1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ ሑቱዎችን የዳኘው ፍርድ ቤት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2008

በሰሜናዊ ታንዛኒያ በትንሿ አቧራማ የአሩሻ ከተማ የተሰየመው ችሎት ተዘጋ። ዳኞች እና አቃብያነ ህግጋት ለ21 አመታት የርዋንዳ የዘር ፍጅትን ቁስል ያደመጡባት አነስተኛ ቢሮ ብትዘጋም ጉዳዩ ግን ሙሉ በሙሉ አላለቀም።

https://p.dw.com/p/1HXpf
Ruanda Internationaler Gerichtshof für den Völkermord
ምስል picture-alliance/dpa/L. Lee Beck

የሩዋንዳ ሑቱዎችን የዳኘው ፍርድ ቤት

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ባቋቋመው የርዋንዳ የዘር ፍጅት ተመልካች ፍርድ ቤት የበርካታ ዘግናኝ ወንጀሎች አፈጻጸም ተደምጧል። ከዘር ፍጅቱ አራት አመታት በኋላ የቀድሞውን ከንቲባ ጄን ፓል አካይሱን በጅምላ ግድያ እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል መፈጸምን ጨምሮ በዘጠኝ ክሶች ተጠያቂ በማድረግ ነበር ፍርድ ቤቱ ስራውን የጀመረው። ከዚያ የዘር ፍጅቱ ቀንደኛ ተዋናዮች ተከተሉ። የቀድሞው የርዋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን ካምባንዳ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በጅምላ ግድያ የተከሰሱ የመጀመሪያው የመንግስት መሪ ሆኑ። በፍርድ ቤቱ ከተከሰሱ 93 ግለሰቦች መካከል ፖለቲከኞች፤የንግድ ሰዎች፤ከፍተኛ የጦር ሰራዊት መኮንኖች፤የመንግስት ባለስልጣናት፤የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና የእምነት መሪዎች ጭምር ይገኙበታል። በ5,800የችሎት ቀኖች ከ3,000በላይ ምስክሮች ከፍርድ ቤቱ ቀርበው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ፍጅቱ

በጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም. ጥቂት የርዋንዳ ፖለቲከኞች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ የዘር ጭፍጨፋን እንደ አማራጭ መረጡ። የአገሪቱን ሐብት እና ስልጣን ተጠቅመው ዘር እና አመለካከትን ያማከለ ፍጅት አቀነቀኑ። ብዙኃኑ ሑቱዎች በአናሳዎቹ ቱትሲዎች ላይ ዘመቱ። በጎርጎሮሳዊው ሚያዝያ 6 1994 ዓ.ም. የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ጁቨናል ሐቢያሪማና ይጓዙበት የነበረው አውሮፕላን ከኪጋሊ ሰማይ ላይ ተመቶ ሁሉም መንገደኞች ሲያልቁ ነበር ሁሉም ነገር ወደ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ያመራው። ፕሬዝዳንቱ ከተገደሉበት ቀን ጀምሮ ባሉት አንድ መቶ ቀናት ውስጥ ከ500,000 እስከ 800,000 የሚደርሱ ሰዎች ማለቃቸው ይነገመታል። ከሩዋንዳ ቱትሲዎች ሶስት አራተኛው አለቁ። ለዘብተኛ ሑቱዎችም የግድያው ሰለባ ናቸው። ዓለም አቀፉን የፖለቲካ መድረክ የተቆጣጠሩት ፈረንሳይ፤ዩናይትድ ስቴትስ፤ቤልጅየም እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፈየዱት አንዳች ነገር አልነበረም። ሁሉም በዚያ ዘመን በርዋንዳ ላይ ያረበበውን ፍጅት ተረድቶ ለማስጠንቀቅ አልፈቀዱም። የዘር ፍጅቱ ሲቀሰቀስም ጥቂት ሰራተኞቻቸውን እና የንጹሃን ዜጎችን ህይወት መታደግ ይችሉ የነበሩ ወታደሮቻቸውን አሸሹ። ርዋንዳ ከዚያ በኋላ እንደቀድሞው አልሆነችም።

Genozid-Gedenkstätte Gisozi
ምስል picture-alliance/dpa

ፍርድ ቤቱ

መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገው የርዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ተመልካች ፍርድ ቤት የመጨረሻውን ይግባኝ ከሰማ በኋላ ባለፈው ሳምንት ተዘግቷል። ፍርድ ቤቱ በጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ላይ በተጫወቱት ሚና የእድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው የነበሩት የቀድሞ የሴቶች ሚኒስትር ፓውሊን ኒያራማሱሁኮ ያቀረቡትን ይግባኝ ማዳመጥ የመጨረሻ ስራው ነበር። ችሎቱ ከጎርጎሮሳዊው 1997 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙትን ኒያራማሱሁኮ ፍርድ ወደ 47 አመታት ዝቅ አድርጓል። ከሁለት አስርት አመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየው ፍርድ ቤት የሌሎች ተከሳሾችን እሥራት ጊዜ በመቀነስ የመጨረሻ ሥራውን አከናውኗል።

የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ የርዋንዳ ባለስልጣናትንና የዘር ጭፍጨፋው ቀንደኛ ተዋናዮችን ከዓለም አቀፍ የፍትህ መድረክ ለማቅረብ ያቀደው ፍርድ ቤት ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት መቋቋም መንገድ እንደከፈተ ይነገራል። በሒውማን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ ፍትህ ተሟጋች ክፍል ኃላፊዋ ማቲዮሊሊ ዜልትነር ፍርድ ቤቱ ቅጥ አልባ ግፍ ሲፈጸም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ መቀየሩን ያስረዳሉ።

Ruanda Völkermord 1994 Flüchtlinge
ምስል Getty Images/AFP/P. Guyot

«አሁን በሮቹን የዘጋው ፍርድ ቤት እጅግ ጠቃሚ ተቋም ነበር።የርዋንዳ የዘር ፍጅት ተመልካች ፍርድ ቤት እንደ ርዋንዳው ከፍተኛ ግፍ ሲፈጸም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።»

ከፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አቃብያነ ህግጋት መካከል አንዱ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ያዕቆብ ሐይለማርያም ፍርድ ቤቱ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ይናገራሉ።«ለርዋንዳም ሆነ ለሌላው የአፍሪቃ አገራት ሰውን ጨፍጭፎ፤ ሰውን በዘሩ፣በሐይማኖቱ ወይም በቋንቋው ምክንያት እንደ ልብ አፈናቅሎ ተንሰራፍቶ መኖር አይቻልም የሚል ማስጠንቀቂያ ይህ ፍርድ ቤት ሰጥቷል።» የሚሉት ዶ/ር ያቆብ ከዚያ በኋላ በአህጉሪቱ መሰል ወንጀሎች መቀነሳቸውን አስረድተዋል።

በጭፍጨፋው እጃቸው አለበት ከተባሉ ተከሳሾች መካከል 80 በመቶ ያክሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ከችሎት ቀርበዋል። ከ93 ተከሳሾች 61 ጥፋተኛ ሲባሉ 14 ደግሞ በነጻ ተለቀዋል። ብዙዎች ፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣቱን ይናገራል። የፍርድ ቤቱ አቃቤ-ህግ ባቡካር ዲያሎ የፍርድ ቤቱ መዘጋት ሲቃረብ «ክስ ከቀረበባቸው መካከል ዘጠኝ ሰዎች ገና በቁጥጥር ሥር አልዋሉም። በእነዚህ ጉዳዮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ሊተባበሩ ይገባል።»በማለት ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ትችቶቹ

የርዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ተመልካች ፍርድ ቤት ላለፉት 21 አመታት ከ2 ቢሊዮን ዶላር ወይም 1.8 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ የተደረገበት ውድ ተቋም እንደሆነም ይተቻል። በአንድ ወቅት ፍርድ ቤቱ እስከ 1,200ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን በአቅም ማነስ፤የሙያ ጉድለት እና ሙስና ይወቀስም ነበር።

Bildergalerie Genozid in Ruanda Juli 1994 RPF erobern Kigali
ምስል Alexander Joe/AFP/GettyImages

ፍርድ ቤቱ ነብስ ማጥፋትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች የሚጠረጠሩ የቀድሞ የቱትሲ አማጽያን የዛሬ የሩዋንዳ ባለስልጣናትን አለመዳኘቱ ሌላው ትልቁ ጉድለቱ መሆኑን በሒውማን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ ፍትህ ተሟጋች ክፍል ኃላፊዋ ማቲዮሊሊ ዜልትነር ይናገራሉ።

«ፍርድ ቤቱ በሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (Rwandan Patriotic Front) ከተፈጸሙ ወንጀሎች መካከል አንዳቸውንም አልተመለከተም። ግንባሩ በአሁኑ ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ የሚመራ አማፂ ቡድን ነበር። ግንባሩ የ1994ቱን ጭፍጨፋ ካስቆመ በኋላ እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ ነው። »

ዶ/ር ያዕቆብ በፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ የሚመራው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የዘር ፍጅቱን ለማስቆም በወሰደው እርምጃ በርካታ ወንጀሎች ሳይፈጸሙ እንዳልቀረ ይናገራሉ። ይሁንና «የተባበሩት መንግስታት ይህን ፍርድ ቤት ሲያቋቁም የርዋንዳ አርበኞች ግንባር ድርጊትን እንድንመረምር ሳይሆን ሑቱዎች ኢንተርሃሙዌይ በተባለው አማካኝነት እና በፓርቲው አማካኝነት የተፈጸሙ ወንጀሎች ብቻ እንድንመረምር ብቻ ነበር የታዘዝንው።» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ ታኅሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በይፋ ቢዘጋም በዘር ጭፍጨፋው ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች የፍርድ ሂደት ግን ይቀጥላል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በርዋንዳ ፍጅት ቁልፍ ሚና የተጫወቱ እና እስካሁን ከችሎት ያልቆሙ ግለሰቦች ታድነው ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል ሲሉ ይወተውታሉ። ተጠርጣሪዎቹ ከጭፍጨፋው ማብቃት በኋላ ርዋንዳን ጥለው በመጥፋታቸው ተመሳሳይ ችሎቶች ፈረንሳይ፤ጀርመን፤ቤልጅየም፤ፊንላንድ እና ካናዳን በመሳሰሉ ሶስተኛ አገሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል። አሁንም በወንጀል ተጠርጥረው ለፍርድ ያልቀረቡ ጥቂት ግለሰቦች አሉ። ዶ/ር ያዕቆብ ፍርድ ቤቱ ቢዘጋም እነዚህን ግለሰቦች ለመዳኘት የሚያስችል መንገድ እንዳለ ተናግረዋል።

ዛሬ በርዋንዳ ሑቱዎችም ይሁኑ ቱትሲዎች ሬድዮ ለማድመጥ ስጋት የለባቸውም። በአንድ ወቅት ጭፍጨፋን ከሰበኩት ባለስልጣናት እና ጋዜጠኞች መካከል አብዛኞቹ ተመልሰው ከማይወጡባቸው የማረሚያ ቤቶች ውስጥ ናቸው። ጥቂቶቹም ቢሆኑ ሽሽታቸው የማያስመልስ ሆኗል። አዲሱ ሥርዓት የፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜን የሶስተኛ የስልጣን ዘመን ፍላጎት የሚያበስርም እንኳ ቢሆን ከትናንት ሳይሻል አይቀርም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ