1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህገ ወጥ ሰፋሪዎች የድሬዳዋን አየር ማረፊያ ስጋት ላይ ጥለዋል

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2011

ህገ ወጥ የመሬት ወረራ በድሬደዋ ትልቅ ችግር እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል። የችግሩ መንሰራፋት ግን የአስተዳደሩ ችግር ብቻ ሆኖ መቆም አልቻለም። በከተማዋ የሚገኘው የድሬደዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ “የመሬት ወረራ አጥሬ ጥግ መድረሱ ለስራዬ ፈተና ሆኖብኛል” እያለ ነው። ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ አየር ማረፊያውን “ሊያዘጋ ይችላል” ተብሏል።

https://p.dw.com/p/3ORBz
Äthiopien Stadansicht Dire Dawa
ምስል DW/M. Teklu

ህገ ወጥ ሰፋሪዎች የድሬደዋን ኤርፖርት ስጋት ላይ ጥለዋል

ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመግታት የሚያስችል ወጥ አሰራር እልፍ ሲል ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ርምጃ መውሰድ ተግዳሮት በሆነበት የድሬዳዋ አስተዳደር ህገ ወጥ የመሬት ወረራን መቼ ማቆም እንደሚቻል መገመት አዳጋች ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው። የከተማይቱ አስተዳደር ከዘጠናዎቹ ጀምሮ ስለ ህገወጥነት ማውራት ቢጀምርም በድሬዳዋ ከሃያ ሺህ በላይ ቤቶች በዚህ መልኩ መገንባታቸውን ለዚህ ዋነኛ ማሳያ አድርገው ያነሳሉ ፡፡

የችግሩ መንሰራፋት ግን የአስተዳደሩ ችግር ብቻ ሆኖ መቆም አልቻለም በከተማዋ የሚገኘው የድሬዳዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ “ህገ ወጥ የመሬት ወረራው አጥሬ ጥግ መድረሱ ለስራዬ  ፈተና ሆኖብኛል”  ብሏል፡፡ የአየር ማረፊያው ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ጥላዬ በሶማሌ ክልል የሺንሌ ወረዳ እና ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በሚዋሰነው የድሬደዋ አየር ማረፊያ መሰል ችግር ፈተና የሆነው በድሬዳዋ አስተዳደር በኩል መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

Äthiopien
በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችምስል DW/Messay Teklu

የሲቪል እና ወታደራዊ በረራዎችን እንዲያስተናግድ ተደርጎ ለሁለት ዓላማ የተቋቋመው አየር ማረፊያ በተለይ የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ባለበት በኩል ችግሩ ጥግ ደርሷል ያሉት አቶ ያሬድ ህገ ወጥነቱን ለመከላከል ጥረት ቢደረግም ፈተና መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ 

የድሬዳዋ አስተዳደር መሬት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ደራራ ሁቃ በድሬዳዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተነሳው ችግር መኖሩን አምነው ህገ ወጥ ሰፋሪዎቹን ለማንሳት አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል። ኃላፊው በአስተዳደሩ “ፈተና ሆኗል” ያሉትን ህገወጥ የመሬት ወረራ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ “አስተዳደሩ ቁርጠኛ ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ ባለፈው አንድ አመት ብቻ በህገወጥ መንገድ በርካታ ሄክታር መጠን ያለው መሬት በህገ ወጥነት በተያዘባት ድሬዳዋ ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ መስጠት ያልተቻለ እንደሆነ፣ “ችግሩ በቀላሉ ሊፈታ አይችልም” የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

መሳይ ተክሉ

ልደት አበበ