1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን በለዉጡ ጎዳና

እሑድ፣ ግንቦት 28 2003

በቤተ-መንግሥታቸው ላይ በደረሰ ጥቃት የቆሰሉት የየመኑ ፕሬዚደንት አሊ-አብዱላህ-ሣሌህ ለሕክምና ሳውዲት አረቢያ ገብተዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠር የየመን ሕዝብ በየከተማው አደባባይ በመሰለፍ ሣሌህ አገር ለቀው መጓዛቸውን ከሥልጣን እንደመወገድ ያህል አድርጎ በነቂስ ወጥቶ ነዉ ደስታዉን የገለጸዉ ።

https://p.dw.com/p/RRqv
ምስል dapd

ፕሪዘዳንቱ ከቤተሰቦቻቸዉ እና ከቤተዘመዶቻቸዉ ጋር በመሆን ወደ ሳዉዲ እንደቡ ነው የተነገረዉ። ተቃዋሚው ወገን አገሪቱን ከሰላሣ ዓመታት በላይ የገዙት ፕሬዚደንት ከእንግዲህ ወደ የመን መመለስ የለባቸውም ባይ ነው። ባለፈው አርብ ሣናአ ውስጥ በሚገኘው ፕሬዚደንታዊ ቤተ-መንግሥት ላይ በተካሄደው የሮኬት ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በጸና መቁሰላቸው ታዉቆአል። የሣሌህን መሄድ ተከትሎ በወቅቱ ምክትል ፕሬዚደንት አብድ-ራቡ-ማንሱር-ሃዲ በጊዜያዊ ፕሬዚደንትነትና የበላይ የጦር አዛዥነት ሥልጣን መያዛቸው ተገልጿል። የመን ውስጥ የፕሬዚደንት ሣሌህን አገዛዝ ከሥልጣን ለማስወገድ ያልተቋረጠ የተቃውሞ ትግል ሲካሄድ ዓመጹ ይበልጥ የተባባሰው በቅርቡ ሣሌህ በባሕረ-ሰላጤው የትብብር ሸንጎ የተደገፈውን የሥልጣን ሽግግር ውል አልፈርምም በማለታቸው እንደ ነበር አይዘነጋም።


አዜብ ታደሰ

መስፍን መኮንን