1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የላይቤሪያ ጤና ጥበቃ ሰራተኞች አድማ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 5 2007

በላይቤሪያ የተከሰተው የኤቦላ ወረርሽኝ ታማሚዎችን ብቻ ሳይሆን የጤና መኮንኖችዋን እና ሀኪሞችዋን ጭምር ስጋት ላይ ጥሎዋል። የጤና መኮንኖቹ እና ሀኪሞቹ በኤቦላ የተያዙትን ሰዎች በማስታመሙ ተግባራቸው ላይ

https://p.dw.com/p/1DW62
Liberia Streikaufruf
ምስል picture alliance/AP Photo

ራሳቸውን ከአስተላላፊው ተሀዋሲ ለመከላከል የሚያስችለው አስፈላጊው ቁሳቁስ አልቀረበላቸውም። በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ጀምረዋል። በላይቤሪያ ሀኪሞች፣ የጤና መኮንኖች ፣ ነርሶች እና የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ወረርሽኙን የመቆጣጠሩ ትግል አዳጋች በሆነበት ባሁኑ ጊዜ ይህን ዓይነት ርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል አይገባቸውም ፣ በወቅቱ በሀገሪቱ ብዙ ክርክር አስነስቶዋል። ኤቦላ አብዝቶ ከጎዳቸው ሀገራት አንዷ በሆነችው ላይቤርያ ውስጥ ወረርሽኙ ከ2,300 የሚበልጥ ሰው ሞቶዋል። የሚያስታምሙት የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ትልቅ ስጋት ተደቅኖባቸዋል። በዚህም የተነሳ ብሔራዊው የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ማህበር ባለፈው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስራ ማቆም አድማ ጠርቶዋል። ማህበሩ ለሰራተኞቹ የተሻለ የሕይወት ዋስትና እና በሙያቸው ለአደገኛ ሁኔታ ለተጋለጡበት ድርጊት የሚታሰብላቸው 500 ዶላር ወደ 700 ከፍ እንዲል ጠይቆዋል። ማህበሩ ይህን ርምጃ የወሰደው ወደ 10,000 የሚጠጉት አባላቱ፣ በተለይ አሁን በኤቦላ ሰበብ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለማጉላት መሆኑን የማህበሩ መሪ ጆርጅ ፖ ዊሊያምስ አስታውቀዋል።

« በመጀመሪያ ደረጃ ማወቅ ያለብህ የኤቦላ ታማሚዎችን የሚንከባከቡት የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ራሳቸውን ከበሽታው የሚከላከሉበት ሁኔታ አልመመቻቸቱን ነው። በርካቶች ሞተውብናል። የነዚሁ የሞቱት ባልደረቦቻችን ቤተሰቦች ከመንግሥት አንዳችም ርዳታ አላገኙም። ይህ አሳሳቢ ችግር ነው። ከዚሁ ጎን ደግሞ፣ የጤና ጥበቃ ሰራተኞች የደሞዝ ጉዳይ ሌላ ችግር ፈጥሮዋል። ስለዚህ፣ መንግሥት የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ራሳቸውን ለአደገኛ ሁኔታ ላጋለጡበት ድርጊት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያስብላቸው እና የሟች የጤና ጥበቃ ቤተሰቦችም አንዳንድ ጥቅም ሊያገኙ የሚችልበት የተሻለ የሕይወት ዋስትና እንዲያደርግላቸው ጠይቀናል። »

Liberia Ebola ländliche Gebiete
ምስል Dominique Faget/AFP/Getty Images

የስራ ማቆሙ አድማ የተጀመረው የላይቤሪያ ሀኪም ቤቶች በወቅቱ የኤቦላ ታማሚዎችን ማስታመም የማይችሉበት ደረጃ ላይ በሚገኙበት ጊዜ ነው። የላይቤሪያ የጤና ጥበቃ ዘርፍ ባካባቢው እጅግ ደካማው ነው። በተመድ መዘርዝር መሠረት፣ በሀገሪቱ ለየ100,000 አንድ ሀኪም ብቻ ነው ያለው። የጤና ጥበቃ ሰራተኞች በወቅቱ ይህን ዓይነት ጥያቄ በማቅረባቸው ያልተደሰቱት የላይቤሪያ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዎልተር ጉዌኒጋል አድማቸውን አቁመው ወደስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

« አንድ የላይቤሪያ ዜጋ ወይም የራሳችሁ ዘመድ እየታመመ እናንተ ለጥቂት ዶላር ብላችሁ ጀርባችሁን ስታዞሩበት ማየት ያሳምማል። እና እኔ እንደ አንድ የጤና ጥበቃ ሰራተኛ ይህን ማድረግ አለብን ብዬ አላስብም። የኔን ርዳታ የፈለገን ታማሚ ይህንን ርዳታዬን ነፍጌው አላውቅም። »

የስራ ማቆም አድማ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹን የሀኪም ቤት ሰራተኞችንም ጭምር ያስቆጣ ሲሆን፣ እነዚሁ ሰራተኞች የስራ ማቆሙን አድማ ጥሪ ችላ በማለት ስራቸውን ቀጥለዋል። ከነዚህም አንዱ በመዲናይቱ ሞንሮቪያ መዳረሻ በሚገኘው የሪደምሽን ሀኪም ቤት የሚሰራው ጄምስ ግባታ ነው።

Redemption Hospital in Monrovia
ምስል picture-alliance/dpa

« ዛሬ ወደስራ ቦታዬ የመጣሁት ሞት ያሰጋቸውን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለመርዳት ነው። መንግሥት በጤና ጥበቃ ሰራተኞች አኳያ የሚከተለውን አሰራር እየነቀፍን፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሲሞቱ በፍጹም ዝም ብለን ማየት አንችልም። »

የስራ ማቆሙን አድማ የላይቤሪያ ጋዜጠኞችም ነቅፈዋል። በጤና ጉዳዮች ላይ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ያቋቋሙት ለጤናው ዘርፍ ድጋፍ የሚሰጠው የላይቤሪያውያን መረብ አስተባባሪ ቪክቶር ሼ ለዕለታዊው ጋዜጣ «ደይሊ ኦብዘርቨር» በሰጡት አስተያየት የጤና ጥበቃ ሰራተኞች የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ የሚሞገስ መሆኑን ቢያመለክትም፣ ዓላማቸውን ከግብ ሊያደርሱ የሚችሉት፣ በስራ ማቆም አድማ ሳይሆን ከመንግሥት ጋር ውይይት በማካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። ከዶይቸ ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የተመ የፀረ ኤቦላ ትግል አስተባባሪ ድርጅት ኃላፊ አንተኒ ባንበሪ የላይቤሪያ ሀኪም ቤት ሰራተኞች ጥያቄን በሚገባ እንደሚረዱት ቢገልጹም፣ የስራ ማቆሙ አድማ የፀረ ኤቦላውን ትግል አብዝቶ እንደሚጎዳው አስጠንቅቀዋል።

Anthony Banbury, Vorsitzender der UNO-Sondermission UNMEER
ምስል Reuters//Christopher Black/WHO

« ዓለም ኤቦላን በመታገሉ ረገድ ግንባር ቀደም የሆኑት የየሀገራቱ የጤና ሰራተኞች የሚገባቸው ደሞዝ እንዲከፈላቸው የማድረግ ጠንካራ የሞራል ኃላፊነት አለበት፣ ቢያንስ ይህን ማድረግ አለብን፣ የጤና ሰራተኞቹ ተግባራቸውን በሚያከናውኑበትም ጊዜ ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ማግኘታቸውንም ማረጋገጥ አለበት። »

ድርጅታቸው የጥና ጥበቃ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሟቾችን የሚቀብሩትም ተመጣጣኝ ደሞዝ እንዲከፈላቸው ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ባንበሪ ገልጸዋል።

የላይቤሪያ ሀኪም ቤቶች የሚገኙበት ሁnኔታ እጅግ አስደንጋጭ ነው። በወቅቱ፣ ምን ያህል ሰራተኞች የስራ ማቆሙን አድማ መቀላቀላቸው በውል አልታወቀም፣ ይሁንና፣ ሀኪም ቤቶቹ የኤቦላ ተሀዋሲ ይዞዋቸዋል ተብለው ለተጠረጠሩ እና ርዳታ ፍለጋ ወደዚያ የሚሄዱ ሰዎችን በሰራተኛ እጥረት የተነሳ የሚመልሱበት ድርጊት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠው ወይም ለማጥፋት የተጀመረውን ጥረት በጣም ይጎዳዋል።

ጁልየስ ካኑባ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ