1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“የተነጠቀም ሆነ የሚነጠቅ ቦታ የለም”- የኦሮሚያ ክልል

ሐሙስ፣ መጋቢት 14 2009

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ይበጃሉ ያላቸውን ተከታታይ እርምጃዎች እየወሰደ ነዉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ በግል ባለሀብቶች ተይዘው የነበሩ የማዕድን ቦታዎችን ለስራ አጥ ወጣቶች እንዲሰጥ ማድረጉ ነው፡፡ በክልሉ ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃዎችን ከተደራጁ ወጣቶች እንዲገዙ የሚያስገድድ ውልም አስፈርሟቸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2Zq9C
Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

Oromia region take over mining quarries - MP3-Stereo

የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ከተለመደው «ወጣ ያሉ» እና «ደፋር» አካሄዶች መምረጣቸው ያነጋግር ይዟል፡፡ እነዚህ አካሄዶች ትኩረት ያደረጉት ክልሉን ባለፈው ዓመት በናጠው ህዝባዊ አመጽ ዋና ተሳታፊዎች በነበሩ ወጣቶች ላይ ነው፡፡ ወጣቱ ከአካባቢው ሀብት ተጠቃሚ ካልሆነ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ በክልሉ ባሉ የግል ኢንቨስትመንቶች ላይ ከደረሱ ጥቃቶች ጋር በግልጽ ሲያይዙት ታይተዋል፡፡

በመፍትሄነት ከወሰዷቸው እርምጃዎች አንዱ “ምንም እሴት የማይጨመርባቸው” ያሏቸውን የማዕድን ማምረቻዎች ከግል ባለሀብቶች ወስዶ ለተደራጁ ወጣቶች ማስተላለፍ ነው፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም የምርት ግብዓቶችን ከወጣቶች እንዲገዙ ስምምነት አስፈርመዋቸዋል፡፡ ትናንት መጋቢት 13 መንግስታዊው ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር አዲስ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እነዚህን እርምጃዎች የሚወስደዉ በዚህ ዓመት ብቻ በክልሉ ላሉ 1.2 ሚሊዮን ስራ አጥ ወጣቶች ስራ ለመፍጠር ከያዘው ዕቅድ ተነስቶ እንደሆነ የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አወሉ አብዲ ይናገራሉ፡፡

“የስራ ዕድል ከሚፈጠርባቸው መስኮች አንዱ ማዕድን ነው፡፡ ማዕድን ምንድነው በመሰረቱ ተቆፍሮ [ከወጣ በኋላ] ፋብሪካ ውስጥ የሚገባ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ እሴት የሚጨመርበት አይደለም፡፡ ማዕድኑ ከምንጩ ላይ ባለው ብቻ ጥቃቅን እና አነስተኛ [ማህበራት] አደራጅተን አነርሱ የመነሻ ገንዘብ እያገኙ የራሳቸውን ቢዝነስ የሚፈጥሩበት ሁኔታ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ ጥቃቅኖች ጥሬ ዕቃ እንዲያቀርቡላቸው ከፋብሪካዎች ጋር ተሰማምተናል፡፡ ከሙገርም፣ ከደርባም፣ ከዳንጎቴም ሌሎች ክልሉ ውስጥም ካሉ 18 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ለስራ ዕድል ፈጠራ ቁጭ ብለን ተስማምተናል፡፡ እነርሱም ‘ይህ ችግር ይመለከተናል፤ እኛም ችግሩን መካፈል አለብን’ ብለው ተሰማምተው በጋራ የተደረገ ነገር ነው” ይላሉ፡፡

Äthiopien Sabata Wirtschaft Arbeitsmarkt
ምስል DW/M. Y. Bula

አቶ አወሉ ይህን ይበሉ እንጂ የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ስምምነቱን እንዲፈጽሙ እንደተነገራቸውና ሁሉም የሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው ተዘግቧል፡፡ የሲሚንቶ ግብዓቶች አቅርቦት ወደ ተደራጁ ወጣቶች መዞር በሲሚንቶ ምርት ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጥርም አስግቷል፡፡ ከፋብሪካዎቹ ሌላ እንደ አሸዋ፣ ጠጠር እና ኖራ ያሉ ማዕድኖቹን ያመርቱ የነበሩ ባለሀብቶች “ማምረቻ ቦታዎቹን ልንነጠቅ ነው” የሚል አቤቱታ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡ “ሀብት የማፍራት ህገመንግስታዊ መብታችን ተጥሷል” ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

ቅሬታዎቹን ለአቶ አወሉ አንስተንላቸው ነበር፡፡ ከባለሀብቶች “የተነጠቀም ሆነ የሚነጠቅ ቦታ የለም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

“አንደኛ ይሄ ማዕድን የሚባለው ነገር የጋራ ሀብት ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚበለጽጉበት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ምስራቅ ሸዋ አካበቢ ያለውን ማዕድን ሶስት፣ አራት ባለሀብቶች የሚባሉ ደላሎች ለብቻ ተቆጣጥረው እንደሚጠቀሙበት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ሁለተኛ ማሽን አልነካንም፡፡ ድንጋይ የሚፈጩ ማሽኖች አካባቢ ድንጋይ አሁንም እነርሱ ናቸው የሚፈጩት፡፡ ጥሬውን ድንጋይ ግን ልጆቹ አውጥተው ለእነርሱ ያቀርባሉ፡፡ እነርሱ ደግሞ ተቀብለው ይፈጫሉ፡፡ እሴት ጨምረው ይሸጣሉ፡፡ ስራ አጡ፣ ወጣቱ ይህን ነገር ሰብስቦ ቢሸጥ ምንድነው ወንጀሉ? ምንም ወንጀል የለውም፡፡ የፍትሃዊነት፣ የእኩልነት፣ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ደግሞ በጋራ ተሰማምተን ከባለሀብቶቹ ጋርም ያለምንም ልዩነት ነው የተለያየነው፡፡ ስለዚህ ይህን በጎን የሚያቀርብ አካል ካለ በራሱ ችግር ያለበት አካል ስለሆነ ራሱን በዚያ መልኩ ቢያርም ጥሩ ነው” ሲሉ አቶ አወል ያስጠንቅቃሉ፡፡

ስለ ጉዳዩ በፌስ ቡክ ገጻችን እና በዋትስ አፕ አድራሻችን አስተያየታቸውን ያጋሩን  ተከታታዮቻችን ለክልሉ እርምጃ አዎንታዊ አመለካከት አላቸው፡፡ ተግባራዊነቱን የሚጠራጠሩ  እንዳሉ ሁሉ እርምጃዎቹን የተቹም በርካቶች ናቸው፡፡ ተስፋዬ ደሳለኝ የተባሉ ተከታታይ“ወጣቶች ከአካባቢያቸው ሐብት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገቢ ነው፡፡ ችግሩ የሚመስለኝ መጀመሪያውኑ ከማደራጀት ያገዳቸው ማን አለ የሚለው ይመስለኛል፡፡ የ25 ዓመት ጥፋትን በችኮላ ማስተካከል አይቻልም” ብለዋል፡፡ ጌች ድሪባ ለታ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው “ልማት አንዱን ሀብታም አንዱን ድሀ ማድረግ ነው ወይስ ሁሉንም የማከለ መሆን አለበት?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ