1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህገ-መንግሥት ክርክር በሶማልያ፣

ሐሙስ፣ ሐምሌ 19 2004

በእርስ በርስ ጦርነት ፤ ተዳቃና የተደላደለ መንግሥት መመሥረት ተስኗት ከ 21 ዓመት በላይ በምስቅልቅል ላይ ለምትገኘው ሶማልያ የሚበጅ ረቂቅ ህገመንግሥት የቀረበ ሲሆን፣ ልዩው ም/ቤት ትናንት ተሰብስቦ መክሯል። ይህ የሆነው ፣ በሙስና የተዘፈቀው

https://p.dw.com/p/15f5e
ምስል Reuters

በአፍሪቃ ኅብረትና በምዕራቡ ዓለም የሚደገፈው የሽግግር መንግሥት፤ የሥልጣን ዘመኑ ከማክተሙ አንድ ወር ቀደም ብሎ ነው።

Somalia Mogadischu Kämpfe
ምስል Reuters

በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ፣ በአገር ሽማግሌዎች የተመረጠው፤ 825 አባላት ያሉት የሶማልያ ብሔራዊ  ሸንጎ፣ በህዝበ ውሳኔ ፤ በመጨረሻ ከመጽደቁ በፊት፣ በጊዜያዊውም ሆነ ረቂቁ  ህገ-መንግሥት ላይ ለመወያየት የ 9 ቀናት ክርክር ያካሂዳል።

በሶማልያ ፤ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ኦግስቲን ማሂጋ እንደሚሉት «የሚካሄደው ተግባር እየሠመረ በመሆኑ ፤ የሚያነቃቃ ነው፤»  

ከ 21 ዓመታት የሽግግር ዘመን በኋላ፣ ለተረጋጋችና የሠመረ የመንግሥት ተግባር እንድታካሂድ ለምትጠበቀው ሶማልያ  አዳዲስ የፖለቲካ ተቋማትን ለማደረጀት የሚበጅ እርምጃም ነው ፤ እንደ ልዑኩ አባባል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩት የህዝብ እንደራሴዎች፤ በአፍሪቃ ኅብረት ጦር ሠራዊትና በሽግግሩ መንግሥት  ፀጥታ አስከባሪዎች ጥበቃ ፤ በቀድሞው የፖሊስ አካደሚ ህንጻ ውስጥ ነው የተሰበሰቡት። ይኸው ውስብስብ ያለው አሠራር፤ 8 ዓመት በሥልጣን ላይ ለቆየውና በጣም ጥቂት የፖለቲካ ዕድገትን ላስመዘገበው ፣ ምዕራባውያን ለሚደግፉት የሽግግር ፌደራል መስተዳድር፤ እንደ አንድ እመርታም ሆነ ጠቃሚ የሥራ ክንውን  ነው የታየው።

Dürre Hungersnot Afrika Kenia Dadaab Somalia Flüchtlinge
ምስል picture alliance/dpa

አምባገነኑ ፕሬዚዳንት  ሲያድ ባሬ፣ በጥር ወር  1983 ዓ ም፤ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሶማልያ የተደላደለ ማዕከላዊ መንግሥት ማቆም እንደተሣናት ነው የምትገኘው። የወደፊቱ ህገ-መንግሥት፤ አገሪቱ የፌደራል ሪፓብሊክ እንድትሆንና ከእስላማዊው ህግ ሸሪያ መሠረታዊ ደንቦች ጋር የተቀራረበ እንዲሆን ተደርጎ ነው የተረቀቀው። የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተዘርግቶ፣ በአገሪቱ ተቋማት ሁሉ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ የሚደነግግ ነው ።

ያለፈውን   ሀገ-መንግሥት ካሁኑ ጋር እንዴት ነው ማነጻጸር የሚቻለው? በምሥራቅ አፍሪቃ የስልታዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ --ኢማኑኤል ኪሲያንጋኒ--

Turkish Airlines in Mogadischu
ምስል picture-alliance/dpa

«የአሁኑ ህገ-መንግሥት፤ የተረቀቀው ፣ የቀድሞው ፤ ለፕሬዚዳንቱ ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ እንደነበረ ታስቦ ነው።  ይኸኛው ፣ ይበልጥ የተስተካከለ፤ የሥልጣን ክፍፍልን ፣ ቁጥጥርንም ፈር ያስያዘ ነው። ህገ-መንግሥትን  በሥራ ላይ ለማዋል፤ ሶማሌዎችም የባህርይ ለውጥ እንዲያደርጉ ነው የሚጠበቅባቸው። ምክንያቱም፤ እንዳየነው፤ ህግ ቢኖርም፤ ፖለቲከኞች፤ የራሳቸውን ጥቅም ለማሣካት በተለዬ ሁኔታ  ነበረ የሚተረጉሙት።»

Somalia Friedensmission Soldaten aus Uganda Flagge
ምስል picture-alliance/ dpa

የሶማልያ ረቂቅ ህገ-መንግሥት፤ ዜጎች ሁሉ፤ የጾታ፤ የሃይማኖት ፤ የማኅበራዊ ኑሮ ፣ የኤኮኖሚም አድልዎ ሳይደረግባቸው በህግ ፊት እኩል ናቸው ይላል። በይፋ እንደተገለጠው ከሆነ፣ ቢያንስ 30 ከመቶ ሴቶች በፓርላማው እንዲወከሉ፤ ወጣቶች፣ የሃይማኖት ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች፤ ነጋዴዎችና የአካደሚ ሰዎች እንዲሁም በውጭ  ሃገራት የሚኖሩ ሶማሌዎች ፤ ሁሉም ተገቢው ውክልና እንደሚኖራቸውም ያትታል።  ያሁኑ ረቂቅ ህገ መንግሥት ፤ ዓለም አቀፍ እውቅና ባታገኝም ነጻነት ካወጀች ከ 20 ዓመት በላይ የሆናትን ሶማሊላንድንም የሶማልያ አንድ አካል ናት ነው የሚለው። ሶማሊላንድ  ግን ፤ አይመለከተኝም በማለት በመቅዲሾው ህገ መንግሥት የማርቀቅ ሂደት አልተሳተፈችም። ታዲያ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው አንድ ጥያቄ፣

የፖለቲካውና የፀጥታው ይዞታ፣ የሽግግሩን ፣ የአስተዳደር ዘመን እንዲያከትም ለማድረግ እስከምን ድረስ አስፋላጊም ሆነ አስተማማኝ ነው? የሚለው ነው። አሁንም ኢማኑኤል ኪሲያንጋኒ-----

Mogadischu Alltag Markt
ምስል AP

«የሽግግሩን መንግሥት የሥልጣን ዘመን እንዲያበቃ ማድረጉ እንዲያውም፣ ዘግይቷል ማለት ነው የሚቻለው። እነዚህ ሰዎች፤ የህዝብ እንደራሴዎቹ፣ ያን ያህል --ምንም ያደረጉት ነገር የለም። አብዛኛውን ጊዜያቸውን በናይሮቢና በሌሎችም ቦታዎች ነበረ የሚያሳልፉት።

አሁን ከዚያ መነሣታቸው፤ እንዲያውም ዘግይቷል። የሚያሳስበው አሁን፤ የ «አሚሶን ጉዳይ ነው።(የአፍሪቃ የሰላም ተልእኮ በሶማልያ)!ያለነሱ፤ የአሁኑ የሽግግር ፌደራል መንግሥት ኅልውና የሚታሰብ አልነበረም። የምለው፤ የአሚሶም ቆይታ ነው የሚያነጋግረው።

በዚያ የሚቆዩበት የሥልጣን ዘመንም፤ ከመጪው ታኅሳስ ወር በላይ የሚዘልቅ ነው። በአሁኑ  ጊዜ ለሽግግሩ ፌደራላዊ መንግሥት ጠቃሚና አስፈላጊ ነው።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ