1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሥነ ቅመማ ሊቃውንት 63ኛ ጉባዔ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2005

በያመቱ ፣ እ ጎ አ ከ 1901 ዓ ም አንስቶ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀውን የኖቤል ሽልማት ለማግኘት የማይመኝ የሳይንስ ተማራማሪ ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግር ይሆናል። ተሳክቶላቸው በየጊዜው ከፍኛውን ሽልማት የሚያገኙትና በሙያው አንቱ የሚሰኙት ሊቃውንት

https://p.dw.com/p/191jb

፥ ተመራማሪዎች፣ የኖቤል ሽልማት የማግኘት ዕድል ከገጠማቸውና ፣ የተሣካላቸው ፣ አሸናፊ መሆናቸው ከተገለጠበት ዓመት በኋላ ምንድን ነው የሚያደርጉት? በምርምር ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ ያለው ተግባር በኅብረትም ሆነ በተናጠል እስከምን ድረስ ነው የሚያከናውኑት?

BASF Anlage zur Herstellung von Ecoflex Kunststoff
ምስል BASF

63ኛው የኖቤል ተሸላሚ የሥነ ቅመማ ሊቃውንትና ወጣት ተመራማሪዎች ጉባዔ ፣ ዘንድሮ ካለፈው እሁድ አንስቶ፣ «ቦደንዜ » በተሰኘው የጀርመን እስዊትስርላንድና ኦስትሪያ አዋሳኝ በሆነው ሐይቅ ዳር በምትገኘው በደቡባዊቷ የጀርመን ከተማ ፤ ሊንዳው፣ ለአንድ ሳምንት በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከ 34 የኖቤል ሽልማት ካላቸው ሊቃውንት ጋር ከ 600 በላይ ወጣት ተመራማሪዎች ናቸው በመሳተፍ ላይ የሚገኙት። በዚህ ዐቢይ ጉባዔ የቀድሞው የምሥራቅ ቲሞር ፕሬዚዳንትና የኖቤል ሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆሴ ራሞስ ኦርታ በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን፣ የጀርመን የትምህርትና የምርምር ጉዳይ ሚንስትር ወ/ሮ ዮሐና ቫንካ ፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማሰማት እስከ ፊታችን ዓርብ የሚዘልቀውን ጉባዔው መርቀው ከፍተዋል።

በዘንድሮው ጉባዔ ዐቢይ ትኩረት የሚደረግበት ርእሰ -ጉዳይ፣ የኃይል ምንጭ በማግኘት በመቀየርና በማጠራቀም፤ ሥነ ህይወታዊና ሥነ ቅመማዊ ሂደትን « አረንጓዴ ሥነ ቅመማ» የተሰኘውን ለተፈጥሮ አካባቢ በሚበጅ መልኩ ሥራ ላይ ማዋል ወይም ተግባራዊ ማድረግ የሚለው ነው።

ያም ሆኖ ከዚህ በላቀ ሁኔታ የሚያጓጓው፤ የኖቤል ተሸላሚዎቹ፣ከሞላ ጎደል ከ 80 ገደማ ሃገራት ከተውጣጡ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችና ወጣት ተመራማሪዎች ጋር ተገናኝተው መወያየት የሚችሉበት አጋጣሚ ነው ። ተሳታፊዎቹ ተማሪዎችና ወጣት ተመራማሪዎች የሚመለመሉትም ሆነ የሚመረጡት ፣ ለሳይንሳዊ ምርምር ተባባሪዎች በሆኑ ድርጅቶች ነው። እነዚሁ የጉባዔው ይፋ ታዳሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ከመላዋ ጀርመን የተውጣጡ 21 የሥነ ቅመማ መምህራንም ጭምር ተጋብዘዋል። ከታወቁት ተሸላሚ የሥነ ቅመማ ሊቃውንት መካከል፤ ኔደርላንዳዊው ፓውል ክሩትዘን፣ የእስዊሱ ኩርት ቩዑትሪኽ ፣ የሙዩኒኩ ሮበርት ሁበር፤ የበርሊኑ ጌርሃርት ኤርትል፤ የፍራንከፈርቱ ሃርትሙት ሚ*ሼል ፣ በፊዚክስ ተሸላሚው የሙዩኒኩ ቴዎዶር ሄንሽ፣ የገዐቲንገኑ ኤርቪን ኔኸር፣ እንዲሁም የሃይድልበርጉ ሃራልድ ሱር ሃውዘን ፤ ሁለቱም በህክምና የኖቤል ተሸላሚዎች ጭምር የጉባዔው ታዳሚዎች ናቸው። የሳይንሳዊው ጉባዔ መርኀ ግብር ቀዳሚ ተናጋሪ ባለፈው ታኅሳስ መባቻ በሥነ ቅመማ የኖቤል ሽልማት የተቀበሉት አሜሪካዊው ተመራማሪ ብራያን ኮቢልካ ናቸው ። በሥነ ቅመማ ፤ ህክምናና ፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚዎች ፣ እ ጎ አ ከ 1951 ዓ ም አንስቶ በያመቱ በተጠቀሰው ቦታ እንዲሰበሰቡ ያበቁት በዚያው በቦደንዜ ሐይቅ የምትገኘው የአበባ ትርዒት የሚታይባት ደሴት ባለቤት የሆኑት ሌናርት ቤርናዶቴ የተባሉት ታዋቂ ግለሰብ ናቸው። እ ጎ አ ከ 2004 ዓ ም፤ አንስቶም በኤኮኖሚ የኖቤል ሽልማት ያገኙ ሰዎች በ የ2 ዓመት አንድ ጊዜ በተጠቀሰው ቦታ ይሰበሰባሉ ።

Bayer Werk Leverkusen Schornsteine
ምስል picture-alliance/dpa

ባለፉት 20 ዓመታት ገደማ በዓለም ዙሪያ ፣ በተለይ በኢንዱስትሪ በገሠገሡት አገሮች፤ «አረንጓዴ ሥነ ቅመማ »የተሰኘው መፈክር በሰፊው ሲስተጋባና ፣ በአረንጓዴ ሥነ ቅመማ ንቅናቄ ግፊት በተግባርም እንዲተረጎም ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው። እንቅሥቃሴው የተጠናከረውም፤ በመጀመሪያ ሰቬዞ በተባለችው የኢጣልያ ከተማ ፣ እ ጎ አ ሐምሌ 10 ቀን 1976 የዲዮክሲን አደጋ፤ ከዚያም እ ጎ አ ታኅስስ 3 ቀን 1984 ዓ ም፤ ቦፓል በተባለችው የህንድ ከተማ ከፋብሪካ በፈነዳውና እጅግ አደገኛ በነበረው መርዘኛ የ«ኬሚካል» ልቀት ቢያንስ 3,000 ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነበር።

ከ ጊዜ ወደ ጊዜ የተፈጥሮ አካባቢ እንዳይበከል የወጡ ህግጋትና ደንቦችን መመሪያ በማድረግ የኬሚካል ኩባንያዎች ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ግፊቱ አየለባቸው ። በመሆኑም ራሳቸው «አረንጓዴ ሥነ ቅመማ » ወደተባለው የአሠራርም ሆነ የማምረቻ ስልት መገፋታቸው አልቀረም። «አረንጓዴ ሥነ ቅመማ » የተሰኘውን መፈክርም ሆነ አባባል በመጀመሪያ እ ጎ አ በ 1991 ዓ ም ያስተዋወቁት ፖል አናስታስ የተባሉት የአሜሪካ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ነክ ድርጅት ባልደረባና የሥነ ቅመማ ምሁር ናቸው።

የአረንጓዴ ሥነ ቅመማ ዋና ዓላማ ፤ ፋብሪካዎች ጥፋት ፤ ብክለት ካደረሱ በኋላ ለማጽዳት ሳይሆን፤ከመጀመሪያው ከሥረ-መሠረቱ ፤ የኬሚካል ማምረቻ ሥነ ቴክኒክን በማደስ፤ አስተማማኝ፤ንፁህ እንዲሁም የኃይል ምንጭ ቆጥቦ ፣ ከሥነ ቅመማው ሥራ ጋር ተያይዞ ፤ ከጅምሩ እስከ ሂደቱና ፍጻሜው እንደአስፈላጊነቱ በታዳሽ የኃይል ምንጭም በመጠቀም፣ የኢንዱስትሪ ዝቃጭ መጠንን በእጅጉ መቀነስ መሆኑንም ነው አናስታስ የሚያስረዱት።

ሥነ ቅመማ አደጋ እንዳያስከትል በተለይ በአዳጊ አገሮች ብርቱ ጥንቃቄ የሚያሻ መሆኑን ጠበብት አበክረው ነው የሚመክሩት። አደጋው ሩቅ አገር ቢከሠትም ፤ በአሁኑ አጽናፋዊ የኤኮኖሚ ትሥሥር ዘመን ፤ ሁሉንም የሚነካካ ነው የሚሆነው። አምራችቾችና ተጠቃሚዎች ፣ ሁሉም በአረንጓዴ ሥነ ቅመማ መጠቀሙ ነው የሚበጃቸው ።ይህን አስመልክተውም ነበር ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO)ባልደረባ ሉዒዘ ፍሬስኮ እንዲህ ሲሉ ያስገነዘቡት።

Arterien und GFP positive Zellen
ምስል picture-alliance/ dpa

«በአውሮፓ የምንኖር ሰዎች የምንመገበውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በይበልጥ ከአዳጊ አገሮች ነው የምናስገባው። ለምሳሌ ያህል ፣ በበረዶአማው የክረምት ወቅት ሰላጣና መሰል ቅጠላ ቅጠልእንዲሁም አትክልት፤ ከአዳጊ አገሮች ወደ ጀርመን ይመጣል። ተመጋቢዎቹ ጀርመናውያን በእነዚህ የምግብ ቅጠላ ቅጠልና አትክልት ምን እንደሚገኝ ማወቁ ጠቃሚአቸው ነው።»

FAO፣ የዓለም ህዝብ ፤ እ ጎ አ እስከ 2030 የሚያስፈልገው የምግብ መጠን 60 ከመቶ ገደማ ከፍ እንደሚል ይገምታል።

አረንጓዴ ሥነ ቅመማ ማለት በሌላ በኩል ለተፈጥሮ አካባቢ ጥንቅ ያልሆነ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ነው። የፀሐይ ፤ የነፋስ፣ ውሃ ፣ እንዲሁም ለተሽከርካሪዎች፣ አማራጭ የሆነው የኤሌክትሪክ ሞተርና የመሳሰሉት የቁሻሻ መቆጣጠሪያ ው ፋብሪካም በዚሁ የሚጠቃለሉ ናቸው። ዘመናዊ መብራት ፣ ግብርና ፣ የመረጃ ሥነ-ቴክኒክ እነዚህና የመሳሰሉት ሁሉ የአረንጓዴ ሥነ ቅመማ እመርታዎች ናቸው። ከ ሁለት ዓመት በፊት በተካሄደ በህዝብ አስተያየት መመዘኛ መጠይቅ ውጤት መሠረት 58 ከመቶው ጀርመናውያን ለቅመማ ኢንዱስትሪዎች ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ነው። 99 ከመቶ ጀርመናውያን ፣ ለወደፊቱ የኃይል ምንጭ ጤናማና አስተማማነትም ያለው የፀሐይ ኃይል ነው ብለው ያምናሉ።

«አረንጓዴ ሥነ-ቅመማ» በተባለው ዘመቻ «አቫንቲየም» የተባለ አንድ የኔደርላንድ ኩባንያ ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ተዋጽዖ ሳይሆን፣ ከአትክልትና ከመሳሰለው የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመስራት ኮካ ኮላን ኩባንያን ሳይቀር አማላይ ሆኗል። ይኸው ኩባንያ በተጨማሪ እንዳብራራው «ባዮፕላስቲክ» የተባለው ከአትክልት የሚቀመመው ፕላስቲክ ዐቢይ ትኩረት ነው የተሰጠው። አቫንቲየም፣ አሁን ባለው ዘመናዊ ሥነ ቴክኒክ በመታገዝ ፣ ከ 50 ከመቶ በላይ «ካርቦንዳይኦክሳይድ» ማትረፍ ችሏል።

Reporter in Lindau: Gianna Grün und Hannah Fuchs
ምስል DW

«አረንጓዴ ሥነ ቅመማ » የሚለው መፈክር በይበልጥ መስተጋባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ በየአቅጣጫው በተቻለ መጠን ፣ ለሰው ለእንስሳትና ለተፈጥሮ አካባቢ ጠንቅ በማይሆን ሥነ ቴክኒክም ሆነ ምርምር ላይ ይበልጥ ለማትኮር ጥረት በመደረግ ላይ ነው።

ለምሳሌ ያህል «ኤለቫንስ» የተባለው የዩናይትድ እስቴትስ ኩባንያ፤ ለሰውነት የሚሆኑ ቅባቶችን ከውሃ አረንጓዴ ይቀምማል። የተፈጥሮ ባህርያቸውን ያላጡ የዘይት ዓይነቶችና ለማጽዳት የሚጠቅሙ ፈሳሾችንም ሶያን ከመሳሰሉ የአተርም ሆነ ባቄላ ዓይነቶች አደይ አባባን ከሚመስሉ አባባዎች፣ ከወይራ ፍሬና ከውሃ አረንጓዴ መቀመም እንደሚቻል ታውቋል።

ቤታ ታዳሽ የኃይል ምንጭ የተሰኘ አንድ የኢጣልያ ኩባንያ ወጪን የሚቀንስና ነዳጅን የሚተካ «ኤታኖል» ማምረት የሚችልበትን ሥነ ቴክኒክ አዘጋጅቷል። ኤታኖል ለማምረት የሆነው ሆኖ ፤ ለምግብነት በሚውሉ አትክልቶች ላይ አይደለም ትኩረቱ፤ የተቆራረጠ እንጨትም ለዚሁ ዓላማ አይውልም።

Chemie-Nobelpreisträger-Treffen in Lindau - 1964
ምስል privat

በተጠቀሰው ዘዴ የሚሠራውና በዓለም የመጀመሪያ የተባለው የተጠቀሰው የኢንዱስትሪ ኩባንያ፤ ሥራውን የጀመረው ባለፈው ታኅሳስ ነው። የዚህ ኩባንያ ባለቤቶች እንደሚሉት ከሆነ ፣ የሚያመርቱት ኤታኖል ፣ በበርሜል 70 ዶላር ያህል የሚያወጣ ሲሆን፣ የተለመደውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት፣ በዓይነትም በጥራትም የሚወዳደር ይሆናል። የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋም ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ነው የሚታሰበው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት መሟጠጡ አይቀርም። ስለሆነም ፤ የሥነ ቅመማ ኢንዱስትሪዎች ለረጅም ጊዜው ጠቀሜታ በጥልቀት ማሰብ ማሰላሰል ነው የሚጠበቅባቸው። በሊንዳው ከተሰበሰቡት፤ የሥነ ቅመማ ሊቃውንትና ተመራማሪዎችም ፣ የተፈጥሮ አካባቢን በማይጎዳ መልኩ የዓለማችን የኃይል ምንጭ ችግር ለመፍታት ከመጣር እንደማይቦዝኑ ይታመናል።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ