1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ የመረጃ አቀራረብ ነፃነት እና ፈተናዉ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4 2007

በምሥራቅ አፍሪቃዊትዋ ሀገር በርዋንዳ የፕሬስ ሕግጋትች ነጻ ሆነዉ ቢቀመጡም፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ጋዜጠኞች በነጻነት መሥራትና መፃፍ እንዳልቻሉ ለጋዜጠኞች የሚሟገቱ ድርጅቶች ዘግበዋል።

https://p.dw.com/p/1E3UQ
ምስል Getty Images/AFP/Marco Longari

ከምሥራቅ አፍሪቃገራት መካከል ለዘብተኛ የፕሬስ ሕግ ያላት ርዋንዳ መሆንዋ ይነገራል። ይሁንና፣ ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚሟገተው በምሕፃሩ « ጄይ» የሚባለው ድርጅት እንዳስታወቀው፣ የርዋንዳ ጋዜጠኞች እንደ አንዳንዶቹ የጎረቤት ሀገራት አቻዎቻቸው ሙያቸውን በነፃነት ማከናወን አይችሉም።

በርዋንዳ 800,000 የቱትሲ እና ለዘብተኛ የሁቱ ጎሣ አባላት ከተጨፈጨፉ 20 ዓመታት በኋላ የሀገሪቱ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ተረጋግቶዋል። ይሁንና፣ ለዚሁ መረጋጋት ብዙ መሥዋዕትነት ነው የተከፈለው። ብዙ ጋዜጠኞች ስራቸውን እንደሚጋባው እንዳያከናውኑ እክል ሲያጋጥማቸው ይታያል። ምንም እንኳን የርዋንዳ ሕገ-መንግሥት ነፃ የፕሬስ እና የመረጃ አቀራረብ ነፃነትን ቢፈቅድም ሂስ አዘል ዘገባ አዘውትሮ እየታፈነ ለሕዝብ እንዳይደርስ መደረጉን ኒው ዮርክ የሚገኘው ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚሟገተው በምሕፃሩ « ጄይ» የሚባለው ድርጅት ያካሄደው ጥናት ውጤት አመልክቶዋል። ደቡብ አፍሪቃዊው የአስተሳሰብ ነፃነት ተቋም እና የጆሀንስበርግ የዊትዎተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ክፍል ኃላፊ አንቶን ሀርበር የጥናታቸውን ውጤት ይፋ ያወጡት 25 ከሚበልጡ የርዋንዳ ጋዜጠኞች፣ አሳታሚ ድርጅቶች እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ካነጋገሩ በኋላ ነው። ሀርበር ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፣ ሂስ የታከለበት ዘገባ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች አዘውትሮ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የማከላከል ተግባር እና እክል ይደርስባቸዋል፣ ለፖሊስ የዘፈቀደ ምርመራ ይጋለጣሉ ወይም ማንነታቸው ከማይታወቅ ግለሰቦች ዛቻ ይደርስባቸዋል።

Symbolbild Pressefreiheit in Ruanda - Radio 10 erstes privates Radio in Ruanda
ምስል Getty Images/AFP/Gianluigi Guercia

« ያነጋገርኩዋቸው ጋዜጠኞች በጠቅላላ ስራዎቻቸው ያስቀጣሉ አያስቀጡም በሚል በራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራሰልፍ ሴንሰርሽፕ») ያደረጉ ይመስለኛል፤ ባያምኑበትም። ስለአነጋጋሪ ጉዳዮች መዘገብ ይፈራሉ። ለብዙዎቹ የኅልውና ጥያቄ ነውና። ምክንያቱም ግለ ቅድመ ምርመራ ካላደረጉ ክትትል ሊያጋጥማቸው ወይም ድርጅታቸው ሊዘጋ ወይም ለስደት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ይሰጋሉ። »

እንደ መንግሥታዊ ያልሆነው የርዋንዳ መገናኛ ብዙኃን ኮሚሽን ሊቀመንበር ፍሬድ ሙቩንዪ ገለጻ፣ መቼ ምን ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በማያውቁት የርዋንዳ ጋዜጠኞች ዘንድ የሚያቀርቡዋቸው ዘገባዎች ያስከስሳሉ አያስከስሱም በሚል የሚያካሂዱት የግል ቅድመ ምርመራ በጣም የተለመደ አሰራር እየሆነ መጥቶዋል።

የመገናኛ ብዙኃንን ጉዳይ የሚከታተለው የመንግሥት መስሪያ ቤት ከአራት ዓመት በፊት ጋዜጠኞች ስለመንግሥቱ ተግባራት መረጃ እንደልብ እንደማያገኙ እና « ኃላፊነት የታከለበት ጋዜጠኝነት » በሚል ሰበብም በስራቸው ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ያቀረበበትን ዘገባ ካወጣ በኋላ ርዋንዳ የምትከተለውን የመገናኛ ብዙኃን አሰራርዋን እንደምታለዘብ እና እንደምታፍታታ የሚል ተስፋ ተፈንጥቆ ነበር። እርግጥ፣ መንግሥት ለአስተሳሰብ ነፃነት መቆሙን አስታውቋል፣ ይሁን እንጂ፣ መንግሥት የማይመቸውን አስተሳሰብ ለማፈን ሙከራውን እንደቀጠለ በመግለጽ መሻሻያ እንዲደረግ ዘገባው ሀሳብ አቅርቦዋል። ግን፣ በግልህ የፕሬስ ነፃነት እንዲኖር ከተፈለገ የፖለቲካው ባህል ሊቀየር እንደሚገባ ዘገባው ማመልከቱን ሀርበር ያስታውሳሉ።

« የፕሬስ ነጻነትን ለማፈን ወደኋላ የማይሉ የመንግሥቱ አካላት መኖራቸው ይታወቃል። በተለይ ጋዜጠኞችን የሚከታተሉት እና የሚያስፈራሩት የሀገሪቱ ጦር እና የፀጥታ ኃይሉ የመገናኛ ብዙኃን በነፃ በገለልተኝነት እና ሂሳዊ ሆነው እንዲሰሩእንዲሰሩ አይፈልጉም። »

Paul Kagame Präsident Ruanda
ምስል picture-alliance/dpa

ርዋንዳ በአፍሪቃ ጋዜጠኞች በደል ሲደርስባቸው ወይም እክል ሲያጋጥማቸው አቤት የሚሉበት መስሪያ ቤታ ያቋቋመች አስራ አንደኛዋ ሀገር ስትሆን፣ ለጋዜጠኞች መረጃ የማያቀርቡ የመንግሥት ሰራተኞች በህግ ሊቀጡ እንደሚችሉ ሀገሪቱ ያወጣቻቸው አዲሶቹ ሕጎች ያስታውቃሉ። ይሁንና፣ በሀገሪቱ የሚሰራባቸው በርካት ዕገዳዎች እነዚህ ሕጎች ተገባራዊ እንዳይሆኑ አከላክለዋል፣ ለምሳሌ፣ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የአመራር ስልት ወይም የርዋንዳ ጦር በምሥራቅ ኮንጎ በቀጠለው ደም አፋሳሽ ውዝግብ ውስጥ እጁ አለበት ስለመባሉ ጉዳይ መዘገብ ወይም የፀጥታ ኃይላትን፣ የመንግሥት ሰራተኞችን መንቀፍ ለእስር ሊዳርግ እንደሚችል እና ጋዜጠኞች መንግሥት ፈፀማቸው የሚባሉ ስህተቶችን የሚያጋልጡበት ምርመራ ማካሄድ ወይም ሂስ አዘል ዘገባ ማቅረብ እንዳላስቻላቸው ሀርበር አመልክተዋል። ይህ በተለይ ሂስ ከመሰንዘር ወደኋላ በማይሉ ጋዜጠኞች ላይ ለሚያርፈው ጠንካራ ክትትል ምክንያት ነው።

« ጋዜጠኞች ለምርመራ ይወሰዳሉ፣ እንዲሁም፣ የአካል ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችልም ዛቻ ይሰነዘርባቸዋል ነው የሚባለው። እና ይህ በጋዜጠኞች ላያ ያለማቋረጥ የቀጠለው ክትትል ትልቅ ስጋት ደቅኖዋል። »

20 ዓመት በፊት 800 የቱትሲ እና የለዘብተኛ ሁቱ ጎሣ አባላት ሞትን ያሰከተለው ጭፍጨፋ በተካሄደባት ርዋንዳ በሕዝቡ መካከል ክፍፍል ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ጎሣን፣ ሀይማኖትን፣ ቋንቋን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ዘገባ ማቅረብም እንደሚያሳስር በሕግ ተጠቅሶዋል። ካጋሜ መንግሥታቸው የሚከተለው ጥጥሩ የመገናኛ ብዙኃን ሕግ የሀገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ እና ካሁን ቀደም የታየውን ዓይነቱን አስከፊ የጎሣ ጭፍጨፋ እንዳይደገም ለማከላከል አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል። የፖሊሲ ህቡዕ ዓላማው የማይመቸውን ሂስ ለማፈን መሆኑን ነው፤ ሀርበር በጥናታቸው ያመለከቱት።

 

« መንግሥት በሚቀርብበት ሂስ እና ተቃውሞ አንፃር ቁጥጥሩን በተለያየ ደረጃ አጠናክሮዋል። በተለይ ከምርጫ በፊት የተቃውሞ ቡድኖችን ሲጨቁኑ እና መሪዎቹንም ሲያስር ታይቶዋል። ምንም እንኳን መንግሥቱ በዴሞክራሲ መንገድ ቢመረጥም፣ እስካሁን በተቃውሞ ቡድኖች አኳያ ያሳየው ትዕግሥት በጣም ንዑስ ነው»

አንዳንድ የርዋንዳ ጋዜጠኞችም ይህንኑ አስተሳሰብ እንደ ራሳቸው በመቀበል፣ ለሚያቀርቡት ዘገባ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ደቡብ አፍሪቃዊው ሀርበር ገልጸዋል።

« የርዋንዳ መንግሥት ጥላቻ እና ክፍፍል የሚቀሰቅሱ ዘገባዎችን ለማከላከል የተከተለውን አሰራር መረዳት ይቻላል። ይሁንና፣ ግልጹንና ነፃ ውይይት ቢፈቅድ ጤናማ ዴሞክራሲ መፍጠር ይችላል ብየ አስባለሁ።

ርዋንዳ በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ላይ ስላሳረፈችው ጨቋኝ ተፅዕኖ ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚሟገተው በምሕፃሩ « ጄይ» የሚባለው ድርጅት በየጊዜው ለሚያቀርበው ክስ እና ሀርበርም በጥናታቸው ላመለከቱት በጋዜጠኞች ስለሚገጥማቸው እክል የርዋንዳ መንግሥት መልስ ለመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ የርዋንዳ መንግሥት አመራርን የሚገመግመው ቦርድ ወቀሳው ሀሰት እና መሠረተ ቢስ መሆኑን አስታውቋል። 

አርያም ተክሌ / ካትሪን ማታይ