1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ

ዓርብ፣ የካቲት 4 2008

የሠላሳ ሐገራት ርዕሳነ-ብሔራትና መራሕያነ-መንግሥታት፤ የሠባ ሐገራት የዉጪ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚንስትሮች ባጠቃላይ ስድስት መቶ ባለሥልጣናት ይካፈሉበታል።ጋዜጠኛዉም ልክ የለዉም።ከአርባ ስምንት ሐገራት ሰባት መቶ ጋዜጠኛ ሙኒክ ከትሟል።

https://p.dw.com/p/1HuYa
ምስል DW/A. Feilcke

[No title]

የዓለም ፀጥታ እና ደሕንነት ሥለሚጠበቅበት ሥልት የሚነጋገረዉ ዓመታዊ ጉባኤ በደቡባብ ጀርመንዋ ከተማ ሙኒክ ዉስጥ ዛሬ ተጀምሯል።ዛሬን ጨምሮ ለሰወስት ቀናት የሚነጋገረዉ ጉባኤ የሶሪያ ጦርነት፤ የሥደተኞች መብዛት እና የፀረ-ሽብር ዉጊያ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።ጉባኤዉ ላለፉት ሠወስት ዓመታት እየተካረረ የመጣዉ የሩሲያ እና የምዕራባዉያን ልዩነትን ለማጥበብ እንደጥሩ አጋጣሚ ነዉ የታየዉ።በጉባኤዉ ላይ ከመላዉ ዓለም የተወከሉ 600 ያሕል መልዕክተኞች ይካፈላሉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

«የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ» በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ደም የተቃቡት ምዕራባዉያን ጠላቶች ዳግም ጦርነት እንዳይገጥሙ ፤ ለዉጊያ ይዛዛቱ የነበሩትን ምዕራብ-ምሥራቆችን ለማቀዛቀዝ፤ በሁሉም መሐል ለመሳለልም ካለሙ መድረኮች አንዱ ነዉ።ሐምሳ-ሁለተኛ ዓመቱ።በአምሳ-ሁለተኛ ዓመቱ ዘንድሮም ሠላም ሥለማታዉቀዉ ዓለም ፀጥታ ሌላ ርዕሥ-አለማግኘቱ ነዉ ዚቁ።ዘንድሮም በሐምሳ ሁለተኛ ዓመቱ በሞስኮ-ዋሽግተኖች ልዩነት መዘወሩ ነዉ-አዲስ አሮጌነቱ።

Deutschland Syrien-Konferenz Kerry Lavrow de Mistura
ምስል picture-alliance/AA/L. Barth

«የምዕራባዉያን እና የሩሲያ ባለሥልጣናት ደጋግመዉ መገናኘታቸዉ ጥሩ ነዉ» ይላሉ ሲፕሪ በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠረዉ የስዊድን ጥናት ተቋም ሐላፊ ዳን ስሚዝ።

«በምዕራባዉያን እና በሩሲያ መካከል ያለዉ ግንኙነት ባለፉት ሰወስት ዓመታት እየሻከረ መምጣቱ ሁለቱንም ጎራ በጣም የሚያሳስብ ሆኗል።የፈለገዉ ትንታኔ ቢደረግም፤ ሁለቱም የየራሳቸዉን መርሕ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም ይበልጥ በተገናኙ ቁጥር ይበልጥ ይቀራረባሉ።»

ጉባኤዉ የሩሲያዉን ጠቅላይ ሚንስር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን ጨምሮ የሠላሳ ሐገራት ርዕሳነ-ብሔራትና መራሕያነ-መንግሥታት፤ የሠባ ሐገራት የዉጪ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚንስትሮች ባጠቃላይ ስድስት መቶ ባለሥልጣናት ይካፈሉበታል።ጋዜጠኛዉም ልክ የለዉም።ከአርባ ስምንት ሐገራት ሰባት መቶ ጋዜጠኛ ሙኒክ ከትሟል።

በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ፖሊስም ሙኒክ ዉስጥ ፈስሷል።የጉባኤተኞቹ ብዛት፤የመገናኛ ዘዴዎቹ ትኩረት፤ከፀጥታ ጥበቃዉ ቁጥጥር ጋር ተዳምሮ-ያቺን ትልቅ ዉብ ዘመናይ ከተማን «የዓለም ርዕሠ-ከተማ አድርጓታል» ይላል የዶቸ ቬለዉ ዘጋቢ።

Deutschland Bundesaußenminister Frank-Walter Steinmeier vor Syrien-Konferenz
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe

ጉባኤዉ በጥሩ ዉል «ገድ ያለ» ነዉ የሚመስለዉ።በዩናይትድ ስቴትስ እና በሩሲያ የሚመሩት የሶሪያ ጦርነት ዘዋሪዎች ጊዚያዊዉም ቢሆን ተኩስ እንዲቆም ተስማምተዋል።በሩሲያ የጦር ጄቶች የሚደገፈዉ የሶሪያ መንግሥት ጦር ሰሜናዊ ሶሪያ በተለይም አሌፖ የመሸጉ አማፂያን ሥንቅና ትጥቅ የሚያገኙበትን መሥመር መዝጋቱ-አማፂያኑን ለሚረዱት አሜሪካ መራሽ መንግሥታት አስደንጋጭ፤ አሳሳቢ፤አሳፋሪም ነዉ-የሆነዉ።

በዚሕም ምክንያት ምዕራባዉያን እና የአካባቢዉ መንግሥታት ባስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ እየወተወቱ ነበር።ሩሲያ ባንፃሩ ተኩስ መቆም ካለበት-የሚቆመዉ መጋቢት መጀመሪያ ነዉ ብላ ነበር።ሙኒክ ላይ ሁለቱም አንዳድ እርምጃ ተራምደዉ ጊዚያዊ ግን አስቸኳይ በሚለዉ ተኩስ አቁም ተስማሙ።

ሥደተኞች ሌላዉ የጉባኤዉ ትኩረት ነዉ።አሸባሪ ቡድናት በተለይ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ ቡድንን ለማጥፋት የሚደረገዉ ዉጊያ እና የሳይበር ጥቃት ይነሳል።አሁን ከሚታዩት የፀጥታ ችግሮች በተጨማሪ ሥለ ወደፊቱም ይመከርበታል ይላሉ የስፒሪዉ ሐላፊ ዳን ስሚዝ።

«ሁለተኛዉ የፀጥታ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና አሁን የምናየዉና ምናልባት ከሃያ ዓመት በኋላ የሚታየዉ የፀጥታ ችግር ዳራ የሚሆኑት ናቸዉ።የተፈጥሮ ሐብቶች አለቅጥ መመዝበር፤ የዓየር ንብረት መዛባት፤በደሐና በሐብታሞች መካካል ያለዉ ልዩነት አለቅጥ መስፋት---ጥቂቶቹ ናቸዉ»

ሙኒክን ጉባኤተኞች ብቻ አይደሉም ያደመቋት-ተቃዋሚዎች ጭምር እንጂ።የጉባኤዉን በተለይም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዓላማ የሚቃወሙ ከተለያዩ ሐገራት የተወጥጣጡ ሠልፈኞች በጉባኤዉ ሆቴል ዙሪያ ይሰለፋሉ።ፖሊስ አራት ሺሕ ገምቷቸዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ