1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች በአፍሪቃ

ሐሙስ፣ መስከረም 20 2008

በኒው ዮርክ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪቃውያን መሪዎች በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች አመርቂ ስኬቶች ማስመዝገባቸውን እየተናገሩ ነው። ለመሆኑ የምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች አፈጻጸም በአፍሪቃ ምን ይመስል ነበር? ባለፈው ሰኞ ይህን ጉዳይ የሚፈትሽ ዘገባ ይፋ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/1GgoZ
Argobba - Tollaha Dorf
ምስል DW

[No title]

የአፍሪቃ መሪዎች ከኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመታዊ ጉባዔ መልስ ለአዲሱ ዘላቂ የልማት ግቦች ትግበራ ስኬታማነት አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮች፤ የገንዘብ ምንጭና የመረጃ አያያዝ መንገድ ያስፈልጋቸዋል። አፍሪቃውያኑ አዲሶቹ ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬታማ ለማድረግ ባለፉት አስራ አምስት አመታት በከወኗቸው የምዕተ-አመቱ የልማት ግቦች አመርቂ ተግባራት ላይ መሠረት ሊያደርጉ ይገባል ሲል አዲስ የወጣዉ ዘገባ አትቷል።


የአፍሪቃ ህብረት፣ የአፍሪቃ ልማት ባንክ፤ አፍሪቃ ኤኮኖሚ ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአፍሪቃ ቢሮ በጋራ ያወጡት ዘገባ የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት፤ የሴቶችን ፖለቲካዊ ውክልና በማሳደግ፤ የህጻናትና እናቶችን ሞት እንዲሁም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን በመቀነስ ረገድ «አስደናቂ ስኬት» አስመዝግበዋል ብሏል።
ለመሆኑ አፍሪቃውያኑ ከምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች የተወሰኑ ዒላማዎችን ማሳካት ለመቻላቸው ምክንያቶቹ ምንድናቸው? ኢኑቺ ካምዌንዶ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአፍሪቃ ቢሮ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው።
«የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አንዱና ዋንኛው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና አመራር ነው። በእነዚህ ግቦች የተሻለ ስኬት በተመዘገበባቸው አገሮች በመንግስት በኩል አገራዊ የባለቤትነት ስሜት አለ። ይህ የባለቤትነት ስሜት በተግባር ላይ ባሉት አገራዊ ፕሮግራሞች ውስጥ እንዲካተት ያግዛል። ለምሳሌ በሩዋንዳ ለጾታ እኩልነት በተለይም የሴቶችን የፖለቲካ ውክልና ለማሳደግ የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነትና አመራር አስተዋጽዖው ከፍተኛ ነው። ለዚያም ነው በሩዋንዳ ፓርላማ ሴቶች አብላጫውን መቀመጫ ያገኙት።»

Schwangere Frauen in Äthiopien
ምስል Getty Images


በዘገባው መሠረት ጋምቢያ ከጎርጎሮሳዊው 1990-2010 ዓ.ም. ባሉት አመታት ድህነትን 32 በመቶ መቀነስ ችላለች። ኢትዮጵያ ለግብርና ትኩረት በመስጠትና የገጠር አኗኗርን በማሻሻል ድህነትን በአንድ ሶስተኛ በመቀነስ ከምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች ስኬት ማስመዝገቧ ተገልጧል። በዚህም ኢትዮጵያ ድህነት በ40 በመቶ ከቀነሰባቸው ሴኔጋል፣ ዩጋንዳ፤ ሞሪታኒያ፤ ጋና፤ ኒጀር፤ ካሜሩን እና ማሊ ተርታ ተመድባለች። ግብጽ፤ ደቡብ አፍሪቃ፤ ቦትስዋና፤ ጊኒ፤ ስዋዚላንድና ናሚቢያ ከጎርጎሮሳዊው 1990 ዓ.ም. ጀምሮ ድህነት በ50 በመቶ የቀነሰባቸው ተብለዋል።


በኒጀር የጎልማሳ ወንዶች የትምህርት አገልግሎት ባሎች በሴቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና፤ የቤተሰብ ምጣኔና ለጾታ እኩልነት አጋር እንዲሆኑ በማስቻሉ ዘገባው ከአህጉሪቱ ስኬቶች ተርታ መድቦታል። በችግኝ ተከላ የደን ሽፋኗን በስድስት በመቶ ያሳደገችው ኬፕ ቬርዴ በአካባቢ ጥበቃ ይበል የሚያሰኝ ሥራ ሠርታለች ተብሏል።


ከጎርጎሮሳዊው 2015 እስከ 2018 ዓ.ም. ባሉት አመታት ለአፍሪቃ የሚያስፈልገው የልማት እርዳታ ሊቀንስ እንደሚችል ዘገባው አትቷል። የልማት እርዳታው መጠን በአማካኝ በዓመት 47 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል። ይህ የልማት እርዳታ ጉዳይ በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች በአፍሪቃ ከገጠሙት ችግሮች አንዱ መሆኑን ኢኑቺ ካምዌንዶ ተናግረዋል።
«ለምዕተ አመቱ የልማት ግቦች የሚያስፈልገው ገንዘብ ችግር እንደነበር ሁላችንም እንስማማለን። የምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች ያደጉት አገሮች ከአመታዊ የምርት መጠናቸው 0.7 በመቶ ለማዋጣት ቃል በገቡት የልማት እርዳታ ላይ ጥገኛ ነበር። እሱም ቃል በተገባው መሠረት አልመጣም። »

Verbesserung der Gesundheitsversorgung der Mütter Millennium Development Goals
ምስል picture-alliance/dpa


ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ወቅት በርካታ የአፍሪቃ አገሮች በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች ያላቸውን አፈጻጸም ለመፈተሽ የሚያስችል የመረጃ አያያዝ አለመኖር ከፍተኛ ችግር መሆኑን ኢኑቺ ካምዌንዶ ተናግረዋል።
ዘገባው የምግብ ዋስትናን ጨምሮ በአፍሪቃ መፍትሄ ያጡ ዘላቂ ችግሮችንም ጠቃቅሷል። ከጎርጎሮሳዊው 2011 እስከ 2013 ዓ.ም. ባሉት አመታት 25 በመቶ አፍሪቃውያን የረሐብና የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር ተፈታትኗቸዋል። ለዚህም ግጭት፤ድርቅና የጎርፍ መጥለቅለቅ በመንስዔነት ተቀምጠዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ