1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሢያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባልነት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 29 2004

ሩሢያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል የምትሆንነት ጊዜ እየተቃረበ በመሄድ ላይ ነው። ሞስኮ ለዚሁ ዓባልነት ስትጥር የ 18 ዓመት ጊዜ አሳልፋለች።

https://p.dw.com/p/RvOK
ምስል AP

አሁን ግን ሩሢያ እንዳስታወቀችው እስካሁን ዓባልነቱን ስትቃወም ከቆየችው ከጆርጂያ ጋር ከሁለት ወገን ስምምነት ተደርሷል። ጆርጂያም ይሄው ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ያለውን ንግድ በጋራ እንዲቆጣጠሩ የሚያደርግ ውል መስፈኑን አረጋግጣለች። ዋሺንግተን ደግሞ በፊናዋ በስዊትዘርላንድ አማካይነት ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ የተገኘውን ስምምነት ስታወድስ ውሉ ሩሢያ እንደ አንድ ግዙፍ ኤኮኖሚ እንዳለው አገር በብቸኝነት ከዓለምአቀፉ ድርጅት ውጭ ሆና መቀጠሏን የሚያበቃ በር የከፈተ ነው የሚመስለው።
በ 2008 ዓ.ም. የአብሃዚያና የደቡብ ኦሤቲያ ጦርነት ተቃቅረው የቆዩት ሞስኮና ጆርጂያ ስምምነቱን በነገው ዕለት ምሽት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል። በስዊስ አማካይነት የተገኘው ይሄው ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል ድንበር አቋራጭ ዓለምአቀፍ የንግድ ቁጥጥርን የሚያሰፍን ነው የሚሆነው። ሩሢያ በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ለመሆን የምታደርገውን ግፊት አጠናክራ ነው የቆየችው። ለዚህም ምዕራባውያን ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሶሥት ዓመታት በፊት ዓለምን ያናጋው የፊናንስ ቀውስና የዓለም ኤኮኖሚ ተጽዕኖ ያሳደረባት ግፊት ምክንያት ሣይሆን አልቀረም። ገበያን በመክፈት ከዓለም በመቀላቀል ሌላ ቀውስ ከተከተለ ጉዳቱን ለዘብ ያለ ለማድረግ በውል የተሰላ ሂደት ነው የሚመስለው።

ለነገሩ ሩሢያ ዓባልነቱን በተመለከተ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያሳየችው ዝንባሌ የተለያየ ነበር። ፕሬዚደንት ዲሚትሪይ ሜድቬዴቭ ሩሢያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል እንድትሆን ፍላጎት ሲያሳዩ በክሬምሊን ቤተ-መንግሥት ከ 2000 እስከ 2008 ዓ.ም. ቀደምታቸው የነበሩትና ምናልባትም በሚቀጥለው ዓመት እንደገና ወደዚያው ሥልጣን የሚመለሱት ቭላዲሚር ፑቲን በአንጻሩ በዓለም ንግድ ድርጅት ጉዳይ ሲቀያየሩ ሞቅ በረድ ሲሉ ነው የቆዩት። ሩሢያ በፑቲን የፕሬዚደንትነት ዘመን በነዳጅ ዘይትና በጋዝ የውጭ ንግዷ በመደገፍ ጠንካራ የኤኮኖሚ ዕድገት ስታሳይ ከዓለም ኤኮኖሚ በመተሳሰሩ ጥረት መቀጠሉ ብዙም ጉዷይዋ አልነበረም።
ግን ሁኔታው እንዲህ አይቀጥልም። የስርዓቷ ድክመት ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በ 2008 ሲከሰት ክፉኛ ይጋለጣል። በተከታዮቹ ሁለት ዓመታት በታላቅ የሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዋ ላይ የደረሰው አደጋና የእርሻው ዘርፍ በድርቅ መመታት አይን ገላጭ ነው የሆኑት። የሞስኮ መንግሥት ከልብ በነጻ የዓለም ንግድ ላይ ማተኮር የጀመረው ምናልባትም ከዚህ በኋላ ነው ሊባል ይቻላል። ለማንኛውም ሩሢያ ዓባልነቱን መፈለጓ ከፖለቲካ ወይስ ከኤኮኖሚ ስሌት? ጉዳዩ እንደገና ጥያቄን ማስነሳቱ አልቀረም። በሰሜናዊው ጀርመን ኪየል ላይ ተቀመጭ የሆነው የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ሮልፍ ላንግሃመር እንደሚናገሩት ከሆነ ከሁለቱም ዝንባሌ መነሳት ይቻላል።

“ምክንያቱ ሁለቱም ነው። ሩሢያ ከቻይና ቀጥላ አሁን ከዓለም ንግድ ድርጅት ውጭ የሆነችው ብቸኛዋ ታላቅ አገር ናት። በሌላ በኩል በሩሢያም ሆነ በዓለም ሕብረተሰብ ዘንድ ዓባልነቱን የሚደግፍ ተጨባጭ የኤኮኖሚ ጥቅም አለ። ዓባልነቱ ከሁለት ወገን፤ ማለት ባይላተራል ስምምነቶች ወጥቶ የሕግ ዋስትናን ለማጠናከር የሚበጅም ነው። ቻይና ለምሳሌ በዚህ ደምብ ከሌሎች ተጽዕኖ እንዳይደርስባት ትጠቀማለች። በሽምግልናው ደምብ ተጠቃሚ ናት። ሩሢያም በአንጻሩ አሁን ዓባል ከሆነች ከየመንግሥታቱ ጋር ያደረገቻቸውን ስምምነቶች በአጠቃላይ ገቢር ማድረግ ይኖርባታል ማለት ነው። ለራሳ ለሩሢያም ይህ ትልቅ የሕግ ዋስትናን ነው የሚያረጋግጠው”

ዓባልነቱ ለሩሢያ የኤኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለው በባለሙያዎች ዘንድ አጠቃላይ የሃሣብ አንድነት አለ። የዓለም ባንክ እንደሚገምተው ሩሢያ ድርጅቱን መቀላቀሏ ብሄራዊ ምርቷን የማሳድግና የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ሁኔታን በጣሙን የሚያሻሽል ነው። እናም አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት የሩሢያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መሆን የኤኮኖሚ ጠቀሜታም ያለው እንጂ የፖለቲካ ክብር ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ የበርሊኑ የሣይንስና የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሱዛን ስቴዋርት እንደሚናገሩት።

“እርግጥ የፖለቲካ ክብር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ከኤኮኖሚ ዕይታ አንጻርም ጠቃሚ ነገር ነው። ለነገሩ የዓለም ንግድ ድርጅት በኤነርጂ ጥያቄ ላይ ያን ያህል ያተኮረ አይደለም። ሩሢያ ደግሞ በአብዛኛው ኤነርጂ ወደ ውጭ የምትሸጥ አገር ናት። በሁለተኛ ደረጃም ድርጅቱ ራሱ በተለይ የዶሃው ድርድር ጥረት ከተቋረጠ ራሱ ትልቅ ችግር ያለው ነው የሚሆነው። የሆነው ሆኖ ግን ለሩሢያ ዓባልነቱ ከመገለል እንድታመልጥና ከዓለም ኤኮኖሚ እንድትተሳሰር አንድ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው የሚሆነው”

ሱዛን ስቴዋርት አያይዘው እንደሚያስገነዝቡት በተለይም በወቅቱ የሩሢያ ኤኮኖሚ በሚገባ ዘመናዊ ባለመሆኑ ለመገለል የተጋለጠ ነው። ስለዚህም ሁኔታውን ለማሻሻል ከትስስሩ ሌላ የተሻለ ምርጫ አይኖርም። ሩሢያ በዓለም ንግድ ድርጅት ዓባልነት ከረጅም ጊዜ አንጻር ተጠቃሚ ብቻ ነው የምትሆነው።

“በዓለም ንግድ ድርጅት ግምት መሠረት ዓባልነቱ ለሩሢያ በረጅም ጊዜ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷን ወደ 11 በመቶ ከፍ እንድታደርግ የሚረዳ ነው። በአጭር ጊዜም ቢሆን የተወሰነ ዕርምጃ መደረጉ አይቀርም። በጥቅሉ ሩሢያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ብትሆን የተወሰኑ የኤኮኖሚ ዘርፎቿ በአገር ውስጥና በውጭ ገበዮችም ለፉክክር ብቁ እንዲሆኑ የሚያደርጋት ነው የሚሆነው”

የሩሢያ የንግድ ድርጅቱ ዓባል መሆን የኤኮኖሚ ተሃድሶን የሚጠይቅና ይህንኑ የሚያራምድ እንደሚሆንም አንድና ሁለት የለውም። ብዙዎች የአገሪቱ ኩባንያዎች ከሁሉም በላይ ደግሞ አምራች የሆኑት ዘርፎች የፉክክር ብቃታቸውን ማሳደግ ይገደዳሉ። ታዲያ ይህን አገሪቱ ንግዷን በመክፈቷ የሚፈጠረውን ግፊት የሚፈሩት የአገሪቱ ተቺዎች ብዙዎች ናቸው። ግን ይህ አስፈላጊ ያልሆነ ስጋት ነው። ሮልፍ ላንግሃመር እንደሚያስረዱት ሩሢያ አሁኑኑ ሙሉ በሙሉ ንግዷን መክፈት የለባትም። የዓለም ንግድ ድርጅት በዓባል ሃገራትም ሆነ በውስጥና በውጭ አምራቾች መካከል አድልዎ እንዳይፈጠር የቆመ መሣሪያ ነው። እናም ሩሢያ እንዲያውም በብዙሃኑ መንግሥታት ውል መሠረት ችግር ሲፈጠር የድርጅቱን የሽምገላ ተግባር ልትጠቀምበት’ ትችላለች።

ሌላው ጥቅሟም የድርጅቱ ደምቦች ሲቀረጹ አብራ ጠረጴዛ ላይ መቀመጥ መቻሏ ነው። አንድ አገር ዓባል ከሆነ በአንዳንድ አቋሙ ከሌሎች ለማበርና በሂደቱ ተጽዕኖ ለማድረግም ዕድል ይኖረዋል። የሩሢያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባልነት አገሪቱ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር አዲስ የሽርክናና የትብብር ውል የማስፈኗን ጥረት የሚያፋጥንም ነው የሚሆነው። የአውሮፓ ሕብረት ከሩሢያ ጋር ያለውን ግንኙነት አቅድ የሚያስይዝ ውል ለማስፈን ሲደራደር የተወሰኑ ዓመታትን አሳልፏል። ይህም በሩሢያ የንግዱ ድርጅት ዓባልነት ላይ የመሠረተ ነው።

እርግጥ ዓባልነቱ ለአንዳንድ በመንግሥት ድጎማ ሲተዳደሩ ለቆዩ ለምሳሌ ለአውቶሞቢልና አሮጌ የመድሃኒት ቅመማ ኢንዱስትሪዎች ማብቂያም ሊሆን ይችላል። ሣይቤሪያን በሚያቋርጡ የአውሮፓ በራሪዎች ላይ ቀረጥ ሲጥል የቆየውን የሩሢያን አየር መንገድም የሚጎዳ ነው። የሩሢያ ገበሬዎችም ከጎረቤት አገሮች በሚገባው የምግብ ምርት ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥማቸው አንድና ሁለት የለውም።

ያም ሆነ ይህ ሩሢያ እስከያዝነው 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በዓለም ንግድ ድርጅት ተቀባይነት እንድታገኝ በቅርቡ ፈረንሣይ-ካን ላይ ተሰብስበው የነበሩት የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎችም ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ሞስኮ ከጆርጂያ ጋር ያላትን ውዝግብ አስወግዳ ባለፈው ሣምንት ጥርጊያውን ከከፈተች ወዲህ ከእንግዲህ የሩሢያን ዓባልነት ሊያሰናክል የሚችለው ምናልባት የኡክራኒያ ተቃውሞ ነው። ሩሢያ ለዓባልነት እንድትበቃ መላው የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መንግሥታት በአንድ ድምጽ መወሰናቸው ግድ ይሆናል። እናም ሞስኮ የመጨረሻውን መሰናክል ለማለፍ ለኡክራኒያ በምትሸጠው ጋዝ ላይ የዋጋ ቅነሣ ማድረግ ግድ ሊሆንባት ይችላል።
ሁለቱ መንግሥታት በወቅቱ አከራካሪ ሆኖ የቆየውን የ 2009 ዓ.ም. ስምምነት በሚተካ በአዲስ የጋዝ አቅርቦት ውል ላይ እየተደራደሩ ነው። የዓለም ንግድ ድርጅት ዛሬ 153 ዓባል መንግሥታት ሲኖሩት ከነዚሁ መካከልም አብዛኞቹ የቀድሞዎቹ ሶቪየት ሬፑብሊኮች ይገኙበታል። ለሩሢያ ሙሉ ዓባልነት በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ የመጨረሻው ድምጽ አሰጣጥ ከታሕሣስ 15 እስከ 17 እንደሚካሄድ ነው የሚጠበቀው። የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባልነትን ጉዳይ ካነሣን በጀኔቫው ተቋም ዘንድ ማመልከቻ ካስገቡት አገሮች መካከል ኢትዮጵያም ትገኝበታለች። ሆኖም ለዚሁ የሚያበቁትን ለውጦች በማካሄዱ ረገድ ለምሳሌ ቴሌኮሙኒኬሺንን ወደ ግል ዕጅ የማዛወሩን ዕርምጃ ጨምሮ ብዙም ጎልቶ የሚታይ ለውጥ እስካሁን የለም።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ