1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል በኢትዮጵያ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2007

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ለሚካሄደው የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ እስካሁን 60 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳታፊነት የምርጫ ምልክቶቻቸውን መውሰዳቸውን እና ከጥር 1 እስከ የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት 42 ቀናት ከ33 ሚሊዮን በላይ መራጮች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1EFGY
a1.
ምስል Yohannes Gebereegziabher

በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መዝገብ በህጋዊነት ከተመዘገቡት 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ምህዳሩ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉት መካከል ለወርሃ ግንቦቱ ምርጫ ስጋት አለን የሚሉ አልጠፉም።

በአምስት አመት አንድ ጊዜ ወርሃ ግንቦት የኢትዮጵያ ፓለቲካና ፖለቲከኞችን ትኩረት ይስባል። ያነቃቃል። ያፋጥጣል። ሁሉም ነገር እንዲህ እንደ ዘንድሮ ገና ግንቦት ከመድረሱ በፊት ተጀምሮ ከግንቦት በኋላም ይዘልቃል። ካሁን ቀደም የተካሄዱት አራት የኢትዮጵያ ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎች አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ያሉ ነበሩ። እንዳጀማመሩ ፍጻሜው ያላማረው የ1997ቱ ምርጫ እና ለአንድ ተቃዋሚ እና ለአንድ የግል ተወዳዳሪ ብቻ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር የሰጠው የ2002 ምርጫ ለከፍታና ዝቅታው ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

Büro des National Electoral Board of Ethiopia NEBE
ምስል DW

በአንድ ወገን ቁጥጥር ስር ያልወደቀ፤ግልጽና ፍትሃዊ የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት ለመመስረት ለሚታገሉ መንግስታት ሁሌም ፈተና መሆኑን አለም አቀፍ የምርጫ፤ዴሞክራሲ እና ደህንነት ተቋም(Global Commission on Elections, Democracy and Security) ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ አመት ያወጣው ዘገባ ያትታል። በዚህ ተቋም ዘገባ መሰረት የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል ፍትሃዊነት ሲያጣ ፖለቲካዊ እኩልነትን ያጎድላል፤ለምርጫ ማጭበርበር ያጋልጣል፤መራጮች በምርጫው ላይ የሚኖራቸውን መተማመንም ያሳጣል። በኢትዮጵያ የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀትን ለፖለቲካዊ ፓርቲዎች ማከፋፈል ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ስልጣን ነው። ለዘንድሮ ምርጫ ማስፈጸሚያ የሚደረገውን የበጀት ክፍፍል አስመልክቶ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉን አቶ ደምሰው በንቲ የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይናገራሉ።

«መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ የክፍፍል ቀመር ላይ ከሃገር አቀፍ እና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ነው ውይይት የተካሄደው። ይህ የገንዘብ ድጋፍ ቀመሩ የሚወጣበት መርሆዎች አሉት። እነዚህ መርሆዎች የእኩልነት መርህ እና የፍትሃዊነት መስፈርት ዋንኞቹ ናቸው። የእኩልነት መስፈርት የሚባለው መመዘኛውን አሟልቶ በጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ የእኩልነት መርህን ተመስርቶ ድጋፍ ማድረግ የሚቻልበት ነው። ፍትሃዊነት የሚባለው ደግሞ ከዚህ ቀደም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤት ባለው መቀመጫ ብዛት የሚከፋፈል ነው። ባቀረቡት እጩ ብዛት ድጋፍ የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታም አለ።እንደዚሁም ሴት እጩዎችን ለሚያቀርቡም ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታም አለ።»

Addis Abeba Äthiopien Wahlen
ምስል Yohannes Gebereegziabher

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩ ተወዳዳሪዎች አላማቸቸውን፤አማራጭ ሃሳብና ግባቸውን ለመራጮች ለማስተዋወቅ ለመወያየትና ሃሳብ ለመቀበል በቂ የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት አስፈላጊ መሆኑን አለም አቀፍ የምርጫ፤ዴሞክራሲ እና ደህንነት ተቋም ያትታል።የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል ላይ በተደረገው ውይይት ከተካፈሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ወክለው የውጭ ጉዳይ ሃላፊው አቶ ዳንኤል ተፈራ ተሳታፊ ነበሩ። አቶ ዳንኤል አሁን በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የቀረበው የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል ቀመር ለገዢው ፓርቲ ያደላ ነው ባይ ናቸው።

«ያቀረቡት የገንዘብ አከፋፈል መስፈርት በምንም አይነት ተቀባይነት ያለው አይደለም አድሎአዊ ነው ብለን ተናግረናል። ይህን ያልንበት ምክንያት ሴት እጩዎችን በሚመለከት የቀረበው 10 በመቶ ውጪ ያሉት ኢ-ፍትሃዊ ናቸው።በተገቢው መንገድ ፓርቲዎችንና አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የተሰራ አይደለም ብለን ተቃውሟችንን ገልጸናል። በተለይም የፍትሃዊነት መስፈር ብለው ያስቀመጡት 55% አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ 99.6% አሸንፊያለሁ ብሎ ፓርላማ ባለበት አጠቃላይ የክልል ምክር ቤቶችን ጠቅልሎ በያዘበት ሁኔታ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን ታሳቢ ሳይደረግ 55% ብሎ መመደቡ ኢህአዴግን ለማንገስ የሚደረግ ሩጫ ነው ብለን ነግረናቸዋል።»

ሌላው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል ውይይት ላይ ተሳትፎ የነበረ ቢሆንም ተወካዩ አቋርጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል። የሰማያዊ ፓርቲ የየጥናትና ስትራቴጂክ ክፍል ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ ፓርቲያቸው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም የሚል አቋም መያዙን ያስረዳሉ። እንደ አቶ ጌታነህ አባባል የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍሉም ቢሆን ፍትሃዊ አይደለም።

በምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል ውይይቱ ላይ የሃሳብ ልዩነት እንደነበር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ይስማማሉ። እንደ አቶ ደምሰው በንቲ ከሆነ በውይይቱ ላይ የተነሱ ሃሳቦችን በመመልከት የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል እስከ ሁለት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይፋ ይሆናል።

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ 450 ተወዳዳሪዎችን ለማቅረብ መዘጋጀቱን የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ተናግረዋል። አቶ ዳንኤል ለምርጫ ዝግጅት የሚደረገው የበጀት ክፍፍል ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የእጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት ሊሆን እንደሚገባ ያስረዳሉ።

An Ethiopian woman
ምስል AP

አራተኛውን አገራዊ ምርጫ 99.6 በመቶ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባላት ቁጥር፤አደረጃጀትና አቅምን በመገንባት ረገድ ሰፊ ልዩነት እንደሚታይባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ደመቀ አጭሶ ያስረዳሉ። እንደ ዶክተር ደመቀ ከሆነ ለምርጫ ማስፈጸሚያ መንግስት ከሚያቀርበው የበጀት ድጋፍ ኢ-ፍትሃዊነት ይልቅ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በህዝብ ዘንድ መስራት የነበረባቸውን ስራ አለመስራታቸው ፈተና ይሆንባቸዋል።

ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የምርጫ ዘመቻ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ይጠቁማል። 60 የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ይወዳደራሉ። ይህ ቁጥር ምርጫ ብቻ ሲመጣ ብቅ የሚሉትን ይጨምራል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ