1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መርሐ-ግብር ስብጥር ምን ይመስል ነበር?

እሑድ፣ ግንቦት 16 2012

በሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ፊት የቀረቡ ባለሙያዎችና አስተያየታቸው ስብጥር ከጉዳዩ አከራካሪነት አኳያ ምን ይመስል ነበር? የቀረቡ አስተያየቶች በመጨረሻው ውሳኔ ላይ ምን ዓይነት ሚና ይኖራቸዋል? የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የዶይቼ ቬለ ውይይት የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የባለሙያዎች አስተያየት ያደመጠበትን መርሐ ግብር ይዳስሳል

https://p.dw.com/p/3cfhI
Äthiopien Anhörung des Äthiopischen Rates für Verfassungsrechtliche Untersuchungen
in Addis Abeba
ምስል Tesfalem Waldyes

ውይይት፦ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መርሐ-ግብር ስብጥር ፍትኃዊ ነበር?

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይተርጎሙ ባላቸው ሶስት አንቀፆች ጉዳይ የባለሙያዎች አስተያየት አድምጧል። የባለሙያዎች አስተያየት የማድመጡ መርሐ-ግብር ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን ሲጠናቀቅ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ «በወፍ በረር በተደረገው መለየት ከቀረቡት 22 አስተያየቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች በተለያየ ምክንያትም ቢሆን ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ የሚያመለክቱ ናቸው» ሲሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ መዓዛ «ጉባኤው [ይኸን ጉዳይ የመመልከት] ሥልጣን የለውም። የሕገ-መንግሥት ጥያቄ አልቀረበም» የሚሉ የባለሙያዎች አስተያየቶች መቅረባቸውንም አረጋግጠዋል።

ይኸ መርሐ-ግብር በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በመንግሥታቸው ቀጣይ የሥልጣን ቆይታ ብሎም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ኹነኛ ሚና ለሚኖረው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ «ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ» ዝግጅት አንድ አካል ነው። «ባለሙያዎቹ ያቀረቡትን አስተያየት የመመልከት፣ በግብዓትነት የመጠቀም ወይም በማጣቀሻነት ለመውሰድ» እንደማይገደድ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጥሪ ባቀረበበት ደብዳቤ ገልጿል። 

ከቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ሶስት ቀናት በተካሔዱ መርሐ-ግብሮች ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ፣ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ እና የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሰዎች መብቶች ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ሰለሞን ደርሶን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎች የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባቀረበው ጥሪ ወይም ግለሰባዊ ግብዣ መሠረት ሙያዊ ትንታኔ አቅርበዋል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጭምር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ለመሆኑ በሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ፊት የቀረቡ ባለሙያዎች እና አስተያየታቸው ስብጥር ከርዕሰ-ጉዳዩ አከራካሪነት አኳያ ምን ይመስል ነበር? የባለሙያዎች አስተያየት ከመደመጡ በፊት የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጉዳዩን የመመልከት ሥልጣን አለው የለውም የሚለው ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት አልነበረበትም? የቀረቡ አስተያየቶችስ  በመጨረሻው ውሳኔ ላይ ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል? ለውይይት የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው። በኖርዌይ በርገን ዩኒቨርሲቲ በሕግ የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሕግ መምህር ሙሉ በየነ እና በቪየና ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ ትምህርታቸውን በመከታተል የሚገኙት የቀድሞው የሕግ ባለሙያ እና መምህር ሞገስ ዘውዱ በዚህ ውይይት ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ