1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ፍርድ ቤት ውሳኔ ትችት

ዓርብ፣ ሐምሌ 24 2007

በሙዓመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል-ኢስላም እና በቀድሞው የሊቢያ መንግስት ባለስጣናት ላይ የተወሰነው ውሳኔ ዓለም አቀፍ ትችት እየቀረበበት ነው። በሊቢያዋ የትሪፖሊ ከተማ ያስቻለው ችሎት ሰይፍ አል-ኢስላምና ሰባት ተከሳሾች በጥይት ተደብድበው ይሙቱ ብሎ ቢበይንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የክስ ሂደቱ ጎዶሎ ነው በማለት እየወቀሱ ነው።

https://p.dw.com/p/1G88M
Saif al-Islam Gaddafi Libyen
ምስል dapd

[No title]

አንድ ወቅት ተራማጅ ለሊቢያ ሕዝብና መንግስትም ተስፋ ነበር። ሊቢያ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ሊኖራት፤ ሰብዓዊ መብቶችና የፕሬስ ነጻነት ሊከበሩ ይገባል የኢኮኖሚ መዋቅሩም ለውጥ ያሻዋል ብሎ ሞግቷል። በስመ-ጥሩው የለንደን ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የተማረውና በምሁራን ሙገሳ የጎረፈለት ሰይፍ አል-ኢስላም የአባቱ ሙዓመር ጋዳፊ ስልጣን በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. የሕዝብ ማዕበል ሲናጥ የተጣለበት ተስፋ ሁሉ መና ቀርቶ ነፍጥ አነሳ። ከቤንጋዚ እስከ ትሪፖሊ የዘለቀው የሊቢያውያን ተቃውሞ መንግስታዊ ስርዓቱን ሲነቀንቅ የታላቋ ብሪታኒያ ንጉሳውያን ቤተሰብን ጨምሮ ያሞገሱት ምዕራባውያን ሁሉ ሸሹት። የሊቢያውያን ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት በዚያው ዓመት በዚንታን ከተማ ታጣቂዎች እጅ የወደቀው ሰይፍ አል-ኢስላም በቀረበበት የጦር ወንጀል በሊቢያ ትሪፖሊ በሚገኝ ፍርድ ቤት በጥይት ተደብድቦ ይሙት በቃ ተፈርዶበታል። በሰይፍ አል-ዒስላም፤ የቀድሞው የሊቢያ የደህንነት ሃላፊ አብዱላህ ስኑሲ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ላይ የሞት ብይን የተላለፈበት የፍርድ ሂደት ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሊቢያ ተመራማሪዋ ማግዳ ሙግሃራቢ የፍርድ ሂደቱ የተከሳሾችን መብት ያላከበረ በመሆኑ ያልተሟላ እንደሆነ ይናገራሉ።

Libyen Eröffnung des neuen Gerichtshauses in Tripoli 2012
ምስል picture-alliance/dpa

«የክስ ሂደቱ በርካታ የሕግ ጥሰቶችና የ37ቱም ተከሳሾች መብት ያልተከበረበት በመሆኑ ጎዶሎ ነው። የተከሳሾች የሕግ ምክር የማግኘት፤ ያለመናገር፤ በችሎት የመገኘት መብቶች አልተከበሩበትም። ያናገርናቸው በርካታ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን በግል የመጎብኘት እድል ተነፍገዋል። ተከሳሾች ጠበቆቻቸው በሌሉበት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል። አንዳንዶቹ የክስ ሂደቱ እስኪጀመር ጨርሶ ጠበቃ አልነበራቸውም። ለምሳሌ ያህል የአብደላ ስኑሲ ቤተሰቦች በተከሳሽ ላይ በቀረበባቸው ከባድ ውንጀላ ምክንያት ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው ማግኘት አልቻሉም።»

በትሪፖሊው ፍርድ ቤት ከቀረቡት የሙዓመር ጋዳፊ ባለስልጣናት መካከል ስምንቱ እድሜ ልክ፤ ሰባቱ የአስራ ሁለት ዓመታት እስር ሲበየንባቸው አራቱ ደግሞ በነጻ ተሰናብተዋል። በሌለበት የተከሰሰው ሳዒፍ አል-ኢስላም ችሎቱን ከዚንታን ከተማ ሆኖ በቪዲዮ ታድሟል። ሰይፍ በቀረበበት ክስ በጥይት ተደብድቦ እንዲሞት ሲፈረድበት የምስክሮችን ቃል እሱም ሆነ ፍርድ ቤቱ አለማድመጣቸውን ማግዳ ሙግሃራቢ ይናገራሉ።

«ሰይፍ አል-ኢስላም በዚንታን ከተማ በታጣቂዎች እጅ ሆኖ ነው ችሎቱን በቪዲዮ የተከታተለው። ይሁንና ከ24ቱ ችሎቶች የተከታተለው አራቱን ብቻ ሲሆን ሞት የተፈረደበትም በሌለበት ነው። በክስ ሂደቱ ለፍትሃዊ ዳኝነት ቁልፍ ጉዳይ የሆነው የምስክሮች ቃል አልተመሳከረም። የክስ ዶሴው በዋናነት መሠረት ያደረገው ተከሳሾች አንዳቸው በሌላቸው ላይ የተናገሩትን ጨምሮ በምስክሮች ቃል ላይ ነው። አንድም ምስክር በፍርድ ቤት ተገኝቶ ቃል አልሰጠም። ይህ ደግሞ ተከሳሾች የቀረበባቸውን መረጃ ለመከላከል እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።»

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የሊቢያ ፍርድ ቤት ክሱን በገለልተኝነት በሙሉ መፈተሽ ነበረበት ሲሉ ይወቅሳሉ። ይሁንና የሊቢያ መንግስታዊ መዋቅር ከፈራረሰ ወዲህ በነጻነት ሥራቸውን የሚከውኑ ተቋማት የሉም። የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሲሆን የፍርድ ቤቶች፤ አቃብያነ ሕግ፤ ጠበቆችና ምስክሮች ደህንነት በታጣቂዎች ፍላጎት ውስጥ የወደቀ ነው።

Gaddafi-Sohn Saif al-Islam wird nicht nach Den Haag ausgeliefert
ምስል AP

ሊቢያ በአሁኑ ወቅት ሁለት መንግሥታት አሉ። አንዱ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ይሁንታ ያገኘው በቶብሩክና አልባይዳ መሠረቱን ያደረገው ሲሆን አብኛውን ምሥራቃዊ ሊቢያ ይቆጣጠራል። አሁን ሰይፍ አል-ኢስላም እና የቀድሞ ባለስልጣናትን የዳኘው ፍርድ ቤት የሚገኘው መቀመጫውን ትሪፖሊ ባደረገው መንግስት ሲሆን አብዛኛውም ምዕራባዊ ሊቢያ ይቆጣጠራል። በሁለት መንግሥታትና በርካታ የታጣቂ ቡድኖች የተከፋፈለችው ሊቢያ የቀድሞ ጠንካራ ሰው ሰይፍ አል-ኢስላም የጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. ተቃውሞ ተከትሎ ተፈጽመዋል በተባሉ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት (ICC)ይፈለጋል። ሊቢያ ግን አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም። አሁን በትሪፖሊ ፍርድ ቤት የተበየነበት የሞት ፍርድ ተግባራዊ ስለመደረጉ ማግዳ ሙግሃራቢ ጥርጣሬ አላቸው። እስከዚያው ግን ሰይፍ አል-ኢስላምና አብረውት የተበየነባቸው የሙዓመር ጋዳፊ መንግስት ባለስልጣናት ፍርድ ለፍትህ ስርዓቱ ላዕላይ ምክር ቤት (Highest Judicial Council)የሚቀርብ ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ