1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዚምባብዌና አምባገነኑ መሪዋ

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 1999

በፖሊስ ቁም ስቅል ያዩት ሞርገን ሽቫንጊራይ

https://p.dw.com/p/E0bF
ምስል AP

የዚምባብዌው መሪ ሮበርት ሙጋቤ ከአንፀባራቂ የነፃነት ታጋይነት እና ከአፍሪቃ የነፃነት ጀግናነት ወደ አምባገነንነት ተቀይረው መላ ህዝባቸውን ያገቱ ሰው ናቸው ። በደፈጣ ውጊያ የነጮችን ቅኝ አገዛዝ ያስወገዱት ሙጋቤ በተገላቢጦሹ ፈላጭ ቆራጭና ዘረኛ የቅኝ ገዥዎችን መሰል ፖለቲካ እያራመዱ ነው ። ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ጥፋት የሚያመጣ ነው ። ስልጣናቸውን ለማደላደልም አዲስ ፀረ ኮሎኒያሊዝም ዘመቻ እንደተያያዙ እንዲታወቅላቸው ይፈልጋሉ ። የነጮችን ፖለቲካ ይነቅፋሉ ። በተለይ ብሪታኒያና አሜሪካን አገራቸውን ለውድቀት እንደዳረጉዋት አድርገው ነው የሚያቀርቡት ። ሆኖም ግን እርሳቸው ተጠያቂ ያደረጉዋቸው አይደሉም ጥፋተኞቹ ። ዚምባብዌን ያደሀይዋት እርሳቸው እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም ። ሀገሪቱ ነፃ ከወጣችበት እአአ ከሺህ ዘጠን መቶ ሰማንያ አንስቶ የሚመርዋት እርሳቸው ናቸው ። ሙጋቤ የሚያራምዱት ሀላፊነት የጎደለው ፖሊሲ ነው የዚምባብዌን የውጭና የውስጥ ንግድ እንዲዳከም በፖለቲካውም ሀገሪቱ እንድትገለል ያደረገው ። ሙጋቤ ፖለቲካ ህዝብን ለማገልገል የኑሮ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚበጅ መሆን እንዳለበት ከዘነጉት ረዥም ጊዜ ሆኗል ። በአሁኑ ሰዓት ከዓለማችን እጅግ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ያለው በዚምባብዌ ነው ። በአሀዝ ሲቀመጥ ግሽበቱ አንድ ሺህ ሰባት መቶ በመቶ ነው ። ሰማንያ በመቶው የዚምባብዌ ዜጋ ስራ አጥ ነው ። የነዳጅ ፣ የስጋና ፣ የዳቦ ዕጥረት አለ ። እንዲሁም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ወደ መንኮታኮቱ ተቃርቧል ። በዚህ ዓመት ሀገሪቱ ከሚያስፈልጋት በቆሎ ግማሽ ያህሉ ብቻ ነው የተመረተው ። የቀድሞዋ የአፍሪቃ የዕህል ጎተራ ዚምባብዌ ለረሀብ ተዳርጋለች ። ዚምባብዌ ከነፃነት በኃላ ከደቡብ አፍሪቃ ጎን በኢኮኖሚው መስክ የስኬት ታሪክ ባለቤት የመሆን በርካታ ዕድሎች ነበርዋት ። ዝምድናና የጥቅም ግንኙነት እንዲሁም ሙስና የሙጋቤ ስርዓት የሚከተለው አሰራር ነው ። የአብዛኛው ድሀ ህዝብ ዕጣ ፈንታም በዚህ አሰራር ውስጥ ነው የወደቀ።
ሙጋቤ በሺህ የሚቆጠሩ ነጭ ገበሬዎችን አባረው የእርሻ መሬቶችን ርሳቸው ለመረጡዋቸው አከፋፍለዋል ። አብዛኛዎቹ በእርሻ ስራ የተሰማሩት ሰራተኞች ግን ባዶ እጃቸውን ነው የቀሩት ። የዚምባብዌ ህዝብ ነፃ ከወጣ ወዲህ ሌላ ፕሬዝዳንት አያውቅም ። በተቃዋሚው ሞርገን ስቫንጋራይ ላይ መንግስት ሊወስድ ይችላል በሚባለው ዕርምጃ ሰዉ በፍርሀት እየተርበደበደ ነው ። በህዝቡ ላይ ጥልቅ የሆነ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነው የሚታየው ። ሙጋቤ ግን በሚቀጥለው ዓመት ከሚካሄደው ምርጫ በኃላም ከዚህ አቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ማስተዳደር እንደሚፈልጉ ነው ያሳወቁት ። ይህ ዕውን የሚሆን ከሆነ ሀገሪቱ ሰራተኛውን አገር ገንቢው ህዝቧን ታጣለች ። የሚችል ሁሉ ሀገሪቱን ለቆ መሰደዱ አይቀርም ። ይሁንና የተቃዋሚው የሞርጋን ስቫንጊራይ መታሰርና ቁምስቅል ማየት ሁኔታዎችን ሊለውጥ ይችላል ። በዚምባብዌ መንግስት ላይ ነቀፌታው ከውስጥም ከውጭም እንዲሁም ከራሳቸው ፓርቲ ጭምር እየጠነከረ በመሄድ ላይ ነው ። ዕርግጥ ነው ተስፋ የቆረጠው ህዝብ ለሰላሳ ዓመታት ሰጥለጥ አድርገው ከገዙት ከፈላጭ ቆራጩ ሙጋቤ በቀላሉ መገላገሉ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም ። ይህ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ግን ከራሳቸው ፓርቲ ግፊቱ ተጠናክሮ ከቀጠለ ነው ። በዚህ ላይ የውጭ አገራትም ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ። በዚምባብዌ ለውጥ እንዲመጣ ከጎረቤት አገራት ደቡብ አፍሪቃ በተጨማሪም የአፍሪቃ ህብረት ትልቁ ድርሻ ይኖራቸዋል ።