበር። ሕፃኑ በዚያን ጊዜ ያሳለፈው ተሞክሮ ከአዕምሮው የሚጠፋ አይደለም።

« ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን ሲያቃጥሉ፣ ሰው ሲገድሉ አይቻለሁ። ይህንን ሁኔታ መርሳቱ በጣም አዳጋች ነው። በሰላም ለመኖር ብትሞክርም እንኳን አተችልም። እነዚህ መጥፎ ሥዕሎች አሁንም አሉ።

Niederlassung des internationalen Straftgerichtshofs für Ruanda ICTR in Kigali
የአሩሻ ፍርድ ቤትምስል DW/A. Le Touzé

የርዋንዳ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ረጅም መንገድ ተጉዞዋል። ፕሬዚደንት ካጋሜ የሚመሩት የርዋንዳ መንግሥት በመጀመሪያ የወሰደው ርምጃ በሕዝቡ መታወቂያ ሰነድ ላይ የግለሰቡን ጎሣ የሚጠይቀውን ጥያቄ መሰረዝ ነው። ሕዝቡ በጋራ ለህብረተሰቡ የሚጠቅም አገልግሎት የሚያበረክትበትን በሀ,ገሩ ቋንቋ « ኡሙጋንዳ » የሚለውን አሰራርም እንደገና አስተዋውቋል። ለጅምላው ጭፍጨፋ ተጠያቂ ተብለው የተጠረጠሩትን ለፍርድ ማቅረብ ይቻልም ዘንድ እአአ በ1994 ዓም በጎረቤት ታንዛያ፣ የአሩሻ ከተማ ወንጀሉን የሚመለከት አንድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተቋቁሞዋል። ግን ፣ ብዙዎቹ ወንጀለኞች ወደ ውጭ ሀገር በሸሹበት እና ማስረጃዎችንም ማግኘት አዳጋች በሆነበት ድርጊት የተነሳ ትልቅ እንቅፋት ተደቅኖበት እንደነበር የአሩሻው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተጠሪ ኢኖሰንስ ካማንዚ የፍርድ ቤቱን ስራ አርኪ ሆኖ አግኝተውታል።

Ruanda Gacaca Gericht
ጋቻቻ ባህላዊ ፍርድ ቤትምስል CC--NC-BY-elisa finocchiaro

« የጅምላው ጭፍጨፋ በተዘጋጀበት ድርጊት የተሳተፉት ብዙዎቹ የመንግሥት ሚንስትሮች ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የጅምላው ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ጠንክረው የተሳተፉ በርካታ የጦር መኮንኖች እና ወታደሮች ፣ ሚሊሺያዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች እና የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮችም ጭምር በሕግ ተጠይቀዋል። »

ፍርድ ቤቱ የመጨረሻውን የክስ ጉዳይ እአአ በ2013 ዓም የዘጋ ሲሆን፣ እአአ እስከ 2015 አጋማሽ ድረስ የይግባኝ ማመልከቻዎችን ብቻ ይመለከታል። በፍርድ ቤቱ ክስ ከተመሠረተባቸው 65 የርዋንዳ ዜጎች መካከል በ38 ላይ ብቻ ረጅም የእስራት ቅጣት በመበየኑ ከኪጋሊ ብርቱ ወቀሳ ተፈራርቆበታል።

በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ስራ መጓተት እና አለመርካት የተነሳ የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እአአ በ2001 በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁቱ እና በቱትሲ ጎሣዎች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ « ጋቻቻ » የተባሉትን 12,000 ባህላዊ ፍርድ ቤቶች አቋቋሙ። እነዚህ ፍርድ ቤቶች እአአ ከ2005 እስከ 2012 ዓም በሕይወት የተረፉት የጅምላው ጭፍጨፋ ሰለባዎች የከሰሱዋቸውን ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጉ ተከሳሾችን ጉዳይ አድምጦ፣ ከነዚሁ መካከል ከግማሽ የሚበልጡትን አንድም በእስራት ቀጥተዋል ወይም የማህበራዊ ስራ እንዲሰሩ አዘዋል። የርዋንዳ መንግሥትም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የሀገሩን ምጣኔ ህብት ይዞታን እና የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እየተከተለው ባላው ፖሊሲ አማካኝነት በቱትሲ እና በሁቱ ጎሣዎች መካከል የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ሂደት ዘላቂ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ጀምሮ እየተንቀሳቀሰ ነው።

አን ለቱዜ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ