1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የላይቤርያ ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 5 2002

ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የላይቤርያና በአፍሪቃ ታሪክም ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚደንት ናቸው። ፕሬዚደንት ሰርሊፍ «ህይወቴ ለላይቤርያ » በሚል ስለ ህይወት ታሪካቸው የደረሱት መጽሃፋቸው ሰሞኑን እዚህ ጀርመን ሀገር ውስጥ በጀርመንኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ወጥቶዋል።

https://p.dw.com/p/KWYz
ፕሬዚደንት ሰርሊፍምስል picture-alliance/dpa

16.01.2006 -ላይቤርያን ለሁልጊዜ የቀየረ ዕለት ነበር። ከአንድ ዓመት በፊት ከተደረገው ምርጫ በኋላ በአፍሪቃ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ሴት ስልጣን ላይ ወጣች፤ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ይባላሉ።

ብዙ ስራ ነው የጠበቃቸው። ከአስራ አራት ዓመታት ጦርነት በኋላ ላይቤርያን መልሰው መገንባት ፤ ሙስናን መታገል እና ለውጊያ ተመልምለው ለነበሩት ህጻናት የስራ ቦታ ማግኘት ነበረባቸው። ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ሁሉ ማድረግ ተሳክቶላቸዋል። በጦርነት ተዳቆ የነበረን አካባቢ እንደገና በራሱ እንዲተማመን አድርገዋል። አንዳንዶች አራት መቶ ገጾችን የያዘውን የህይወት ታሪካቸው የሚያወሳውን መጽሀፍ የአዲሲቱ ላይቤርያ መስራች መመሪያ አድርገው ተመልክተውታል። ደራሲዋ ግን ያለፉት ዓመታት የስራ ውጤት የመጀመሪያ ግምገማ፡ ለሂሰኞቻቸው ደግሞ መልስ አድርገው ነው የተመለከቱት።

« ሰዎች የህይወት ታሪክሽን ለምን አሁን ጻፍሽው፡ የስልጣን ዘመንሽ እስከሚያበቃ አትጠብቂም ነበር ብለው ይጠይቁኛል። መልሴ ቀላል ነው። ያለፈው ይጠፋል፤ የወደፊቱ ሁኔታ ደግሞ ከፊታችን ይጠብቀናል። በመሆኑም መስራት ያለብህን አሁን በዚህ ወቅት ስራ። ተሞክሮየን ለማካፈል እፈልጋለሁ። ተሞክሮየ ምናልባት ሌሎችን ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ ያደፋፍር ይሆናል። »

የላይቤርያ ዜጎች ኤለን ጆንሰንን በፍቅር ማ ኤለን ብቻ ብለው ሳይሆን ባላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳም ጠንካራዋ ወይዘሮ ብለው ይጠሩዋቸዋል። የአንድ ጀርመናዊ የልጅ ልጅ የሆኑት ሰርሊፍ፡ ወጣት ሳሉ ይኸው ፍላጎታቸው አሜሪካውያኑ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አድርሶዋቸዋል። በዓለም ባንክም ውስጥ ትልቅ ስልጣን ነበራቸው። በላይቤርያ ፖለቲካ ውስጥ ተግተው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ሰርሊፍ በሰባኛዎቹ ዓመታት ውስጥ የገንዘብ ሚንስትር ሆነው ተሾመውም ነበር። የቀድሞው የላይቤርያ ፕሬዚደንት ሳምዩዌል ዶ አስፋፍተውት በነበረው ሙስና አንጻር ሳይፈሩ በመናገራቸውም የመታሰር መጥፎ ዕጣ ገጥሞዋቸውም ነበር።

Studenten an der Universität Monrovia, Liberia
ምስል picture alliance/dpa

ሰርሊፍ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፡ ምንም እንኳን ሳያሸንፉ ስለቀረው፡ ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በዕጩነት ቀርበው ነበር። ከጦርነቱ ፍጻሜ እና አምባገነኑ የቀድሞ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር ከታሰሩ በኋላ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ወደሀገራቸው ተመለሱ። ስለራሳቸው ሲናገሩ ባለሙያ፡ ጠቢብ፡ ፖለቲከኛ እና ያጋጣሚም ነገር ሴት ነኝ የሚሉት ሰርሊፍ ወደትውልድ ሀገራቸው መመለሳቸውን እንደ ትልቅ ድል ይቆጥሩታል።

« ሴቶችን አነጋግሬአለሁ፤ የላይቤርያ ሴቶችን፡ የአፍሪቃ ሴቶችን፡ የዓለም ሴቶችን ማነጋገር ነው የምፈልገው። የላይቤርያ ሴቶች እዚህ በርስ በርሱ ጦርነት ጊዜ ብዙ መጥፎ ነገር ደርሶባቸዋል፤ ተደፍረዋል፤ በባርነት ቀንበርም ተይዘው ቆይተዋል። ያም ሆኖ ግን እነዚሁ ሴቶች ነበሩ በሀገራችን ሰላም ለማውረድ ጠንክረው የሰሩትና የጣሩት። መንግስቴ ለነርሱ ክብር ሲል፡ ለሴቶች በሁሉም የሀገሪቱ ጉዳዮች በጠቅላላ ጉልሁን ሚና ይሰጣቸዋል። የወደፊቱ ሁኔታ የኛ ነው፤ ምክንያቱም የኛ ብለን ተቀብለነዋልና። »

ላይቤርያን የዴሞክራሲ፡የግልጽነትና የመልካም አስተዳደር አርአያ ለማድረግ ነው የሚፈልጉት። ግን እዚያ ለመድረስ ፕሬዚደንት ሰርሊፍ ገና ብዙ ትግል ይጠብቃቸዋል። በላይቤርያ በርግጥ ጉልህ ዕድገት ቢታይም፡ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ወድቆዋል። ባንዳንድ የመዲናይቱ ሞንሮቪያ አካባቢዎች ኮሬንቲ እና ውሃ አለ፤ ብዙው የላይቤርያ መሰረተ ልማት ግን ተንኮታኩቶዋል። ከሀገሪቱ ህዝብ መካከል ሰማንያ ከመቶው ስራ አጥ ነው። ብዙው ህዝብም ማንበብና መጻፍ አይችልም። ይህም ብዙው የላይቤርያ ህዝብ በሀገሩ መንግስት ላይ ቅር እንዲሰኝ አድርጎታል። የፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ተቃዋሚዎች፡ በጎረቤት ሲየራ ልዮን ለተካሄደው የርስበርስ ጦርነት በከፊል ተጠያቂ ናቸው በሚል ክስ ተመስርቶባቸው በዴን ኻግ ኔዘርላንድስ አሁን ለፍርድ የቀረቡት የቀድሞው የላይቤርያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር ጭምር ይህንን የላይቤርያን ህዝብ ቅሬታ በፕሬዚደንትዋ አንጻር ቅስቀሳ ለማካሄድ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ።

« ሚስተር ቴይለር ለሁሉ ጊዜ በታሪክ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲጣሉ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። እኔና የላይቤርያ ህዝብ፡ ሚስተር ቴይለርን ወደኋላ በመተው፡ በአንድነተ ወደፊት መራመድ እንፈልጋለን፤ የዕርቀ ሰላሙን ሂደት፡ የኤኮኖሚ መልሶ ግንባታውን ለመጀመር እና ልማት ለማስገኘት እንፈልጋለን። »

በእስራት የሚገኙት ቻርልስ ቴይለር ደጋፊዎቻቸውን በማንቀሳቀስ የፕሬዚደንት ሰርሊፍን ገጽታ ለማበላሸት ሙከራቸውን ቀጥለዋል። ፕሬዚደንትዋ ግን ለሚሰነዘርባቸው ወቀሳ ተጠያቂ አለመሆናቸውን ሁሌ፡ በመጽሃፋቸው ሳይቀር፡ ከመግለጽ ወደኋላ አላሉም።

« ቻርልስ ቴይለር ጨካኙን አምባገነን ሳሙየል ዶን ከስልጣን ለማውረድ ባደረጉት ጥረታቸው ላይ መጀመሪያ ላይ መደገፌን ሁሌም ተናግሬአለሁ። ቴይለር የኋላኋላ ሀቀኛውን ገጽታቸውን ባሳዩ ጊዜ ግን ዋነኛ ተቃዋሚያቸው ሆኜአለሁ። ይህንን ሁሌ በግልጽ አሳውቄአለሁ። ቻርልስ ቴይለርን በሚገባ ባለማወቄ የላይቤርያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። »

ማ ኤለን ከህዝብ ጋር ባላቸው ቅርበት ስላላቸው፡ ግልጹ አሰራር በመከተላቸው እና ለላይቤርያም የተሻለ የወደፊት ዕድል ለመስጠት በመነሳታቸው ለጊዜው በስልጣናቸው ላይ እንደተደላደሉ ይገኛሉ።


አሌግዛንደር ገብል/አርያም ተክሌ