1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ወታደር አራት ባልደረቦቹን ገደለ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2 2007

አንድ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ወታደር ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ አራት የሩዋንዳ ባልደረቦቹን ገደለ ፤ ሌሎች ስምንት ደግሞ አቆሰለ። እንደ ሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር ከሆነ ግድያ ፈፃሚው ራሱን አጥፍቷል። ጥቃቱ የተፈፀመው ዛሬ ጠዋት ባንግዊ መዲና ነው።

https://p.dw.com/p/1GC8O
Symbolbild UN Truppen in der Zentralafrikanischen Republik
ምስል picture alliance/AA/Str

የጥቃቱን መንስኤ በፍጥነት ማጣራት ጀምረናል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጆሴፍ ንዛባምዋቲ ለሮይተርስ ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ በአሁኑ ሰዓት የሚጠረጠረው የሽብር ጥቃት መሆኑንም ተናግረዋል።

ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የወደቀች ከሁለት ዓመታት በፊት ሙስሊሞች የሚያመዝኑበት የሴልካ አማፂያን ስልጣን በመቆጣጠራቸው የፀረ-ባላካ ክርስቲያን ታጣቂዎች በወሰዱት የበቀል ርምጃ ከአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በማባረራቸው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን ለማረጋጋትና ከውድቀት ለመታደግ የሽግግር መንግስቱን የሚደግፍ ሚኑስካ በተሰኘ ተልዕኮ ወታደሮችን ወደ ሀገሪቱ ማዝመቱ አይዘነጋም።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዜጎችን ለሞት የዳረገውን የሃይማኖት ግጭት ለመፍታት ወደ አገሪቱ የገባውና ሚኑስካ የተሰኘው ተልዕኮ ወታደሮች ከሁሉም የከፋ ነው ተብሏል።

የወታደሩ ጥቃት በተልዕኮው ቃል አቀባይና የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጦር ሰራዊት የተረጋገጠ ሲሆን የሩዋንዳ ጦር አመራሮች እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

የሚኑስካ ተልዕኮ ከብሩንዲ፤ካሜሩን፤ኮንጎ፤ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ጋቦን፤ሞሮኮ፤ሴኔጋል፤ፓኪስታንና ኢንዶኔዥያ የተውጣጡ 10,800 ወታደሮችን የያዘ ነው።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ