1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሠራተኞች ቀንና ታሪካዊ ዳራዉ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2002

ከካይሮ-እስከ ጁሐንስ በርግ፥ ከአዲስ አበባ እስከ ዳካርም አንድ ሰሞን ኢንተርናሲኖናል ሲዘመር፥ ሲፈከር ነበር።ዘንድሮ ግን የለም።ካለም ከቁብ የሚገባ አይነት አይደለም።

https://p.dw.com/p/NDWD
አልሞት ባይ ኮሚንስቶች-ሩሲያምስል AP

የገሚስ አለምን አደባዮችን በየአመቱ የዚያን ዕለት የሚያጨናንቀዉ የቀይ ባንዲራ፣የማጭድ መዶሻዉ ድምቀት ብዛት፣ ግዝፈት ኮስምኗል።የድፍን አለምን አይን፣ ጆሮ፣ ቀልብ፣ ከሞስኮ፣ ሐቫና፣ ቤጂንግ፣ በርሊን ጋር የሚያጣብቀዉ የሠልፍ፥መፈክር-ንግግር ዛቻ-ስግግምታ፥ ካለፈዉ ዘመን ጋር ያለፈ ታሪክ ነዉ።የራሞንድ ላቪኘ ያሮጌ-ዘመን ጅምር ግን በርግጥ አልደበዘዘም።የሔይማርኬት ተጨፍጫፊዎችም ከተረሳዉ ዘመን ጋር አልተዘነጉም።የአዲሱ አለም ሠራተኛ አዲስ ብሶቱን እየጮኸ የአሮጌ ዘመን ብጤዎችን ቅዳሜ ዘከረ።ሜይ ዴይ እያለ።የሠራተኞች ቀን-የዘንድሮ አከባበር መነሻ፣ጥንተ ዳራዉ ማጣቃሻ፣ የአዲሱ አለም እዉነታ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

«ሠራተኞች የደረሰባቸዉ ድብደባ» አሉ ኤሮኮስ ፊናሊስ።የአቴና ነዋሪ ናቸዉ።የማተሚያቤት ሠራተኛ።የቅዳሜ ሠልፈኛ።በፖሊስ ላይ የሰነዘሩት ክንዳቸዉ በቆመጥ ተቀጥቅጦ-አብጧል።ፖሊስን የገላመጡበት አይናቸዉ በአስለቃሽ ጢስ ተጨናብሷል።ብሶታቸዉን የሚጮኹበት፣ከችግር የዶሏቸዉን የሚያወግዙበት አፋቸዉ ግን፥ ድምፃቸዉ ሰለለ እንጂ አልተዘጋም።-«በምዕተ አመታት ዉስጥ ከተፈፀሙት ድብደባዎች ሁሉ በጣም የከፋ ነዉ።»

ጥንጣን እንደ በላዉ ግንድ ቅንጥስ ያለዉን የግሪክን ምጣኔ ሐብት ለመጠገን የሐገሪቱ መንግሥት ከአዉሮጳ ሐገራትና ከአለም የገንዘብ ድርጅት አንድ መቶ አስር ቢሊዮን ዩሮ ለመበደር ተስማምቷል። ብድሩን ለማግኘት ግን መንግሥት የሐገሪቱን የገንዘብ ተቋማት ሥርዓት መቀየር፣ ሰራተኞችን መቀነስ፣ ለማይቀነሱት የሚሰጠዉን ደምዝና ጥቅማ ጥቅም ማሳነስ ግድ አለበት።

1.Mai Berlin
የበርሊኑ መፈክርምስል DW

እንደ ፊናሊስ ሁሉ የመንግሥታቸዉ እቅድ የሚቃወሙት ወይዘሮ-ማን እየበላ-ማን ሊራብ አይነት ይጠይቃሉ። ድምፅ

«ትምሕርት ቤትና ዩኒቨርስቲ ለመማርና ለማጥናት ሃያ-አምስት አመት እንፈጃለን።ይሕን የምናደርገዉ በወር የተጣራ አንድ ሺሕ ዩሮ ለማግኘት ሥንልን ነዉ።ከዚችዉ አቅም ሊቀንሱበን ነዉ?የምክር ቤት አባላትና ሥራ-አስኪያጆች በወር አስራ-ስምንት ሺሕ ዩሮ እያገኙ ሊቀጥሉ ነዉ?»

ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊ ኪሳራ የገጠማት የግሪክ ሠራተኞች አጭበርባሪ የባንክ ባለቤቶች፣ጉበኛ ሹመኞች፣ ስግብግብ ባለኩባንያዎች ላደረሱት ኪሳራ ወትሮም ያልደላዉ ሠራተኛ ሥራ-ኑሮዉን እንዲሰዋ መጠቁን-ፊናሊስ፥ ወይዘሮዋና በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ብጤዎቻቸዉ በየጊዜዉ በስራ-ማቆም አድማ በአደባባይ ሠልፍ እንዳወገዙት ነዉ ቅዳሜ የደረሱት።

ሰልፍ-አድማዉ ያመጣዉ ለዉጥ የለም።የአቴና፣ የቴሳሎንኪ የሌሎችም ትላልቅ ከተሞች ሠራተኛ የቅዳሜዉን የሠራተኞች ቀን ከሠልፍ፣ ዉግዘት፣ አድማ ይልቅ የችግሩ ምክንያት ያደረጋቸዉን ባንኮች፣ የገንዘብ ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የንግድና የኩባንያ ሕንፃዎችን በመሰባበር ያከብር ገባ።

የቅዳሜዉን ሠልፉ ካደራጁት የግሪክ ሠራተኛ ማሕበራት ያንዱ መሪ አሌክሲስ ሲፕራስ እንደሚሉት የሠራተኛዉ ጥያቄ፥-ንብረት የመሰባበር አመፁ ምክንያትም ግልፅ ነዉ።

«የግሪክ ሕዝብ የማንም እዳ የለበትም።ለችግሩ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸዉ ባለፉት አመታት የግሪክን ሐብት የበዘበዙት ወገኖች ናቸዉ።የጡረታ አበሉን የመዘበሩት ናቸዉ እንጂ አሁን ሕልዉ ለአደጋ የተጋለጠበት ሠራተኛ አይደለም፥ሥራ አጡ አይደለም፥ ወጣቱ አይደለም፥ የቀን ሠራተኛዉ አይደለም።»

ሠልፈኛዉ ከፖሊስ ጋር በገጠመዉ ግብግብ በመቶ የሚቆጠር ሰዉ ቆስሏል።ብዙ ንብረትም ጠፍቷል።የመተሚያ ቤት ሠራተኛዉ እንደሚሉት ግን የፖሊስ አፀፋ ሲበዛ ከባድ ነበር።«እነሱ ወደ አሥራ-ዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ሊመልሱን ነዉ የሚፈልጉት» አከሉ የሜይ ዴይ ሠልፈኛ- ፊናሊስ።

1.Mai Berlin NO-FLASH
ምስል dpa

አስራ-ዘጠነኛዉ ክፍለ-ዘመን።ወደዚያ ዘመን መመለስ ቢቻል ኖሮ በዘመኑ መጀመሪያዉ ላይ ካርል ሐይንሪሽ ማርክስን እናገኘዉ ነበር።«አለም የሠራተኞች ትሆናለችን ወይም የአለም ሠራተኞች ተባበሩን ሲያስተምር-ሲፅፍ እንሰማ-እናነበዉ ነበር።በዘመኑ ሁለተኛ አጋማሽ የማርክስና የወዳጁ የኤንግሥ ኮኒስታዊ ፍልስፍና ትወራ የነቀነቀዉ ምሁር- ለፖለቲካዊ ለወጥ፥ ወዛደሩ የቀን የሥራ-ሠዓት ከስምንት ሰአት እንዳይበልጥ ሲታገሉ እናይ፥ እንሰማ ወይም እንሳተፍ ነበር።

በስተዘመኑ ማብቂያ በተለይም ግንቦት 4 , 1886 ( ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በማርክስ-ኤንግልስ ፍልፍና የተጃገኑት የቺካጎ ላብ አደሮች የቀን የሥራ-ሠአታቸዉ ከስምንት ሠአት እንዳይበልጥ ለመጠየቅ-ሔይ ማርኬት አደባባይ ወጥተዉ ነበር።የሠልፈኛዉና ሠልፈኛዉን ለመበተን የዘመተዉ ፖሊስ ጠብ ዘንድሮ-አቴና ሌላም ጋ እንደሆነዉ በዱላ-ጢስ ዉሐ ድብድብ አላበቃም ነበር።

በጥይት-ጭፍጭፋ እንጂ።አለም እስካሁን ለሚያዉቀዉ እንደሚመቸዉ ለሚተረጉመዉ ለሠራተኞች ቀን መከበር ሠበብ-ምክንያት የሆነዉም ያኔ በቺካጎ ሠራተኞች ላይ የደረሰዉ ግድያ ነበር።ብዙ ጊዜ የሔይማርኬት ጭፍጨፋ ተብሎ የሚጠራዉ ጠብ-ግጭት ግድያ በተፈፅመ በሰወስተኛ አመቱ ሁለተኛዉ አለም አቀፋዊ የተሰኘዉ ጉባኤ ፓሪስ-ፈረንሳይ ላይ ተሰየመ።ከጉባኤተኞቹ አንዱ የነበሩት ራይሞንድ ላቪኘ የአለም ሠራተኞች የቺካጎ ሙታንን በየአመቱ በሠልፍ እንዲያስቡ ጠየቁ።

ጥያቄዉ ፀደቀ።1890-የመጀመሪያዉ ሠልፍ ተደረገ።በአስራ-አራተኛ አመቱ አምስተርዳም-ኔዘርላንድስ የተሰየመዉ የአለም ሶሻሊስቶች ጉባኤ የአለም የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲዎችና የሠራተኛ ማሕበራት ግንቦት አንድን-በየአመቱ እንዲያከብሩት ደነገገ።የአለም ወዝ-አደር በየአመቱ የዚያን ዕለት በየአደባባዩ-ይሠለፍ «ተነሱ እናንት የረሐብ እስረኞችን» በየቋንቋዉ ይዘምር-ይፈክርም ያዘ።

በ1889ኙ የፓሪስ ጉባኤ ላይ ከሩሲያ ከተወከሉት አምስት መልዕክተኞች ሁለቱ ቭላድሚር ኤሊይቼ ሌሊንና ሊዮን ትሮትስኮይ ነበሩ።ሁለቱ ፖለቲከኞች፥ ኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ላብ-አደር ወዝ አደር እያሉ እንደተቀያየሙት፥ ቦልሸቪክ ሜንሼቪክ ባሏቸዉ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎቻቸዉ አማካይነት እስከተቃቃሩ ድረስ ባንድ ያሳደሙት ሕዝብ ከሞስኮ ቤተ-መንግሥት ዶላቸዉ ነበር።1917።

ሌኒን የመሯቸዉ ኮሚንስቶች የሠራተኞች ቀንን ማክበር ከጀመሩበት የስታሊኗ ግዙፍ የተባበረችዉ የሶቬት የሶሻሊስታዊት ሪፐብሊክ እስከ ተፈረካከሰችበት ድረስ እለቱ ከወትሮ-አለማ ምክንያቱ ይልቅ የኮሚንስት ካፒታሊስቶች ፍጥጫ ማንፀባራቂያ፥ የዛቻ ፉከራ ቀረርቶ መንዢያ፥ጡንቻ ማሳያ የገሚስ አለም በአልም ሆነ።

ዛሬ የማርክስ-ኤንግሥ ፍልስፍና ለአብዛኛዉ አለም ያረጀ-ያፈጀ መርሕ ነዉ።ኮኒዝም-ሶሻሊዝም ባይቀበር-በርግጥ አልሞተም ማለት ጅልነት ነዉ።የእነ ሌኒን ጅምር-ባይሞት ተፈረካክሷል።የአለም ሠራተኞች ቀን ግን በሰማንያ ሐገራት ይከበራል።ለበአሉ መከበር ሠበብ-ምክንያት ለሆኑት ለዩናይትድ ስቴትስ ሠራተኞች ግን ሜይ ዴይ ድሮም-ዘንድሮም በአል አይደለም።

የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች የኮሚንስቶች፥ የሶሻሊስቶች፥ የጋጠ-ወጦች መሰብሰባ ያሉትን በአል ሌላዉ አለም በሚያከብርበት ቀን ላለማክበር የወሰኑት ገና በ1887 ነበር።በዚሕ ጊዜ በፀደቀዉ ደንብ መሠረት ሠራተኛዉ በየአቱ መስከረም-የመጀመሪያዉ ሰኞ ላይ በአሉን ያከብራል።ዘንድሮ ቅዳሜ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ታላቅ ሠልፍ ነበር።የሠልፉ-አለማ ግን ከሰራተኞች መብት መከበር ይልቅ የስደተኞች ተቃዉሞ፥ ተሰላፊዎችም ባብዛኛዉ ስደተኞች ነበሩ።

የአሪዞና መስተዳድር የግዛቲቱ ፖሊስ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የላቸዉም ብሎ የሚጠረጥራቸዉን ሰዎች መታወቂያ እንዲጠይቅ ተጣቂዎች መረጃዉ ከሌላቸዉ እንዲታሰሩ የሚደነግገዉን ሕግ የሚቃወመዉ ሕዝብ በተለይ የሎሳንጀለስ፥ የዳላስ፥ የቺካጎ እና የዋሽንግተን ዲሲ አደባባዮችን በሠልፍ-አጨናንቆ-በመፈክር መዝሙር አድምቋቸዉ ነዉ-የዋለዉ-ቅዳሜን።

ከአሪዞና ደቡብ ምሥራቅ ሐቫና ከ1960ዎቹ ጀምሮ-እንደለመደችዉ ሜይዴይን ለማክበር ሞክራለች።ግን ቀዝቃዘ ነበር።ከአትላንቲክ ወዲሕ ማዶ ሞስኮዎች ሜይ ዴይ ብለዋል።አል-ሞት ባይ አፍቃሬ ኮሚንስቶች የድሕረ-1990ዎቹን በአል እንዳይረሳ-ታደሙ እንጂ የዚያን ዘመኑን አይነት በአል አከበሩ ማለት ይከብዳል።

የሠራተኛዉን አምገነናዊነት የሚሰብከዉ ኮሚንዝም ከመለዘብ-ባለፍ ያልሞተባት ቤጂንግ ቀይ ማንዲራ ማዉለብለቧ፥ የማጭድ መዶሻ አርማ ማስነገቧ አልቀረም።የነ-ማኦ አይነት ሜይ-ዴይ ግን የለም።ሕዝቡ በተለይ ወጣቱም ኑሮን ለማሸነፍ-የወደፊት ሕይወትን ለማሻሻል የሃያ-አራት አመቷ ወጣት ቶን ዬ እንደምትለዉ ብልሐቱ ሌላ ነዉ ይል ይዟል።

«መጀመሪያ ከሠራሁበት የፋብሪካ ሥራ ዳግም አልሠራም።አሁን የተሻለ ነገር አይቻለሁ።ሰዉ ሽቅብ ያድጋል እንጂ ቁልቁል አይጫጫም።በገንዘብ ኪሳራዉ የሆነ-ሥሕተት ካደረግን ለሚከተለዉ ችግር ተጠያቂዎች ልንሆን ይገባል።ብዙ ጊዜ ትርፍ ሠአት መስራት አይፈቀድልንም።ድርጅቱ ጥሩ እየሰራ ነዉ።አልፎ-አልፎ ትርፍ ሠአት እንሠራለን።ያንድ ቀን እረፍት ብቻ ማግኘት ግን በጣም ከባድ ነዉ።»

ብዙዉ እስያዊ ሌላዉ አለምም ከመፈክር-አርማ ለዉጥ ባለፍ ከወቅቱ ፍላጎቱ ልዩነት በስተቀር የቅዳሜዉን የሠራተኞች በአል ያከበረዉ አንድ አለማ አንግቦ ነዉ።የሥራ-ዋስትና።እስያን ከአዉሮጳ የምታገናኛዉ ጥንታዊቷ ታሪካዊት ሐገር ቱርክ በጣሙን ታሪካዊቷ ትልቅ ከተማዋ ኢስታንቡል ለሜይዴይም ልዩ ግን ዘመናዊ ታሪክ አላት።1977 ግንቦት-አንድ ላይ አንድ ያለ ታሪክ።

የታክሲምን አደባባይ ያጭናነቀዉ የኢስታንቡል ሠራተኛ ያዉ በየአመቱ እንደሚያደርገዉ ቀይ ባንዲራዉን እያዉለበለበ ይዘምር-ይፈክራል።መዝሙር-መፈክሩ ጎላ-ደመቅ ጠንከር ደገምገም ማለት ሲጀምር ከአደባባዩ ትይዩ ከሚገኘዉ የሆቴል መስኮት የሚዘንብ የጥይት እሩምታ አካባቢዉን አተረማመሰዉ።ፀጥታ አስከባሪዎች ሰልፈኛዉ በብረት ለበስ ተሽከርካሪ እየገፉ አደባባዩን ወደሚጎራበተዉ ጉብታ ነዱት።

በጉብታዉና በአደባዩ መሐል ግን ትላልቅ መኪኖች ተደርድረዉ ነበር።ጥይቱን እየሸሸ፥ በጦር ሠራዊት እየተገፋ፥በብረት ለበስና በጭነት ተሽከርካሪዎች መካካል የተቃረጠዉ ሕዝብ እየተደናቀፈም-በጥይት እየተመታም ይወድቅ ያዘ።ከሰላሳ በላይ ሞተ።ብዙ ቆሰለ።የገዳዮች ማንነት፥ ጦር ሐይሉ እንዲያ አይነት እርምጃ የወሰደበት ምክንያት እስከ ዛሬ ሚስጥር ነዉ።የታክሲም አደባባይም እስካለፈዉ ቅዳሜ ድረስ ለሜዴይ ሰልፍ ተዘጋ።

ቅዳሜ ግን ሠራተኛዉ ዳግም እዚያ አደባባይ ወጥቶ-ከሰላሳ አመት በፊት የሞቱ አጋሮቹን ደም ደመ-ከልቦ እንደሆነ እንዳይቀር እንደገና በሰልፍ ጠየቀ።ለጀርመኖች የአፍቃሬ ናትሲዎችና የግራ-ዘመሞች መፋጠጪያ፥የሁለቱን ወገኖች ሰልፈኛ ለመለየት መሐል የገባዉ የፀጥታ አስከባሪ መጨነቂያ ነበር-የዘንድሮዉ የሠራተኞች ቀን።በርሊን።

ለወትሮዉ ወደ ግራ የሚያዘነብለዉ የሠራተኛዉን ጥያቄና አለማ የሚንፀባረቅበትን ዕለት ለመቀማት የሞከሩት የኒዮ ናትሲዎቹ አለማ በርግጥ አደገኛ አደረጃጀት-አሰላለፋቸዉም አስጊ ነበር።ማንነታቸዉን በግልፅ ማሳየት፥ ለመገናኛ ዘዴዎች መግልፅ መስጠት፥ ከሰጡም ትክክለኛ ስማቸዉን መናገር አይፈልጉም።ግን ይሰለፋሉ።ናትሲዎቹን በመቃወም አደባባይ የወጡት ባንፃሩ ሰላማዊ ነን ይላሉ-እናንት ማንናቸሁ።

ናትሴዎቹን ለመቃዉም በርሊን አደባባይ ከወጡት አንዱ የቀድሞዉ የጀርመን ምክር ቤት ፕሬዝዳት ቮልፍ ጋንግ ቲርዘ አፍቃሬ ናትሴዎች-ሜይ ዴይን ለመጥፎ አላማቸዉን ሊያዉሉት አይገባም ይላሉ።

ከበርሊን ይልቅ የደቡባዊቷ የጀርመን ከተማ ጠንከር ያለ ግጭት ነበረባት።ቢሆንም የፖሊስ ባለሥልጣናት እንዳሉት የከፋ የሚባል-አይነት አይደለም።ለነገሩ ፓሪስ፥ ሮም፥ ለንደንም የሠልፈኛና የፀጥታ አስከባሪዎች ግጭት አልተለያቸዉም።ሜይ ዴይ በዓሉ አለ።አከባበሩ ግን ከተለወጠዉ አዲስ አለም ጋር ተለዉጧል።

ከካይሮ-እስከ ጁሐንስ በርግ፥ ከአዲስ አበባ እስከ ዳካርም አንድ ሰሞን ኢንተርናሲኖናል ሲዘመር፥ ሲፈከር ነበር።ዘንድሮ ግን የለም።ካለም ከቁብ የሚገባ አይነት አይደለም።የኢትዮጵያ ሠራተኞ ማሕበራት ኮንፌደሬሽን ኢሠማኮ ያወጣዉ መግጫማ ደግሞ በሉን ማክበር ቀርቶ የሠራተኞች የመደራጀት መብት እንኳ የለም የሚል ነዉ።ሊባኖስ ዉስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያዉን ግን ከሌሎች ሐገራት ብጤዎቻቸዉ ጋር ሆነዉ-ከቤይሩት አደባባይ ቢያንስ ብሶታቸዉን መናገር ችለዋል።ሜይ-ዴይ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Agenturen,Dw

Negash Mohammed

Shewaye Legesse