1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ እና ቡሩንዲ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 5 2008

የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ጉባዔ ባለፈው ሀሙስ፣ መስከረም ስምንት፣ 2016 ዓም በታንዛንያ የዳሬ ሰላም ከተማ ጉባዔ አካሄዱ። የኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳ፣ ርዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች ጉባዔ ካካባቢው የኤኮኖሚ ጉዳይ ባለፈም በተለይ በቡሩንዲ በቀጠለው ውዝግብ እና መፍትሔው ፍለጋ ጉዳይም ላይ አትኩሮ ነበር።

https://p.dw.com/p/1JzUm
Karte Ostafrikanische Gemeinschaft Englisch

[No title]

በዳሬ ሰላም በተካሄደው የአንድ ቀኑ ጉባዔ የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት መሪዎች የቡሩንዲን ውዝግብ ለማብቃት በተጀመረው ጥረት ላይ እስከዛሬ የተደረገውን ያን ያህል አበረታቺ ያልሆነውን ሂደት በተመለከተ የቀረበ አንድ ዘገባ አድምጠዋል። ይህንኑ ዘገባ በወቅቱ የሸምጋይነቱን ሚና የያዙት የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚደንት ቤንጃሚን ምካፓ ነበሩ ለመሪዎቹ ያቀረቡት። በዳሬ ሰላሙ የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ያልተገኙ ሲሆን፣ እርሳቸውን እንዲወክሉ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚንስትራቸውን አላ ኤሜ ኒያሚትዌ ወደ ስብሰባው ልከዋል።
እንደሚታወቀው፣ ካለፈው አንድ ዓመት በላይ ወዲህ መቋጫ ባለገኘ ቀውስ ወስጥ የምትገኘው የቡሩንዲ ዜጎች ሰላም እና መረጋጋት የሚወርድበትን ቀን ለማየት ጓጉተዋል። ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ እና ተወዳድረውም አሸነፍኩ ካሉበት ከሚያዝያ እና ሀምሌ፣ 2015 ዓም ወዲህ በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው ቀውስ ከ450 የሚበልጡ ሰዎች ሞተዋል፣ ብዙዎችም ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል።
በቡሩንዲን ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ ቀደም ሲል በአሩሻ ፣ ታንዛንያ በምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ ሸምጋይነት የተካሄዱ ሁለት የውይይት ዙሮች፣ የመንግሥት ተቃዋሚዎች የመብት ጥሰት ፈፅመዋል ከሚሉዋቸው የመንግሥት ተወካዮች ጋር፣ በሌላ በኩል የቡሩንዲ መንግሥት ደግሞ ፕሬዚደንቱን ከስልጣን ለማውረድ ተሞክሮ በከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ሴራ ላይ እጃቸው አለበት ከሚሉዋቸው ወገኖች ጋር ለመደራደር ባልፈለጉበት ድርጊት ውጤት ሳያስገኙ መቅረታቸው ይታወሳል፣ እና በዚህ ሰበብ ብዙዎቹ የቡሩንዲ ዜጎች የአንድ ቀኑ የዳሬ ሰላም ጉባዔ ውጤታማ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳልነበራቸው ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
አፍሪቃውያን የሀገር መሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ በስልጣን በሚቆዩበት ሕገ ወጥ ድርጊት ሰበብ የሚፈጠር ውዝግብ ከሚፈቀድላቸው ጊዜ በላይ በስልጣን ለመቆየት እያሉ ሕገ መንግሥቱን በቀየሩ ፕሬዚደንቶች መፍትሔ እንደማይገኝለት ነው በመዲናይቱ ቡጁምቡራ የሚገኙ አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ያስታወቁት።
« እውነቱን ለመናገር፣ ከጉባዔው ምንም አልጠብቅም። ጉባዔ አዎንታዊ ውጤት አያስገኝም። እንደምታውቁት፣ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት በጉባዔው አልተካፈሉም። ወደዳሬሰላም ጉባዔ የላኩት አንድ ባለስልጣናቸውን ነው። የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔርን ወይም ባጠቃላይ በአፍሪቃ ያሉትን መሪዎች ስንመለከት እና አነጋጋሪው ጉዳይ ሶስተኛ የስልጣን ዘመን መሆኑን ስንገነዘብ፣ ለቡሩንዲ ቀውስ መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት የጀመሩት ራሳቸው ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን አብቅተው ወደ ሶስተኛው የተሸጋገሩ ናቸው። ስለዚህ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛን አሁን የጀመሩትን ሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንዲያቋርጡ እና ስልጣናቸውን እንዲተው ለማግባባት አይችሉም። »
ያለፉት ሁለት የቡሩንዲ የውይይት ዙሮች ካላንዳች የረባ ውጤት መበተናቸውን የጠቀሱ በመዲናይቱ የሚገኙ የአንድ መደብር ባለቤትም የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚደንት ቤንጃሚን ምካፓ ያቀረቡት ዘገባ ቅር የሚያሰኝ እንደነበር ገልጾዋል።
« አስታውሳለሁ፣ የሸምጋይነቱን ሚና የያዙት ምካፓ በመጨረሻው በአሩሻ፣ ታንዛንያ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በዚያ የተገኙት ተቀናቃኞቹ የቡሩንዲ ቡድኖች የሚሉትን ለማድመጥ ነበር በዋነኝነት የሄዱት። ግን ሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች ባንድ ላይ ተቀምጠው ለመነጋገር እንኳን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ኃላፊነት የተሰጣቸው ምካፓ ተልዕኮ ሳይሳካ ቀርቷል። እና ተቀናቃኞቹ ወገኖች አሁንም አብረው ቁጭ ብለው ለመነጋገር ፈቃደኛ እስካሆኑ ድረስ እኒሁ ሸምጋይ ምን ዓይነት ዘገባ ሊያቀርቡ ይችላሉ በሚል ነበር ራሴን የጠየቅሁት። »
ይሁንና፣ የቡሩንዲ የወደፊት እጣ ፈንታን በተመለከተ በአሩሻ የተጀመረው የሰላም ውይይት በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ማውረድ የሚቻልበትን መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችል ብቸኛው አማራጭ ነው በማለት በሀገሪቱ ብሩሕ ጊዜ የሚመጣበትን ጊዜ በተስፋ የሚጠብቁ አንዳንዶች አልጠፉም።
« ተስፋ አድርጌአለሁ። እርግጥ ነው፣ ቤንጃሚን ምካፓ የቡሩንዲን መንግሥት እና ተቃዋሚዎችን ለማቀራረብ ባለፉት ጊዚያት ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም። ይሁንና፣ በአሁኑ ጊዜ፣ ከምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር ጋር ባንድነት ለቡሩንዲ ሰላም የሚያወርድ እና ቡሩንዲ ለተደቀነባት ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስም መፍትሔ የሚያስገኙ አዳዲስ ሀሳቦችን ሊያቀርቡ ይችላሉ ብየ አምናለሁ። »
ሌላው የመዲናይቱ ነዋሪም ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያሰማው።
« በጉባዔው ላይ የተካፈሉት የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት መሪዎች በጠቅላላ በሳል ናቸው ብየ ስለማስብ ደህና ውጤት ይገኛል የሚል ትፅቢት አለኝ። በቡሩንዲ የቀጠለውን ውዝግብ ለማብቃት የሚያስችለውን መፍትሔ በመወያየት እና በመማከር እንደሚያስገኙ አሁን ተስፋ አድርጊያለሁ። »
ይሁን እንጂ፣ ውይይት እና ምክክር ብቻውን ለቡሩንዲ ቀውስ መፍትሔ ማስገኘቱን የሚጠራጠሩ ወገኖች፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት መሪዎች እና ሸምጋዮ፣ ቤንጃሚን ምካፓ በቡሩንዲ ተቀናቃኞች ላይ ጫና ሊያሳርፉ እንደሚገባ ይናገራሉ።
« ሸምጋዮቹ የቡሩንዲ መንግሥት እና የተቃዋሚ ቡድኖች መድረክ ፣ በምህፃሩ የ«ሴናርድ» ተወካዮች በመፍትሔ መሻቱ ድርድር ላይ አብረዋቸው እንዲወያዩ በነዚሁ ወገኖች ላይ ግፊታቸውን ማጠናከር በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ አስፈላጊ ይሆናል። »
የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ ከአውሮጳ ህብረት ጋር በተደረሰ የንግድ ስምምነት ላይ የመከረ ሲሆን፣ ታንዛንያ እጎአ የፊታችን ጥቅምት አንድ፣ 2016 ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን ስምምነት ለጊዜው እንደማትፈርም አስታውቃለች። ኬንያ እና ርዋንዳ ስምምነቱን ቀደም ሲል ፈርመውታል፣ ይሁንና፣ የማህበረሰቡ አባል ሀገራት በጠቅላላ እስካልፈረሙት ድረስ ተግባራዊ ሊሆን ስለማይችል የስብሰባው ተሳታፊዎች ሁሉም እንዲፈርሙት በማሳሳብ ስብሰባቸውን አጠናቀዋል።

DEU Karte Burundi
Tansania - Flüchtlinge aus Burundi
ቤንጃሚን ምካፓምስል Getty Images/AFP/T. Karumba
Afrika Kenia Nairobi Benjamin Mkapa ehemaliger Präsident von Tanzania
የቡሩንዲ ስደተኞችምስል DW/K. Tiassou

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ