1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህፃንነት ዘመን መዝሙሮች

ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2005

ለመሆኑ በልጅነት የትኛውን መዝሙር ነው ተጫውታችሁ ያደጋችሁት? እቴሜቴ የሎሚ ሽታ፣ ጨረቃ ድንቡል ቦቃ...ወይንስ ሌላ? የህፃናት መዝሙሮች ባህልን በማስረፅ ረገድ ድርሻቸው ምንድን ነው?

https://p.dw.com/p/17yBB
ምስል nano+art

ሶስቱም የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቃን ናቸው ። ሙዚቃን ተምረው ህይወታቸውን ከሙዚቃ አቆራኝተው የሚኖሩ ወጣት እንስት ሙዚቀኞች። ሶስቱም የህፃናት መዝሙሮችን ዜማና ግጥም ደርሰው የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለኢትዮጵያውያን ህፃናት አበርክተዋል።

Bildergalerie nach Europa eingeschleppte Tiere und Pflanzen Symbolbild Artenvielfalt
ምስል Fotolia/hjschneider
Botanik Blume Gerbera
ምስል Fotolia/d.albert


ህይወት ማሞ ትባላለች። ከያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ፒያኖና ክራር የሙዚቃ መሳሪያዎችን አጥንታለች። ለቤተሰቧ 4ኛ ልጅ ስትሆን፤ በሙዚቃው የዘለቀች ብቸኛዋ ልጅ ናት። በእርግጥ እህት ወንድሞቿም በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ተሰማርተዋል። ህይወት ሙዚቃን ለልጆች ከማስተማርም አልፋ የተለያዩ የልጆች መዝሙሮችን አሳትማለች። በተንቀሳቃሽ ምስል ተደግፈው በቪሲዲ ከተቀረፁት መዝሙሮቿ መካከል «ተነሱ እንጫወት» ስትል ርዕስ በሰጠችው መዝሙሯ ህፃናት የሀገራቸውን የተለያዩ ጭፈራዎች እንዲማሩ ትሞክራለች።

ሳምራዊት ታደሰ፤ ከ10 ዓመታት በፊት ከያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት በረቂቅ ሙዚቃ የተመረቀች ሌላኛዋ ሙዚቀኛ ናት። በዋናነት ያጠናችው ክላርኔት የተሰኘውን ሙዚቃ ሲሆን፤ በሁለተኛነት ደግሞ ፒያኖ ተምራለች። ለቤተሰቦቿ አምስተኛ ልጅ የሆነችው ሳምራዊት ወደ ልጆች መዝሙር ስራ እንድትሳብ ያደረጓት ውጭ ሀገር የሚኖሩት የእህቷ ልጆች ናቸው። የእህቷ ልጆች በጥልቀት ለማያውቁት የሀገራቸው ባህላዊ መዝሙር የመመሰጣቸው ነገር ሳምራዊትን የበለጠ ሳይስባት አልቀረም። ሳምራዊት ባህልን በልጆች መዝሙር ውስጥ ወደ ህፃናት ለማሻገር ከፍተኛ ጥረት እንደምታደርግ ትጠቅሳለች። በእርግጥም «እሹሩሩ» የተሰኘው ስራዋ ጥረቷን በግልፅ ያንጸባርቃል። ሳምራዊት «እሹሩሩን» ከማቀናበሯ በፊት በኢትዮጵያ የተለያዩ ስድስት ቋንቋዎች ወላጆች ህፃናትን ለማስተኛት እንዴት እንደሚያባብሏቸው ለማወቅ ሰፋ ያለ ጥናት እንዳደረገችም ገልፃለች።

ትዕግስት ጌታቸው፤ በመጀመሪያ በ1989 ዓም ከያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት በዲፕሎማ ተመረቀች። ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላም በድጋሚ ወደ ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ተመስልሳ በ1999 ዓም በዲግሪ መርሀ ግብር ትምህርቷን አጠናቃለች። በዋናነት ያጠናችው ቫዮሊን የተሰኘውን የሙዚቃ መሳሪያ ሲሆን፤ ፒያኖን በሁለተኛ ደረጃ አጥንታለች። በቫዮሊንና በኦርጋን የተቀነባበሩ ሙዚቃዎችን በቡድን ሆና በተለያዩ ሆቴሎች ታቀርባለች። የሙዚቃ መምህርት ናት። «ነው ወይ ልንለያይ» የተሰኘውን የውጭ ዜማ «በመስከረም እንገናኝ» ስትል የትዝታ ቅኝት አላብሳ ለልጆች እንዲህ ተጫውታዋለች።

ትዕግስት የልጆች መዝሙሮችን ስታቀናብር በስፋት የተለመዱ የውጭ ሀገር መዝሙሮችን ሳይቀር የሀገረሰብ ዜማና ግጥም እንዲላበሱ ጥረት ታደርጋለች። ህፃናት የሀገራቸው ባህል በውስጣቸው እያቆጠቆጠ አብሯቸው እንዲያድግ የልጆች መዝሙሮች ሚናቸው ላቅ ያለ ለመሆኑ የሳምራዊት ሌላኛው ስራ ገላጭ ነው።


የህይወት ስራዎች ውስጥም ብዙዎች በልጅነት የተጫወቷቸው እንደ ጨረቃ ድምቡል ቦቃንና እቴሜቴን የመሳሰሉ የልጅነት መዝሙሮች ይገኛሉ። ህይወት ከድምፅ ባሻገር በምስል የተቀናበሩ ሁለት የቪሲዲ ህትመቶች አላት። «የኔታን ይማርልን» የተሰኘው ቅንብሯ የቆሎ ተማሪ ቤት ድባብን ለማምጣት ይሞክራል። የኔታ ቡልኮዋቸውን ተከናንበው፣ ጭራቸውን እንደጨበጡ ፊደል በሚቆጥሩ ህፃናት ተከበው መዝሙሩ ይጀምራል።

ህይወት «የኔታን ይማርልን» በሚለው ስራዋ ህፃናት እየተዝናኑ በቀላሉ ፊደል እንዲቆጥሩ ለማድረግ ስትጥር ትታያለች። ሌላኛዋ የሙያ አቻዋ ትዕግስት በበኩሏ «መፅሐፍ ነው የኔ ጓደኛ» በሚለው ስራዋ ህፃናት የማንበብ ባህላቸው ገና በአፍላው መሰረት እንዲይዝ ታበረታታለች።

ህይወት የልጆች መዝሙሮችን ስታዘጋጅ ባህልን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ነጥቦችን ለመዳሰስ ከመጣሯ ባሻገር ስራዎቿ ንፁህ የሆኑ ቦታዎችንና ምስሎችን ማንጸባረቅ እንዳለባቸውም አፅንኦት ትሰጥበታለች። ይህ በእርግጥ አብዛኛው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ይወክል እንደሆንም አንዳንድ ሰዎች ይጠይቋታል።

ሶስቱም ወጣት ሙዚቀኞች የልጆች መዝሙሮች ባህልን ለማንፀባረቅ ድርሻቸው ላቅ ያለ ነው ይላሉ። ሳምራዊት ሙዚቃ ዓለምአቀፍ ቢሆንም ልጆች በሙዚቃ ቋንቋቸውን እንዲያውቁ ማድረጉ አገራቸውን እንዲያስታውሱ ይረዳል ትላለች።
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ