1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21 2009

ስርጭቱን ከውጭ ሀገር የሚያከናውነው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዐረቢኛ ቋንቋ ስርጭት ሊጀምር እንደሆነ መገለጡ የሳምንቱ ዋነኛ መነጋገሪያ ርእስ ሆኖ ቆይቷል። ቢቢሲ በ2016 በትዊተር ሰፊ ሽፋን ያገኙ ካላቸው የአፍሪቃ ጉዳዮች ውስጥ የኢትዮጵያን ጉዳይ ዘንድሮም አካቷል።

https://p.dw.com/p/2V219
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በዐረቢኛ ቋንቋ ሥርጭት ሊጀምር ነው የመባሉ ዜና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙዎችን አነጋግሯል። ቢቢሲ በ2016 በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት የተሰራጩ እና ውይይት የተደረገባቸው ካላቸው የአፍሪቃ ጉዳዮች መካከል የኦሮሞ እና የአማራ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደሚመደቡ ያስታወቀው በዚሁ ሳምንት ነው።

ስርጭቱን ከውጭ ሀገር የሚያስተላልፈው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፦ በዐረቢኛ ቋንቋ ተጨማሪ ስርጭት ሊያከናውን እንደሆነ የመገለጡ ዜና በርካቶችን አነጋግሯል። ጣቢያው በዐረቢኛ ብቻ አይደለም በሌሎችም ቋንቋዎች ስርጭት ማከናወኑ ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም ሲሉ አስተያየት የሰጡ በርካቶች ናቸው።

በዛው መጠን ደግሞ ጣቢያው በዐረቢኛ ቋንቋ ከግብጽ ስርጭት ለመጀመር ማሰቡ ከጀርባው አንዳች ተልእኮ ቢኖረው ነው ሲሉ ጥርጣሬያቸውን እንዲሁም ድምዳሜያቸውን ያሰሙም ነበሩ። ከሁለቱም ወገን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

ዕውቅና ካላቸው የኦሮሞ የፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል ግርማ ጉተማ በትዊተር ገጹ ባስተላለፈው መልእክት፦ «ኦ ኤም ኤን ዓረብኛ በጥር 2017 ይጀምራል» ብሏል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የአንድ ደቂቃ የቴሌቪዥን ማስታወቂያንም አያይዞ አቅርቧል።

ኤፍሬም አደባባይ በፌስቡክ ያቀረበው ጽሑፍ  ሰበብ አያስፈልግም የሚል እንድምታ ይዟል። «በእርግጥ በአረብኛ ማስተላለፉ «የአጋጣሚ ነገር» ነው፣ «አረብኛ ከዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች አንዱ ስለሆነ» ነው የሚለው አያስኬድም። ሻቢያ አረብኛን ሲጠቀምበት የነበረበት ምክንያት እና አሁን ደግሞ የኦ.ኤም.ኤን ኃላፊዎች ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱበት ምክንያት ፖለቲካዊ አንድምታው እንደ ፀሐይ ግልጽ ነው። በደፈናው አረብኛን እና እስልምናን አንድ አድርገው በመውሰድ በትንሹ ቱግ የሚሉ አንዳንድ ሰዎችን ላለማስከፋት አብዛኛው «ፖለቲከኛ» ዝም የሚልበት ምክንያቱ ቢገባንም በኦሮሞ ትግል ሰበብ አረባዊነት ለማስፋፋት ሲደረግ የኖረውን የቆየ ሙከራ ማስታወስ ግድ ይለናል። ይህ ጠጋ ጠጋ የቆየው ነገር መገለጡን ከማስረዳት ያለፈ ነገር የለውም። የኦሮሞ ትግል ተጭኖበት የቆየው አንዱ ችግር «ኦሮሙማ» እና «እስላሙማ» እጅና ጓንት ሆነው መቆየታቸው ነው» ብሏል።

አቡኪ አቡኪ አቡኪ ፌስቡክ ላይ፦ «አረቢኛ በዓለማችን ቡዙ ተናጋሪ ካላቸው ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው» በማለት ይጀምራል፡፡ ቢቢሲ እና አልጀዚራን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ የሚዲያ ተቋማትም የአረቢኛ ቋንቋ ስርጭት እንዳላቸው በመጥቀስ፤ «እነዚህ የሚዲያ ተቋማት የአረቢኛ ቋንቋን መጠቀማቸው ከእስልምና ጋር የሚያገናኘው ምክንያት የለም» የሚል መልእክት አስነብቧል፡፡ «omn አረቢኛን መጠቀሙ ከሃይማኖቱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም» በማለት «ሃይማኖትና ቋንቋን ለይተን ማየት ያለብን ይመስለኛል» ሲል አክሏል፡

ሄለን ጋዲሳ ዳቢ በትዊተር ገጿ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በኦሮሚኛ ቋንቋ «አስደሳች ዜና» ሲል በትዊተር ያቀረበውን መልእክት በማያያዝ፦ «omn በቅርቡ በዓረቢኛ» ስትል ጽፋለች።

Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ኢሕአዴግን በትጋት ከሚደግፉ ሰዎች መካከል  አብዱልባሲጥ አብዱሰመድ በፌስቡክ ገጹ፦ «አረቡ አለም ደግፎት የወደቀ፥ የከሸፈ እና የተፈረካከስ ትግል እንደሆነ እንጂ ሊያልፍለት ተስፋ የነበረው ትግል እንኳ በ20ኛው እና በ21ኛው ክፈለ ዘመን በምድር ላይ አልታየም» ሲል ጽፏል። ከሶማሊያአንስቶ የተለያዩ የዓረብ ሃገራትን በመጥቀስ «በሃይማኖት መነገድ» ብሏል። ኦ ኤም ኤን ከካይሮ ሊጀምር ያቀደው የዓረቢኛ ቋንቋ ስርጭት ዓላማ አደገኛ መሆኑን ገልጧል።

ቢኒያም ሐብታሙ በፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው አጠር ያለ አስተያየት ደግሞ፦ «'ትክክለኛው' ኦሮሞ ሙስሊም ነው በተባለበት አፍ፣ 'ትክክለኛው' ኦሮሞ አረብኛ ተናጋሪ ነው ሳይሉ ይቀሩ ይሆን?» የሚል ነው።

ሌሊሳ ሌንጮ ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስነበበው ጽሑፍ፦ «ለመሆኑ ዓረቢኛ መርሐ-ግብር የመጀመር ዕቅዱን የቀፈቀፈው ማነው?» በሚል ይጠይቃል። ዕቅዱንም «በብዥታ የተጋረደ» ሲል ይተቸዋል።

ዘርአያቆብ ጌታቸው ጉዲና በፌስቡክ ባስተላለፈው መልእክት፦ «ባለፈው ቢቢሲ የሬዲዮ ስርጭት በኦሮምኛ አማርኛ እና ትግርኛ ፕሮግራም ሊጀምር መሆኑን የተዘገበበት ወቅት ግብፅ ውስጥ ኦሮምኛ ተናጋሪ አለ ብለው ተፅፎ አንብበን አጂብ ብለን ባላየ ባልሰም ነገሩን ዋጥ አርገን ጭጭ ብለን አለፍነው» ይላል።  OMN በአረብኛ ቋንቋ ስርጭት ሊጀምር መሆኑን መስማቱ በግርምት እንዳጫረበትም ይገልጣል። «በአሁኑ ሰአት ዓረብኛን ከሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ ለምን ማስቀደም አስፈለ?» ሲል ሌላ ጥያቄ አስፍሯል። ሳባ ዮሐንስ « ይሄን ነበር መንግስት ሲናገረው የነበረው፤ የግብፅ ተላላኪ ሲል ታሾፍ ነበር» ብላለች።

ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ በፌስቡክ ያስነበበው ጽሑፍ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ማሠራጪያ ጣቢያዎች በዐረቢኛ ቋንቋ ይተላለፉ የነበሩ ስርጭቶች ዓላማ እና ግብን በማብራራት ይጀምራል። «በአረብኛ ቋንቋ የሚተላለፈውና ይተላለፍ የነበረው ስርጭት ለኢትዮጵያውያን አልነበረም/ አይደለም» በሚል ርእስ የቀረበው የአርጋው ጽሑፍ ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ ዐረቢኛ ቋንቋን የተጠቀሙበት የውጭ ዜጎችን ዒላማ በማድረግ እንደሆነ ይገልጣል።

«ዐረብኛን ለኢትዮጵያውያን አድማጮች በማቅረብ OMN የመጀመሪያው ይሆናል» ያለው አርጋው «ግር የሚያሰኘውና ለጥርጣሬ በር የሚከፍተው ይህን ስርጭት ለመጀመር የተመረጠበት ወቅትና ቦታ (ካይሮ መሆኑ) ነው። ግብፅ ለዓመታት በአማርኛ የሚተላለፍና ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ የራዲዮ ፕሮግራም ነበራት። የተሳካ አይመስለኝም። አሁን ስለመኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም። በርካታ የአረብ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ ሀይማኖታዊና ሌሎች ስርጭቶችን በሳተላይት ያካሂዳሉ። ይዘታቸውን ለመዘርዘር ይቸግረኛል። ሚዲያን ለጂኦ-ፖለቲካል ፍላጎት ማሰፈፀሚያ ማዋል በሰፈሩ አዲስ ነገር አይደለም። የOMN አዲሱ ስርጭት በአረብ ሀገር የተደገፈ ነው የሚለው ስሞታ እውነት ከሆነ አላማው አንድና አንድ ነው፣ የራስን ጂኦ-ፖለቲካል ጥቅም ማስጠበቅ። እንዴት? እነሱ በሀገራቸው የሚዋጉትን ፅንፈኝነት በመስበክ። የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ይህን ጨዋታ ጠንቅቆ ያውቃል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ OMN ለምን አሁን አረቢኛ ስርጭት ለመጀመር ወሰነ? የሚለውን ከራሱ በሰተቀር የሚያስረዳ ሊኖር አይችልም» ሲል ሐሳቡን አጠቃሏል።

Symbolbild Facebook Social Media Fake News
ምስል picture-alliance/dpa/J. Büttner

ቢቢሲ ዓለም አቀፍ የዜና አውታር በጎርጎሪዮሱ 2016 ትዊተር ላይ ጎልተው መነጋገሪያ የሆኑ ሃሽ ታግ የተደረጉ ርእሰ-ጉዳዮችን በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል። ከርእሰ-ጉዳዮቹ መካከል የኦሮሞ እና የአማራ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች  በዋነኛነት ይገኙበታል።  

ቢቢሲ «ለታላቅ የሙዚቃ ሰው ኅልፈት ሐዘንን ለመግለጥ፤ ፕሬዚዳንቶች ላይ ለመሳለቅ ወይንም የተቃውሞ ንቅናቄዎችን ለመጀመር አፍሪቃውያን ከምንጊዜውም በበለጠ በ2016 ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅመውበታል» ሲልም ጽፏል። ትዊተር የማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ላይ በኢንተርኔት አሠሣ በቀላሉ እንዲገኙ ምልክት ማለትም «ሃሽ ታግ» የተደረገላቸው ርእሰ ጉዳዮች እና ታሪኮች «እኚውላችሁ» ሲል ቢቢሲ ዘርዝሯል። ከዝርዝሮቹ መካከል የአማራ እና የኦሮሞ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ቁጥር  በማስመዝገብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ።

ኢትዮጵያን የሚመለከት ይዘት ያለው የትዊተር ሀሽታግ የቢቢሲን ቀልብ ሲስብ የመጀመሪያው አይደለም። ቢቢሲ የትዊተር አካሄዶችን በሚገመግምበት ገጹ በጎርጎሪዮሱ 2014 እና 2015 የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ይፈቱ በሚል በትዊተር የተከፈተው ዘመቻ ዓለም አቀፍ ትኩረት ስቦ እንደነበር ሰፋ ያለ ዘገባ ማስነበቡ ይታወሳል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ