1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን፣ የጦርነት መሐል ስደተኛ መንግስት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 19 2013

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳምና ሐቻምናዉ ሁሉ ዘንድሮም ሟች-ቁስለኞችን ይቆጥራል።ድርጅቱ እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአረብ-አፍሪቃ ሐገራት ጦር የመንን ከወረረበት ከ2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ ከ112 ሺሕ በላይ ሰዉ አልቋል።አብዛኛዉ ሰላማዊ ሰዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3nIKN
Saudi-Arabien Riad | Einigung auf Friedensplan im Jemen
ምስል Reuters/Saudi Press Agency

የመን «ከመስመጥ» የሚያድናት ይኖር ይሆን?


ዓለም አቀፍ የሥጋት ኮሚቴ (IRC) እንደሚለዉ የመን እንደ አምና ዘንድሮዉ ሁሉ በመጪዉ የጎርጎሪያኑ 2021ም ከዓለም ከፍተኛ ሠብአዊ ቀዉስ ማስተናገዷ አይቀርም።ከየመን ቀጥሎ ከፍተኛ ሠብአዊ ቀዉስ ይታይባታል የተባለችዉ አፍቃኒስታን ናት።ሶስተኛዋ---ይገምቱ?።የርዳታ ድርጅቶች ከኒዮርክ እስከ ዤኔቭ ለየመን ሕዝብ ርዳታ ሲማፀኑ፣ከመካ እስከ ቫቲካን የሚገኙ የኃይማኖት መሪዎች ለየመን ሠላም ሲፀልዩ የሰሜን የመን ገዢ የአንሳር አላሕ (አንሳሩላሕ) ወይም የሁቲ ታጣቂዎች የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማከማቻን አጋዩ።ወዲያዉ የሳዑዲ አረቢያን ሰዉ አልባ ጄት መትተዉ ጣሉ።የተማፅኖ፣ ዱዓ-ፀሎት ዉጊያዉ ተቃርኖ አነጋግሮ ሳያበቃ፣ ተቃርኖ የማያልቅባት ሐገር  ፖለቲከኞች ሪያድ-ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ አዲስ መንግስት መሠረቱላት ተባለ።ቅዳሜ።ይበጃት ይሆን? 
                                        
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳምና ሐቻምናዉ ሁሉ ዘንድሮም ሟች-ቁስለኞችን ይቆጥራል።ድርጅቱ እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአረብ-አፍሪቃ ሐገራት ጦር የመንን ከወረረበት ከ2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ ከ112 ሺሕ በላይ ሰዉ አልቋል።አብዛኛዉ ሰላማዊ ሰዉ ነዉ።በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ቆስሏል።
ድርጅቱ እንደ ሟች ቁስለኞች ሁሉ የረሐብተኛ-በሽተኛ የተፈናቃይ-ስደተኞችን ብዛት ያሰላል።ርዳታ ይማፀናልም።የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ የአንቶኒዮ ጉተረሽ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱዠሪክ ባለፈዉ ሳምንት።
                                     
*«ለርዳታ አቅርቦታችን የሚዉለዉ ገንዘብ ከሚፈለገዉ በግማሽ ያነሰ እንደሆነ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ባልደረቦቻችን አረጋግጠዉልናል።ያለዉ ገንዘብ ከሚያስፈልገዉ 49 በመቶ ነዉ።ለችግረኛዉ ርዳታ ለመስጠት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል።ባሁኑ ወቅት በየወሩ መርዳት የምንችለዉ 9 ሚሊዮን ሕዝብ ነዉ።በዚሕ ዓመት መጀመሪያ ላይ ርዳታ ፈላጊዉ 13 ሚሊዮን  ነበር።ከየመን ሕዝብ 80 በመቶዉ ሠብአዊ ርዳታና ከለላ ያስፈልገዋል።በመጪዉ ዓመት ከየመን ሕዝብ ግማሹ ይራባል።ከ5 ሚሊዮን የሚበልጠዉ ደግሞ ለከፋ ጠኔ ለመጋለጥ አንድ ደረጃ ብቻ ይቀረዋል።50 ሺሕ ያሕሉ የሚላስ የሚቀመስ አያገኝም።»
ረጂዉም በርግጥ ተሰላቸ።እስካሁን 29ኝ ቢሊዮን ረድቷል።6ኛ ዓመቱ።የኃይማኖት መሪዎች ዱዓ-ፀሎት፣ምሕላ፣ ተማፅኖ ግን እንደቀጠለ ነዉ።
«የፈጣሪ ቃል ወደ ሕፃን ልደት በሚቀየርበት በዛሬዉ ዕለት፣ፊታችንን በመላዉ ዓለም በተለይም ሶሪያ፣ ኢራቅና የመን ዉስጥ የጦርነትን ከፍተኛ ዋጋ ወደሚከፍሉት እጅግ ብዙ ሕፃናት ማዞር አለብን።የሕፃናቱ አሳዛኝ ገፅታ የመልካም አሳቢ ሰዎችን ልቡና ይነቀንቅ ዘንድ፣ የግጭት ምክንያቶች እንዲወገዱ፣ ለሰላም ለመስፈን እንድንጥር ያራራን ዘንድ እንመኝ።»
የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ።ዓርብ።ግጭት ግድያዉም አላባራም።ስድስት ዓመት ሊደፍን ሶስት ወር ቀረዉ።የርዳታ ጥሪዉ ከኒዮርክ በተነገረ ሳልስት፣ የሠላም ፀሎቱ ከቫቲካን በተሰማበት ዋዜማ ከሰሜን የመን የአንሳር አላሕ ተዋጊዎች ድል ተነግሮ ነበር።
ተዋጊዎቹ መትተዉ የጣሉትን የሳዑዲ አረቢያ ሰዉ አልባ የስለላ አዉሮፕላን ድሮን ያሉትን በራሪ ከበዉ ይጨፍራሉ።የበራሪዉን አካል እየገነጣጠሉ ይፎክራሉ።ለተጨማሪ ዉጊያና ድል ይዝታሉም።
«የሕዝባዊ ኮሚቴዉ (ሑቲ) ጀግኖች ነን።ዛሬ ማሪድ ግዛት ዉስጥ አሜሪካ ሠራሽ ሰዉ አልባ ሠላይ አዉሮፕላን (ድሮን) መትተን ጥለናል።በፈጣሪ ፍቃድ መዋጋታችንን እንደቀጥላለን።»
የሳዑዲ አረቢያዉ ልዑል መሐመድ ቢን ሠልማን ጥር በ2015 የሐብታም ሰፊ፣ የሙስሊሞች ቅዱስ ሥፍራዎችን ተቆጣጣሪይቱን ሐገር የመከላከያ ሚንስትርነትን ተሾመዉ የዓለምን ፖለቲካ ሲቀየጡ ከዋሽግተን፣ ለንደን፣ ቴልአቪቭ መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና አንዳድ መገናኛ ዘዴዎች የተንቆረቆረላቸዉ አድናቆት ዉዳሴ ለአያት፣አጎቶቻቸዉ ምናልባትም ለአባታቸዉ በየዘመናቸዉ ከዘነበላቸዉ አድናቆት ዉዳሴ የበለጠና የተለየ አልነበረም።
ይሁንና ወጣቱ ልዑል «ለዉጥ አራማጅ፣ዘመናይ፣ አፍቃሬ ምዕራብ፣ ለዘብተኛ፣ ፀረ-ኢራን ወዘተ» እየተባሉ የመወደስ-መሞካሸታቸዉን ምክንያት እንደ ብዙ አጎቶቻቸዉ በጥሞና ከማብሰልሰል ይልቅ እንደ  አያቸዉ ሳይታበዩበት አልቀረም።
ብዙዎች እንደሚሉት «ታሪክ ራሱን ደገመ» እንበል ይሆን?የመሐመድ ቢን ሰልማን አያት ኢብን ሳዑድ እራሳቸዉን  «የኒጃድ ንጉስ» ብለዉ የሰየሙት በአዉሮጳ-አረብ-አሜሪካኖች ጦር ዉጊያ የኦስማን ቱርክ ከመካከለኛዉ ምሥራቅ በተባረረ ማግስት ነበር።ኢብን ሳዑድ የሐሺማይት ገዢዎችን አስገብረዉ፣ በ1932 በስማቸዉ የሰየሟትን ሰፊ በረሐማ ሐገር መሠረቱ።ሳዑዲ አረቢያን።
የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ለኢብን ሳዑድ ዘመናይ ጦር መሳሪያ፣ የፖለቲካና የዉጊያ ምክር ከመስጠት በተጨማሪ  እንደ ሰለሞን ብልሕ፣ እንደ ናፖሊዮን ጀግና እንደ ቢስማርክ ዘመናይ፣ እንደ ክሮምዌል አርቆ አሳቢ እያሉ ማወደስ ማድነቃቸዉ አዲሱ ንጉስ፣ አዲስ ግዛታቸዉ ላይ ተጨማሪ ግዛት ለመደረብ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል።
በ1932 የዛሬዋን ሰሜን የመንን ወረሩ።የአዉሮጶችን ዘመናይ ታንክ መድፍና መትረየስ የታጠቀዉ የሳዑዲ አረቢያ ጦር ባጭር ጊዜ ዉስጥ አሲርን፣ጂዛንን ናጂራንና  ሁዴይዳን ተቆጣጥሮ ወደ ሰነዓ ተጠጋ።የሳዑዲ አረቢያ ወራሪ ጦር ከዘመናዊ ጦር መሳሪያና የዉጊያ ስልት ጋር በማይተዋወቀዉ በየመን ባሕላዊ ተዋጊ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ አልቀረም።ይሁንና ጠንካራዉ የሳዑዲ አረቢያ ጦር በዚያ ተራራ፣ ጉጥ-ስርጓጉጥ  የመሸገዉን የመናዊ ተዋጊ ድል አድርጎ ሰነዓንና አካባቢዋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልቻለም።
ኢብን ሳዑዲ የጦር ሜዳዉ ዉጊያ እንዳሰቡት እንዳልሆነ ሲያዉቁ ከየመኑ ገዢ ከኢማም ያሕያ መሐመድ ሐሚድ ኢድ-ዲን ጋር ተደራድረዉ 20 ዓመት የሚፀና የሠላም ዉል ተፈራረሙ።1934።በጦር መሳሪያ ብዛት ታብየዉ፣ በምዕራቦች አድናቆት ሰክረዉ፣ የያዙትን አጥተዉ ከመዉደቅ በርግጥ ዘየዱ።
የየመን-ሳዑዲዎች ግጭት-ጦርነት፣ የድንበር ግዛት ይገባኛል ዉዝግብ ሙግት ግን ቀዝቀዝ-ሞቅ፣ ቀጥ- ዘወርወር እያለ እንደቀጠለ ቀጠለ።የከፋዉና እስካሁን ብልሐት ያጣዉ ግን የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በ2015 የተሞጀሩበት ነዉ።እንደ ቅድመ አያታቸዉ በጦር መሳሪያ የበላይነት፣ በአሜሪካ ብሪታንያዎች ሁለንተናዊ ድጋፍ፣በአቡዳቢ፣ካይሮዎች አይዞሕ ባይነት ታብየዉ የመን ላይ የጫሩት እሳት የመከበር፣ መወደድ፣መፈራት፣ መወደሳቸዉ ምንጭ የሆነዉን የነዳጅ ሐብታቸዉን እያጋየዉ ነዉ።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን የአንሳር አላሕ (ሑቲ) ተዋጊዎችን ለማጥፋት በሪያድ-አቡዳቢ መሪነት ሰባት ሐገራት ጦር አዝምተዋል።ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ጦር መሳሪያ፣ የጦር አሰልጣኝ፣ አማካሪና መረጃ ይሸጣሉ ወይም ይሰጣሉ።ኤርትራና ጀቡቲ የጦር ሰፈር በመፍቀድ ይሳተፋሉ።አጥኚዎች እንደሚሉት አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ 100 ቢሊዮን ዶላር ከስክስላች።የነዳጅ ማዉጪያ ጉርጓድ፣ ማከማቻ ጋኗ፣ መርከቦቿ፣ ዜጎችዋ ጭምር በሚሳዬል ይጋያሉ።
ሐአሬትስ የተባለዉ የእስራኤል ጋዜጣ ባለፈዉ ሳምንት እትሙ «የመን ቀይ ባሕር ዉስጥ እየሰመጠች ነዉ፣ ግን ማዳን አይቻልም?ጠየቀ።መሐመድ ቢን ሰልማን ከአያታቸዉ መታበየን ብቻ ሳይሆን አቅም ሲያጥጥ የመደራደር መነጋገር ብልሐትን ወርሰዉ ቢሆን ኖሮ፣ የዋሽግተን-ለንደን መሪዎች መርሕ ጠመንጃ ከመቸብቸብ ይልቅ ለሰዎች ሕይወት የቆመ ቢሆን ኖሮ፣ የመንን ብቻ ሳይሆን ሳዑዲ አረቢያንም ከድጥ-ማጥ ስጥመቱ ማዳን በርግጥ አይገድም ነበር።
እስካሁን ግን ዉድመት-ጥፋት ስምጠቱን እንጂ ድርድር መድሕኑን አላየንም።ቢን ሰልማንም መፍትሔ ያሉት ሁለቱን የሁቲ ጠላቶች ማስማማቱን እንጂ ከጦርነቱ ዋና ተዋጊዎች ከሁቲዎች ጋር መደራደሩን አይደለም።
ባለፈዉ ቅዳሜ በሪያድ ግፊት፣ እዚያዉ ሪያድ ዉስጥ ተመሰረተ የተባለዉ ተጣማሪ መንግስት ፕሬዝደንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ አዲሱ መንግስት ክፍፍል ያስወግዳል ይላሉ።«ዛሬ ከአዲስ ምዕራፍ ደርሰናል።ተጣማሪዉ መንግስት ወድማማችነትና ትብብር የሚፀናበት፣ ክፍፍልን የሚያስወገድ መሆን አለበት።በሕዝቡ ፍላጎት ላይ አትኩሮ፣ ስጋቱን የሚያስወግድ መንግስትና ተቋማትን መገንባት፣ ፈተናዎችን እየተጋፈጥን ከአዲሲቱ የመን ጋር በወደፊቱ ጉዳና መጓዝ አለብን።»
አብድ ረቦ መንስር ሐዲ የሚመሩት የየመን ስደተኛ መንግስት የስደተኛ መንግሥትነቱን አየር የሚተነፍሰዉ የሪያድ ገዢዎች መጥነዉ በሚከፍቱለት ሳምባ ነዉ።አይደሩስ ቃሲም ዐብዱል አዚዝ አል ዙቤይዲ የሚመሩት የደቡብ የመን ነፃ አዉጪ ምክር ቤት በሁለት እግሩ የቆመዉ የአቡዳቢን ገንዘብ ተመርኮዞ ነዉ።
በዚሕም ምክንያት ነዉ ለ-በአመክንዮ አሳቢዎች 24 ሚንስትሮች ያሉት አዲሱ የአንድነት መንግስት ከድፍን የመንነቱ ይልቅ የደቡብ የመን፣ከደቡብ የመንነቱ ይበልጥ፣ የሁለቱ የቀድሞ ጄኔራሎች የአብድ ረቦምና የአል ዙቤይዲ፣ ከሁለቱ ጄኔራሎች ይብስ የሪያድ-አቡዳቢ ገዢዎች ጥምረት የሚሆነዉ።የመግቢያ ላይ ጥያቄዬን መልሰዉ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

Jemen Versammlung Huthi Rebellen
ምስል picture-alliance/NurPhoto/M. Hamoud
Jemen | Huthi Rebellen
ምስል picture alliance/dpa/Y. Arahab
DW Exclusive Deutsche Waffen in Jemen SPERRFRIST 26.02.2019 20 Uhr saudische Luftwaffe Folgen
ምስል picture-alliance/Xinhua/M. Dhari
Jemen Krieg Hungersnot
ምስል Reuters/K. Abdullah

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ