የሊቢያ ፀጥታና ጠቅላይ ሚንስትሯ
ሐሙስ፣ መስከረም 30 2006
የሊቢያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ዚዳን ዛሬ ሲነጋጋ በታጣቂዎች ከታገቱ በሕዋላ ማርፈጃዉ ላይ ጉዳት ሳይደርስባቸዉ ተለቅቀዋል።የሊቢያ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ጠቅላይ ሚንስትሩን ያገቱት የሊቢያ አብዮታዊ ኮሚቴ የተሰኘዉ የቀድሞ አማፂ ቡድን ታጣቂዎች ሲሆኑ፥ ያስለቀቋቸዉ ደግሞ የሌላ ታጣቂ ሐይል ባልደረቦች ናቸዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዚዳን ለሥድስት ሰዓት ያሕል ከታገቱ በሕዋላ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸዉ ቢለቀቁም የማገቱ እርምጃ ብዙዎችን ያስነደቀ፥ አነጋጋሪም ነዉ። በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉን ሰሜን አፍሪቃዊት ሐገር ፀጥታም ብዙ እያሳሰበ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።
መፈንቅለ-መንግሥት ለአፍሪቃም፥ ለአረበብም እንግዳ እንዳይደለ፥ከአፍሪቃዊቷ፥ አረባዊቷ ሊቢያ በላይ እማኝ በርግጥ የለም።የመሪዎች መገደል፥ ለአፍሪቃም፥ ለአረብም አዲስ እንዳልሆነም ከሊቢያ የተሻለ የቅርብ ጊዜ-ምሳሌ አይገኝም።ከትልቅ ከተማ፥ ምናልባት በጥብቅ ከሚጠበቅ ትልቅ ሆቴል ትልቅ መሪ ሲታገት ግን ጀርመናዊዉ የፖለቲካ አጥኚ ጊዶ ሽታይበርግ እንደሚሉት የዛሬዉ የመጀመሪያዉ ሳይሆን አይቀርም።
አፍሪቃ አረብ-ጉድ፥ አጃኢብ ሲል የፖለቲካ ተንታኝ ሽታይንበርግ አስደናቂ አሉት።
«ሁኔታዉ በርግጥ አስደናቂ ነዉ።በአካባቢዉ ጠቅላይ ሚንስትር የታገተበትን ጊዜ አላስታዉስም። (በመሪዎች ላይ) የግድያ ጥቃት ተሰንዝሮ ያዉቃል።አንድ ሁለት መሪዎች ተገድለዉም ነበር። በሥልጣን ላይ ያለ ጠቅላይ ሚንስትር ከትልቅ ሆቴል፥ ያዉም ርዕሠ-ከተማይቱ ዉስጥ ከሚገኝ ያን እሚያሕል ሆቴል፥ በቂ ጥበቃ ሳይደረግላቸዉ መታገታቸዉ፥ ለማመን ፍፁም የሚከብድ ነዉ።»
ግን ሆነ።የ63 ዓመቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዓሊ ዚዳን በርግጥ የተደገሰላቸዉን አያዉቁም። ኮሪንታል ከተሰኘዉ ግዙፍ፥ ምቹ ሆቴል ምናልባት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ላይ-ይሆኑ ይሆናል።ጎሕ መቅደዱ ነዉ።ዚዳን፥ የሙዓመር ቃዛፊን አገዛዝ በመቃወም እንደ ዲፕሎማት፥ እንደ ሰብአዊ መብት ጠበቃ፥ ከጄኔቭ ብራስልስ በሚመላሱበት ወቅት ፈረንሳይ፥ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ በመሩና ባስተባበሩት ዓለም እየተረዱ የጋዛፊን ጦር የወጉት አማፂያን አንድ መቶ ሐምሳ መኪኖች እያርመሰመሱ ከትልቁ ሆቴል ደረሱ።ጊዜ አላጠፉም።የጎደለዉን የኮሪታል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አብድል አል-ረዛቅ፥ ሞሉት።
«ሰዎቹ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተሰጠን ያሉትን ወረቅት ይዘዉ መጡ።ጠቅላይ ሚንስትሩን የማሠሪያ ትዕዛዝ ይዘዉ ነበር።አማፂዎች ናቸዉ።መጡ ጠቅላይ ሚንስትሩን ያዙ ሔዱ።»
አመፂያኑ ከሆቴሉ ከመሔዳቸዉ በፊት ያጎሳቆሏቸዉን ጠቅላይ ሚንስትር መንፅራቸዉ እንደወለቀ፥ ሸሚዛቸዉ ሳይቆለፍ፥ ፂማቸዉ ሳይላጭ ከቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ገተሯቸዉ።ጠቅላይ ሚንስትሩን ያገተዉ የሊቢያ አብዮታዊ ኮሚቴ የተሰኘዉ የሚሊሺያዎች ቡድን እንደ ብዙዎቹ የሚሊሺያ ሐይላት ሁሉ ከሊቢያ መንግሥት ካዝና በጀት የሚቆረጥለት፥ከሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር በቅርብ ተባብሮ የሚሠራ ነዉ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የተያዙት በሙስና ሥለሚፈለጉ ከሐገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ በተሰጠ ትዕዛዝ ነዉ-የሚለዉን መግለጫ ግን የርዕሠ-ከተማ ትሪፖሊ የፀጥታ አስከባሪ አዛዥ ሐሺም በሽር አስተባብለዋል።
«ለዓቃቤ ሕጉ ስልክ ደውዬ ነበር፣ በአሊ ዜይዳ ላይ የእሥር ማዘዣ አለማውጣታቸውን በመግለፅ ዜናውን አስተባብለዋል። ይህን አድርጌ ቢሆን ኖሮ፣ እኔም ወንጀለኛ ሆኜ ነበር ሲሉ ነበር ቃል በቃል የነገሩኝ። ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማሰር ሕጋዊ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይግባል።»
አጋቾች ኋላ ላይ እንዳስታወቁት ጠቅላይ ሚንስትሩን ያገቱት፥ ዩናይትድ ስቴትስ በ1990 የናይሮቢና የዳሬ-ሰላም ኤምባሲዎቿን ካጋዩ «አሸባሪዎች አንዱ» ያለችዉን አቡ አነስ አል ሊቢን ባለፈዉ ሳምንት ከሊቢያ አፍና ስትወስድ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተባብረዋል በሚል ለመበቀል ነዉ።ሰበብ ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ታዛቢዎች እንደሚሉት የቀድሞዉ የሊቢያ አምባገገን ገዢ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከተገደሉ ወዲሕ ሊቢያ ማንም ታጣቂ በፈለገበት ጊዜ ያሻዉን የሚያደርግባት የሥርዓተ-አልበኞች ሐገር መሆናን መስካሪ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ