1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የሙጋቤ መጨረሻ

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 2010

ግሬስ በአርባ አንድ ዓመት ታንሳቸዋለች።ግን ዉብነች።ጠቀለሏት-ጠቀለለቻቸዉ። አገቧት-አዘዘቻቸዉ።የተዋጉ፤የታሰሩ፤የቆሰሉ፤በአደባባይ የተሟገቱላትን ሐገር ከነሥልጣናቸዉን የመዉረስ ፍላጎትዋን ለመፈፀም ታማኞቻቸዉን እየካዱ ከስልጣን ያሽቀንጥሯቸዉ ገቡ።

https://p.dw.com/p/2nhUp
Zimbabwe Mugabe Rally
ምስል picture-alliance/AP Photo/T.Mukwazhi

NM - MP3-Stereo

የዚምባብዌ ጦር ሠራዊት እና ፖለቲከኞች ሐገሪቱን ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ከሚያመራ እርምጃ እንዲታቀቡ የአዉሮጳ እና የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች እና ድርጅቶች አሳሰቡ።ዚምባቡዌ እንዳትታበጥ ቀድመዉ ያሳሰቡት ደቡብ አፍሪቃ እና የአዉሮጳ ሕብረት ናቸዉ።ዛሬ ጠዋት ሐራሬ የሚገኙ የመንግስት ዋና ዋና ተቋማትን የተቆጣጠረዉ የሐገሪቱ ጦር ሠራዊት እርምጃዉ «ወንጀለኞችን ለማፅዳት» እንጂ መፈንቅለ መንግስት እንዳልሆነ አዛዡቹ አስታዉቀዉ ነበር።የዜምባቡዌ የረጅም ጊዜ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ለደቡብ አፍሪቃዉ አቻቸዉ በስልክ እንደተናገሩት ግን እሳቸዉ እና ባለቤታቸዉ መኖሪያ ቤታቸዉ ዉስጥ ታግተዋል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

ዚምባቡዌ፤ በዚሕ ስሟ ከተጠራች፤ ነፃ ሐገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ እሳቸዉን እንጂ ሌላ አታዉቅም።ሮበረት ጋብርኤል ሙጋቤ።እንደ መሪ እሳቸዉንና እሳቸዉን ብቻ የሚያዉቀዉ ዜጋቸዉ የዕድሜያቸዉን መግፋት እያነሳ-የተኪያቸዉን ማንነት ሲያጠያይቅ  አምና «እኔ የትሔጄ?» ጥያቄዉን በጥያቄ መለሱ-እየሳቁ።
                                    
«ለምን? አሁንም አለሁኝ።ለምንድነዉ ተተኪ የምትፈልጉት?መኖሬን እንድታዉቁ በቡጢ ልንርታችሁ?።» 
ዛሬም በርግጥ ታገቱ እንጂ አሉ።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎችን፤ የኢያንስሚዝ  ነጭ ገዢዎችን፤ የቄስ ፖለቲከኞችን፤ የጆሽዋንኮሞ ተከታዮችን፤ የጦር ጄኔራሎቻቸዉን፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፤ ምክትሎቻቸዉን ተራ በተራ እየደቆሱ «የዘረሩበት» ብልሐት፤ ያ ጠንካራ ክንዳቸዉም በርግጥ ዛሬ ዝሏል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት «አንዳንዴ ቆንጆዎችን ታያላሕ።ለናትሕ መላክ የሚገባሕን ገንዘብ እነሱ ላይ ታጠፋለሕ።መጨረሻ ላይ እንዲያዉ ምትሐት ወይም ጥንቆላ ያለዉን ኃይል ለመቀበል ትገደዳለሕ»  ብለዉ ነበር አንጋፋዉ የነፃነት አርበኛ።ሐበሻ «ሴት የላከዉ ሞት አይፈራ» እንደሚለዉ ዓይነት ማለታቸዉ ይሆን?አሉም አላሉ አደረጉት።
ጀግናዉ የነፃነት ተዋጊ፤ ለብሪታያ፤ለነጭ ገዢዎች፤ ለጥቁር አድርባዮች ያልተበገሩት ሙጋቤ በግሬስ ዉበት ተሸነፉ።ግሬስ በአርባ አንድ ዓመት ታንሳቸዋለች።ግን ዉብነች።ጠቀለሏት-ጠቀለለቻቸዉ። አገቧት-አዘዘቻቸዉ።የተዋጉ፤የታሰሩ፤የቆሰሉ፤በአደባባይ የተሟገቱላትን ሐገር ከነሥልጣናቸዉን የመዉረስ ፍላጎትዋን ለመፈፀም ታማኞቻቸዉን እየካዱ ከስልጣን ያሽቀንጥሯቸዉ ገቡ።
የግሬስን ተቀናቃኞች ከሥልጣን የማፅዳቱ እርምጃ ምክትል ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋዋጋ መድረሱ ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዋንጋ እና ለመሰሎቻቸዉ የ«ነግበኔ» ዓይነት ማስጠንቀቂያ ነበር።
ጄኔራሉ በርግጥ ሙጋቤ ኮትኩተዉ ያሳደጉ፤ሾመዉ የሸለሟቸዉ ታዛዣቸዉ ነበሩ።የግሬስን አልጋወራሽነት በተለይ ደግሞ የቅርብ ወዳጃቸዉ የምክትል ፕሬዝደንት ምናንጋዋ ከስልጣን መወገድ ፈፅሞ አልተቀበሉትም።ሙጋቤን በተዘዋዋሪ አስጠነቀቁ።የሙጋቤ ፓርቲ ፤ ጄኔራሉን «የሐገር ክሕደት ባሕሪ» በማለት መዉቀሱ-የሚቀጥለዉን እርምጃ ለማወቅ ጄኔራሉ ሁለቴ ማሰብ አልጠየቃቸዉም።የወታደር ደንቡ ሳይቀድሙ መቅደም ነዉ።«ቀጥል» አሉ ጦራቸዉን።ቀደሙ።ዛሬ ማለዳ የሐራሬን ፖለቲካዊ ሕልቅት በቀላሉ ፈጠረቋት።ከጄኔራላቸዉ አንዱን «በል» አሉትም።
                                     
«ለሕዝባችን እና ከድንበራችን ማዶ ላለዉ ዓለም በሙሉ በግልፅ ማስወቅ የምንፈልገዉ ይሕ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አለመሆኑን ነዉ።የዚምባቤዌ መከላከያ ኃይል የሚያደርገዉ መፍትሔ ካልተበጀለት ደም አፋሳሽ ብጥብጥ ሊያስከትል የሚችለዉን የሐገራችንን  ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማሕበራዊ ቀዉስን ማረጋጋት ነዉ።»
ሮበርት ሙጋቤ አሁንም የሐገሪቱ ፕሬዝደንት እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መሆናቸዉን ጦሩ አስታዉቋል።የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ እንዳሉት ግን አንጋፋዉ ፖለቲከኛ እና ባለቤታቸዉ ታግተዋል።የመንግሥት እንቅስቃሴም ቆሟል።ደቡብ አፍሪቃ የዚምባቡዌ ሕገ መንግሥት እንዲከበር አደራ ብላለች።መከላከያ ሚንስትሯንም ወደ ሐራሬ ልካለች።የአዉሮጳ ሕብረት ዜምባብዌዎች ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ መክሯል።
ዩናይትድ ስቴትስ ለዜምባብዌ ሳይሆን ዙምባብዌ ያሉ ዜጎቿ እንዲጠነቀቁ ነዉ-ያሳሰበችዉ።ብዙዎቹ የሐራሬ ነዋሪዎች «ሰላም  ይስፈን» እንጂ----ባዮች ናቸዉ።
                                  
«የምንፈልገዉ ሐገራችን ሰላም እንዲሰፍን  እና ሌሎቹ ጣልቃ እንዳይገቡ ብቻ ነዉ።» ይላል እሱ ፤ ይኸኛዉም 
                        
«በዚሕ ሁሉ ትርምስ መሐል ተስፋ የምናደርገዉ ሠላም እንዲሰፍን ነዉ።የዕለት ከዕለት ኑሯችን እንዲታወክ አንፈልግም።» ወጣቶች ናቸዉ።ከሙጋቤ ሌላ መሪ አያዉቁም።የሰላሳ ሰባት ዓመቱ ገዢ ዓምና ይሔኔ «አስተማሪ ነኝ፤ ኤኮኖሚስት ነኝ፤ፖለቲከኛ ነኝ፤ አሁን ደግሞ ተራኪ ነኝ።የቀረኝን እድሜ ታሪክን ስተርክ ወይም ስፅፍ ባሳላፍ ደስ ይለኛል ብለዉ ነበር» ይሳካላቸዉ ይሆን? ወይስ እንደ ብዙዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች «ሲያልቅ አያምር?»

Simbabwe Constantine Chiwenga und Robert Mugabe
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe
Simbabwe Krise Straßenszenen aus Harare
ምስል Getty Images/AFP

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ