1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራስታፋርያን የተሰፋ መሬት

Merga Yonas Bulaረቡዕ፣ ግንቦት 3 2008

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለሥላሴ ከ50 ዓመት በፊት ጀማይካን ከጎበኙ ወዲህ «ራስታፋርያን» በብዛት ተስፋፍቶአል። የጉብኝታቸዉን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የአፄ ኃይለሥላሴ የልጅ ልጅ ልዑል ኤርሚያስ፤ ባለፈዉ ሰሞን ጃማይካን በጎበኙበት ወቅት የራስታፋርያን እምነት ተከታዮች ከፍተኛ አቀባበል አድርገዉላቸዋል።

https://p.dw.com/p/1Il7t
Reggae Fans in Addis Abeba bei einem Festival
ምስል picture-alliance/ dpa

[No title]

የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለሥላሴ ጃማይካን የጎበኙበትን ተከትሎ የዛሬ 50 ዓመት ገደማ ነበር «ራስታፋርያንም» የተባለዉ እምነትና የራሱ የሆነ የኑሮ ዘይቤ በጃማይካ የተወለደዉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሚሊዮን ተከታዮች እንዳሉት የሚነገርለት የራስታፋርያን እምነት አራማጆች አፍሪቃን፣ በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን፣ እንደ ቅዱስና የተስፋ መሪት እንደሚያዩዋት ይታወቃል። ግን ይህ ይህ የታስፋ መሬት ለራስታፋርያኖች ምን ያል ተስፋ ሰጥቶ ይሆን?


ላለፉት 40 ዓመታት በሻሸማኔ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዴስሞን ማርቲን፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙት የራስታፋርያን ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ናቸዉ። ዴስሞን ማርቲን በኢትዮጵያ ለአራት አስርተ ዓመታት ሲኖሩ ቋሚ የመኖርያ ፈቃድና ሞያዊ ሥራም እንደሌላቸዉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የራስታፋርያን ማኅበረሰብ ተጠሪ ዜግኔት የማገኘት ስራ እየሰሩ እንደሆነ ይናገራሉ።

«በአሁኑ ጊዜ በሻሸመኔ ለሚኖሩ ራስታፋሪያን ማኅበረሰብ የመኖርያ ፍቃድና ተያያዥ ችግሮች እንዲቀረፍላቸዉ እየሰራን ነዉ። ምክንያቱም መንግሥት እስከ አሁን ለእነዚህ ማኅበረሰቦች እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እዉቅና አልሰጣቸዉም። እንደ ማኅበረሰብ ግን እዉቅናን ተሰጥቶአቸዋል። እነዚህ ማኅበረሰቦች እስካሁን ድረስ የዉጭ ዜጋ እና ጃማይካኖች ናቸዉ። በአንድ በኩል መንግስት እየቀለደም ይመስላል፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ከጃማይካን ወላጅ የተወለደ ልጅ እንዴት የጃማይካ ዜጋ ይሆናል? እዚህ አገር የሚወለዱ ሕፃናት የኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊሰጣቸዉ ይገባል። እንዲያም ሆኖ ኢትዮጲያ አሁንም የተስፋ መሬት ናት፣ የኤዴን ገነትን የሚያጠጣዉ የአባይ መነሻ አገር። ኢትዮጵያ የጽዮን መግብያ በር ናት።»


ዜግነትም ሆነ ቋሚ የመኖርያ ፈቃድ እንደሌላቸዉ የሚገልፁት ዴስሞን፤ እንዲያም ቢሆን ኢትዮጵያ የተስፋ መሪትና የጽዮን መግብያ በር እንደሆነች ይናገራሉ። እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር 1920ዎቹ የተጀመረዉ የራስተፋርያን እንቅስቃሴ በተፈጥሮዋዊ አኗኗር እና በአፍሪቃ ነፃነት መሠረት ያደረገ ነዉ ሲሉ የሚገልፁት የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ አቶ ዘለቀ ገሴሴ ራስታፋርያኖች ኢትዮጵያን እንደ መንፈሳዊ ቤት አርገዉ እንደሚቆጥሩም ተናግረዋል። አቶ ዘለቀ በመቀጠል በኢትዮጵያ ለሚኖሩት ራስታፋርያን ችግራቸዉን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ምክር እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ