1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕወሓት ከአፋር ወጥተናል ማለትና ማኅበረሰቡ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19 2014

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች ተቆጣጥረውት ከቆዩባቸው የአፋር ክልል፤ ዞን ሁለት፤ ስድስት ወረዳዎች መውጣታቸውን ቢገልጹም፤ የአከባቢው ነዋሪዎች እና የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ጉዳዩን አስተባብለዋል። የሕወሓት ኃይሎች በአንዳንድ የአፋር ቀበሌዎች እንደሚገኙ እና የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4AW92
Äthiopien Landschaft in Provinz Afar Kamele durch die Wüste
ምስል picture-alliance/dpa

«በአንዳንድ የአፋር ቀበሌዎች ይገኛሉ» ነዋሪዎች

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች ተቆጣጥረውት ከቆዩባቸው አጎራባች የአፋር ክልል፤ ዞን ሁለት፤ ስድስት ወረዳዎች መውጣታቸውን ቢገልጹም፤ የአከባቢው ነዋሪዎች እና የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ጉዳዩን አስተባብለዋል። የሕወሓት ኃይሎች በአንዳንድ የአፋር ቀበሌዎች እንደሚገኙ እና የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ያስገቡት እነዚህን የአፋር ክልል ዞን ሁለት ስድስት ወረዳዎች የተቆጣጠሩት ወታደራዊ ከበባን ለመስበር እና ለትግራይ የሰብዓዊ ርዳታ በር ለመክፈት ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ኃይላቸው ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለቅቆ መውጣቱን ሰኞ እለት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። 

ሕወሓት ከሳምንታት በፊት እንደገለጸ ሁሉ ባለፉት ሦስት ቀናትም በአፋር በኩል ሰመራ-አባዓላ-መቀለ ኮሪደርን መሰረት አድርጎ የሚገባው የርዳታ ቁሳቁሶች ላይ እንቅፋት ላለመፍጠር የአፋር ክልልን ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን እገለጹ ነው። ይሁን እንጂ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ደድርጅት ፕሬዝዳንት ገዓዝ አህመድ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት፤ የሕወሓት ኃሎች ለወራት ተቆጣጥረውት ከቆዩት አንጻር ከበርካታ አከባቢዎች ለቅቀው ቢወጡም አሁንም ቀላል የማይባሉ ቀበሌዎችን አለመልቀቃቸውን አመልክተዋል። እንደ አቶ ገዓዝ እስከ ባለፉት ሦስት ቀናት በአፋር ዞን ሁለት በርካታ ስፍራዎች የተኩስ ድምጽ መሰማቱ አልቀረም። 

Äthiopien Landschaft in Provinz Afar Kamele durch die Wüste
ምስል picture-alliance/dpa

ከጥር አጋማሽ ጀምሮ በጦርነት ላይ ካለው የአፋር ዞን 2 አንዱ ወረዳ ከሆነው እረብቲ ተፈናቅለው የቆዩት ሌላው የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት የሕወሓት ኃይሎች ከበርካታ ስፍራዎች የወጡት አንድም ቀን ጦርነት ሳይቋረጥ ነው። የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ሠራዊትን ከአፋር ክልል ማስወጣት ያስፈለገው የሰብዓዊ እዳታ ትግራይ ክልል እንደ ልብ ሊገባ ይችላል የሚል ተስፋ ስላላቸው መሆኑን የሮይተር ዘገባ ያሳያል፡፡ አቶ ገዓዝ አህመድ ግን አሁንም አፋርን ሙሉ በሙሉ ለቀው ያልወጡት የትግራይ ኃይሎች ክልሉን ሙሉ በሙሉ ቢለቁ እንኳ እንደ ዘላቂ ሰላም መደምደሙን በጥርጣሬ ይመለከቱታል፡፡ 

የፌዴራል መንግስት የሰብዓዊ ርዳታ ትግራይ ክልል ያለምንም ችግር እንዲገባ የተኩስ አቁም በማወጅ የትግራይ ኃይሎች በወረራ ይዘዋል ካላቸው የአፋር እና አማራ ክልሎች አጎራባች አከባቢዎች እንዲወታ መጠየቁ አይዘነጋም። ሕወሓት በበኩሉ በወቅቱ አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን ቢያሳውቅም ጦሩን ርዳታው ከሚገባበት አፋር ክልል ሳያስወጣ ሳምንታት ተቆጥረዋል። 
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ከሦስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫም የትግራይ ኃይሎች ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ በመጠየቅ፤ ወደ ትግራይ የሄዱና ያልተመለሱ ከአንድ ሺህ በላይ የጭነት መኪኖች እንዲመለሱና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግም ጠይቆ ነበር።

የሕወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲ፣ ኮላባ እና በራህሌ የተባሉ 6 ወረዳዎችን በቁጥጥራቸው ስር ማዋል የጀመሩት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ነበር። የተኩስ አቁሙ ከታወጀ በኋላ 144 የርዳታ መኪኖች ወደ ትግራይ መግባታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) መረጃ ያመለክታል።
ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ