1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩስያ ብሔራዊ ሸርፍ «ሩብል» ዋጋ መውደቅ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 9 2007

የሩስያ ማዕከላይ ባንክ የሀገሩ ገንዘብ «ሩብል» ዋጋ እያሽቆለቆለ የተገኘበትን ሁኔታ ለማከላከል በአሁኑ ጊዜ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፣ ይሁንና፣ የእስካሁኑ ጥረቱ አንድም የረባ ውጤት አላስገኘለትም። የሩብል መውደቅ ሩስያን ወደ ከፋው የኤኮኖሚ ቀውስ ወስጥ ይጥላት ይሆን?

https://p.dw.com/p/1E6iR
Symbolbild - Rubel auch nach Riesen-Zinsschritt auf Talfahrt
ምስል picture-alliance/dpa/Karl-Josef Hildenbrand

የሩስያ ማዕከላይ ባንክ የሀገሩ ገንዘብ «ሩብል» እየወደቀ የሄደበትን ድርጊት ለማስቆም ትናንት ሁነኛ ርምጃ ወሰደ። ባንኩ ለገንዘብ ድርጅቶች የሚሰጠውን ወለድ ከ10,5 ከመቶ ወደ 17 ከመቶ ከፍ አድርጎታል። የማዕከላዩ ባንክ ኃላፊ ኤልቪራ ናቢውሊና ትናንት «ሮሲያ 24» ለተባለው የሀገራቸው ራድዮ እንዳስረዱት፣ ይህ ርምጃ ሩብል የገጠመውን ከፍተኛ የዋጋ ውድቀትን ገደብ ሊያሳርፍበት ይችላል። ማዕከላይ ባንኩ ባለፈው ሳምንት አክስየን በመግዛት እና መጠነኛ የወለድ ጭማሪ በማድረግ ሁኔታውን ለማስተካከል ሙከራ ቢያደርግም፣ ጥረቱ ውጤት አልባ ነበር፣ እንዲያውም ለአንድ ዶላር 80 እንዲሁም ለአንድ ዩሮ 100 ሩብል ነበር የተከፈለው። እ.አ.አ. ከ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ ወዲህ ሩብል 60 % ዋጋውን አጥቶዋል። ለዚሁ ውድቀት በተለይ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ የቀነሰበት እና ምዕራቡ ሩስያ በዩክሬይን ውዝግብ ተጫውታዋለች ባለው ሚና የተነሳ የጣለባት ማዕቀብ ተጠያቂ ነው። በሩብል ዋጋ ውድቀት ሰበብም በሩስያ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ በጣም ተወዶዋል።
እነዚህ ሁኔታዎች ሀገሪቱን ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት ይችላል በሚል ሩስያውያን ስጋታቸውን ሲገልጹ ይሰማል። ይሁንና፣ በበርሊን የፍራየ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ አውሮጳ ጥናት ተመራማሪ ጀርመናዊው ሀንስ ሄኒንግ ሽረደር ፣ ችግሩ ያን ያህል ርቆ እንደማይሄድ ነው ለዶይቸ ቬለ ያስረዱት።
« ሩስያ አንትኮታኮትም። እርግጥ፣ ሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ችግር ላይ ትገኛለች፣ ይኸው ችግርም በሚቀጥለው ዓመትም ብዙ ሩስያውያንን ይጎዳል። ይሁንና፣ ይህ በዩክሬይን ውዝግብ ሰበብ በሩስያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ፣ የሩስያ አመራር አንዳችም ገላጋይ ሀሳብ ላይ ሳይደርስ፣ ሊነሳ አይገባም። ሩስያ የአውሮጳውያኑን የሰላም ሥርዓት በማስከበሩ ተግባር ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆን አለባት። »
የብሬመን ፌዴራዊ ግዛት ማዕከላይ ባንክ የኤኮኖሚ ጠቢብ ፎልከር ሄልማየርም የሩስያ ሸርፍ «ሩብል» ውድቀት ቢያጋጥመውም፣ የሀገሪቱ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ አዎንታዊ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
« ወቅታዊው ሁኔታ ከ15 ዓመታት ወይም ከዚያ በፊት ከታየው ቀውስ ጋ የሚነፃፀር አይደለም፤ ምክንያቱም፣ ሩስያ አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ከዚያን ጊዜው የተለየ ነውና። የውጭ ምንዛሪውን ክምችት እንኳን ብንመለከት፣ 420 ቢልዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያላት ሩስያ በዓለም ሶስተኛውን ቦታ ነው የያዘችው። ዩኤስ አሜሪካ 120 ቢልዮን ዶላር፣ ዩሮን ብሔራዊ ሸርፋቸው ያደረጉት አውሮጳውያት ሀገራት በጠቅላላ ደግሞ 220 ቢልዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ክምችት ነው ያላቸው። ከዚህ በተጨማሪ የሩስያ የመንግሥት በጀት ትርፍ የታየበት ሲሆን፣ ዘንድሮ 1,5% ጭማሪ አስመዝግቦዋል። በጀርመን የመንግሥቱ በጀት ምንም ጭማሪ ያላሳየ ሲሆን በዩኤስ አሜሪካ ከዜሮ በታች 5,5 ከመቶ ነው። የሩስያ መንግሥት የውጭ ዕዳ ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢው 13 ከመቶ ሲሆን፣ የጀርመን 77 ከመቶ፣ የዩኤስ አሜሪካ ደግሞ 108 ከመቶ ነው። »
በመሆኑም፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰው መዘርዝር የሩስያ ኤኮኖሚ ያን ያህል አስከፊ ደረጃ ላይ አለመድረሱን ያሳያል። ያም ቢሆን ግን፣ ይላሉ በበርሊን የፍራየ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ አውሮጳ ጥናት ተመራማሪ ጀርመናዊው ሀንስ ሄኒንግ ሽረደር፣ በተለይ ባለፈው ሀምሌ ወር ምዕራቡ አጠናክሮ የጣለው ተጨማሪ ማዕቀብ፣ ማለትም፣ በሩስያ ባንኮች ላይ ጫናውን ያጠናከረበት ርምጃ በሩስያ ኤኮኖሚ ዘርፍ ላይ ሥነ አዕምሮአዊ መዘዝ አስከትሎ፣ በማዕቀቡ የተነሳ በሩስያ ገንዘባቸውን የሚያሰሩ ባለሀብቶች ቁጥር ቀንሶዋል። ይሁንና፣ ይኸው እየተጠናከረ የመጣው ጫና፣ የሩስያን አመራር የማዕቀቡ ምክንያት በሆነው የምሥራቅ ዩክሬይን ውዝግብ ላይ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ድርድር እንዲጀምር ዝግጁ ሊያደርገው መቻል አለመቻሉን ሽረደር ሳያጠያይቁ አላለፉም።

Russland Währung Euro und Rubel
ምስል RIA Novosti
Russische Zentralbank Moskau
ምስል imago


ኡልሪኽ ክላውስ/አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ