1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ አላማ እና ግብ በሶርያ

ዓርብ፣ መስከረም 13 2009

በሶርያዉ የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ሩሲያ መሳተፍ ከጀመረች አንድ ዓመት ሊሆናት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተዋል። የፖለቲካ ተንታኞች ሞስኮ በዚህ ግጭት ዉስጥ ለመግባት የተነሳችበትን አላማ አጋሯ የሆኖት ፕሬዝደንት ባሽር አላሳድ መንበር እንዳይገለበጥ በማድረግ፤ ዩናይትድ ስቴትስንም ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ በማስቀመጥ አሳክታለች ባይ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1K7FZ
Syrien Angriff auf Hilfskonvoi
ምስል Getty Images/AFP/O. Haj Kadour

[No title]

ያም ሆኖ ዕለት በዕለት እየፈራረሰች የምትሄደዉ ሀገር ዉስጥ የተቀሰቀሰዉን ግጭት ለማብረድ የሚችል መፍትሄ ግን እስካሁን አይታይም።

ሶርያ ዉስጥ አሌፖ ግዛት የተመድ እርዳታ የጫነ አጀብ ጥቃት ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሩሲያ እና ዩናይትድ ስቴትስ የሚለዋወጡት ቃላት ጠንከር ብሏል። የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ፤ ከሩሲያዉ አቻቸዉ ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ከተወያዩ በኋላ፤ ረቡዕ ዕለት በኒዉዮርክ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጉዳይ ስብሰባ ባሰሙት ንግግር ሞስኮ በሌላ ዓለም ዉስጥ የምትኖር ይመስላል ሲሉ ተችተዋል። የእርዳታዉ አጀብ ላይ የደረሰዉ የአየር ጥቃት ነዉ የምትለዉ ዋሽንግተን፤ ለዚህም ወይ የሶርያ አለያም የሩሲያ መንግሥት ተጠያቂዎች ናቸዉ ባይ ናት። ጥፋተኛዉ ይሄ ነዉ ብሎ ለመወንጀል መቸኮል እንደማይገባ ያስጠንነቀቁት ላብሮቭ በበኩላቸዉ፤ አጠቃላይ የምርመራዉ ዉጤት ይፋ እስኪሆን መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። ክሱን የተቃወሙት የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴርም በፋንታዉ ጣቱን ተጠያቂዎች ናቸዉ ወዳላቸዉ አማፅያን ወይም አሜሪካን ላይ ጠቁሟል። አክሎም ከእርዳታዉ አጀብ አቅራቢያ ላዉንቸር የተጠመደበት ተሽከርካሪን የሚያሳይ ከአየር የተነሳ ፎቶግራፍም ይፋ አድርጓል።

US-Außenminister John Kerry Staffan de Mistura und Sergey Lavrov
ኬሪ እና ላቭሮቭምስል picture alliance/abaca/F. Aktas

በሶርያ መንግሥት ወታደሮች ኃይል ሥር በምትገኘዉ አሌፖ ከተማ ለሚገኙ ዜጎች ከተመድ የተላከዉ የመጀመሪያዉ እርዳታ ሰኞ ዕለት በደረሰበት ጥቃት ወድሟል። በዚህም 29 የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። አማፅያኑ የዋሽንግተንን አቋም ይደግፋሉ። የሩሲያን መንግሥት የሚተቸዉ የግጭት ሰላይ ቡድን በምሕጻሩ CITም እንዲሁም ከኢንተርኔት ይፋዊ መረጃዎችን በመመርመር ሞስኮን ተጠያቂ አድርጓል። CIT ባቀረበዉ ትንተናም የእርዳታ አጀቡ የወደመዉ በአየር ጥቃት መሆኑ እሙን ነዉ፤ ይህም ወይ የአሳድ መንግሥት ወይም የሩሲያ የአየር ጥቃት ሊሆን ይቻላል ባይ ነዉ። የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ያቀረበዉ መረጃም አንድም «ከዚህኛዉ አጋጣሚ ጋር ግንኙነት የለዉም» አንድም « ሐሰት ነዉ» ሲልም ደምድሟል።

ዶቼ ቬለ ላነጋገራቸዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ተንታኝ ለአሌክሲ ማላሼንኮ ጥቃቱ ምሥጢራዊ ነዉ፤ «ሁሉም ነገር ቢያንስ ወደ ሶርያ ጦር፤ ከዚያም አልፎ የሩሲያ እጅ እንዳለበት የሚጠቁም ነዉ። ሩሲያ ግን በፍፁም ይህን አታምንም። ፕሬዝደንት ቪላድሚር ፑቲን፤ አዝናለሁ ስህተት ሰርተናል ሲሉ አይታህም?»

ዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ አድርጋለች። ከቀናት በፊት አሜሪካ መራሹ የጦር ጀት የሶርያ ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሷል። ሩሲያ እንደምትለዉ 60 የሶርያ ወታደሮች ተገድለዋል። ሞስኮ እና ደማስቆ ድርጊቱን ተቃወሙ። ዋሽንግተን ለተፈፀመዉ ስህተት ይቅርታ ጠየቀች። ሁለቱ አጋጣሚዎች ሩሲያ እና ዩናይትድ ስቴት ጄኔቫ ላይ መክረዉ ከመስከረም ሁለት 2009 ዓ,ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የተስማሙበትን የተኩስ አቁም ጥያቄ ላይ ጥሎታል። የሶርያ መንግሥት የተኩስ አቁሙ ማብቃቱን ያንንም፤ አማፅያኑ አፍርሰዋል ሲል ይከሳል። በዚህም ምክንያት ሞስኮ በአካባቢዉ ወታደራዊ ኃይሏን አጠናክራለች። ሩሲያ ጦር ሶርያ ዉስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሆን ነዉ። አምና ሞስኮ የጦር አዉሮፕላኖች እና መርከቦቿን ወደ ዚያ ስታጓጉዝ ምን እንደምታደርግ ለዓለም እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር። ዘግየት ብሎ ግን በምዕራብ ሶርያዋ ክፍለ ሃገር ላቲካ ላይ የአየር ኃይል ጦር ሠፈር እየገነባች እንደነበር ታወቀ። መስከረም 20 ነበር ሽብር ላይ ያነጣጠረ ነዉ ያለችዉን የአየር ጥቃት የጀመረችዉ። ምዕራቡ ዓለም ሞስኮ ለዘብተኛ የሆኑ የአሳድ ተቃዋሚ ኃይሎችንም ትደበድባቸለች ሲሉ ከሰዋል። ሩሲያ በበኩሏ በዚህ በኩል የምታደርገዉ አዎንታዊ አስተዋፅኦ አለዉ ባይ ናት። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉትም በአንድ በኩል አጋሯ የሆኑትን ፕሬዝደንት ባሽር አላሳድን ትደግፋለች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ለድርድር እንድትቀመጥ ማስገደድ ችላለች። በዚህም በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እንደተባለዉ በአካባቢዉ «ብቸኛ ኃይል» እንደሌለ ማሳየት በመቻሏም የሞስኮ ዕቅድ ግቡን መቷን ይላሉ አሌክሲ ማላሼንኮ። በምዕራባዉያን ምሁራን ዕይታ አሁን ሩሲያ ይዞታዋን በመካከለኛዉ ምሥራቅ አጠናክራለች። በበርሊኑ የፖለቲካ ምርምር ተቋም ባልደረባ ማርጋሬተ ክላይን እምነትም፤ ሶርያ ዉስጥ ካለ ሞስኮ ወይም ከፍላጎቷ በተቃራኒ ምንም ማድረግ አይቻልም። ያም ሆኖ ይላሉ ማላሼንኮ፤ ለችግሩ የሚበጅ መፍትሄ ሞስኮም ሆነች ዋሽንግተን ስላላቀረቡ ግጭት ጦርነቱ መቀጠሉ አይቀርም። እንደዉም ትችታቸዉ ሩሲያ ላይ ይጠናል።

Syrien Situation in Aleppo
በዉጊያ የደቀቀችዉ አሌፖምስል picture-alliance/dpa/Imageslive/O. Jumaa

«ፑቲን ጠንካራ ስልታዊ አቋም አላቸዉ፤ ሆኖም እንዴት ሊጫወቱበት እንደሚገባ አያዉቁም፤ አሳድ እንደሚሰናበቱ ያዉቃሉ፤ ግን ማን ነዉ የሚተካቸዉ?»

ሮማን ጎንቻሬንኮ/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ