1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዚምባቡዌ፤ ምርጫና የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2005

የዚምባብዌ የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤት ባለፈዉ ወር የተካሄደዉ ምርጫ የሀገሪቱን ሕግ የተከተለ ነዉ ሲል የቀረበዉን አቤቱታ ዉድቅ አድርጓል። ፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ነፃ እንዳልነበረ የሚሞግቱት ወገኖች በበኩላቸዉ የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ መንበራቸዉን እንዳይለቁ መንገድ አመቻችቷል ሲሉ ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/19UFX
ምስል Reuters

የዚምባቡዌ ምርጫ ዉጤት ተጭበርብሯል ሲሉ አቤቱታቸዉን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞርጋን ቻንጊራይ ወደፍርድ ቤት ከወሰዱ በኋላ፤ ሕገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ምን ሊወስን ይችላል በሚል ጥርጣሬ ሲጠበቅ ቆየ። የትናንት ደግሞ ይህ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ በሐምሌ 24ቱ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በ 61 በመቶ ድምጽ ማሸነፋቸዉን አረጋገጠ።

ዋና ዳኛ ጎድፍሬ ቺዲያዑሲኩ ሙጋቤ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ዳግም መመረጣቸዉን ይፋ ሲያደርጉም ምርጫዉ ነፃ፣ ፍትሓዊና ተዓማኒ ነዉ በማለት ነዉ ያሰሩት። ይህም የ89ዓመቱ አዛዉንት በድጋሚ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በትረ ስልጣናቸዉን እንደጨበጡ እንዲዘልቁ መንገዱን አመቻችቷል። ይህን የሰሙት የሙጋቤ ጠበቃ ተረንሲ ሁሴንም ደስታቸዉን መቆጣጠር አልቻሉም፤

Douglas Mwonzora
የMDC ቃል አቀባይ ዳግላስ ሞዋንዞራምስል Jekesai Njikizana/AFP/Getty Images

«በጣም ተደስተናል ምክንያቱም ዉሳኔዉ መረጋጋትና እርግጠኝነትን አምጥቷል፤ አሁን ወደፊት መቀጠል እንችላለን። አሁን ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ፕሬዝደንታችን ማን እንደሆነ አዉቀናል ብዬ አስባለሁ።»

ሙጋቤ ላለፉት 33 ዓመታት ዚምባቤዌን ሲገዙ፣ ሲያስተዳድሩ ኖረዋል፤ ሐሙስ ዕለት ደግሞ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ቦታዉን ይዘዉ ለመቆየት ቃለመሃላ ይፈጽማሉ። የቃለመሃላ ስርዓቱ ምርጫዉ ከተካሄደ አንስቶ እንስካሁን የዘገየዉም ዉጤቱ በተቃዋሚዉ ፓርቲ ተዓማኒነት እንደሌለዉ ተገልጾ ወደሕግ በመቅረቡ ነዉ። የቻንጊራይ ፓርቲ የንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለዉጥ ቃል አቀባይ ዳግላስ ሞዋንዞራ ፍርድ ቤቱ ለሙጋቤና ፓርቲያቸዉ አድልቷል፤ ተቃዋሚዉ ወገን ትግሉን ይቀጥላል ብለዋል።

«በዚህች ሀገር ለፍትህ መታገላችንን እንቀጥላለን። የሕግ የበላይነት በሥርዓታችን ቦታዉን ማግኘቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ትግላችንን አናቋርጥም። ከዚህ ሁኔታ የደረስንበት ምክንያት አቤቱታችንን የሚደግፉልንን አስፈላጊ ነገሮች ማግኘት ባለመቻላችን ነዉ። ፍትህ አላገኘንም።»

MDC የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በሐምሌ 24ቱ ምርጫ ሥራ ላይ የዋሉ ቁሳቁሶችን በሙሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሚዛናዊ ፍትህ አላገኝም በማለት ባለፈዉ ዓርብ ነዉ አቤቱታዉን ማንሳቱን ያስታወቀዉ። ከዚም ወደደቡብ አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ SADC ልዑካኑን የላከዉ። ምንም እንኳን ፓርቲዉ SADC ሙጋቤ ምርጫዉን እንዲደግሙ ይጠይቃል በሚል ተስፋ አላደረኩም ቢልም ከደቡባዊዉ የአፍሪቃ ሀገራት ማኅበረሰብ ጠንከር ያለ ትችት ሳይጠብቅ አልቀረም።

»ሆኖም የአካባቢዉ ተቋማት ማለትም የአፍሪቃ ኅብረትና SADC ይህን አላደረጉም።እንዲያም ሆኖበአንድ ወገን ምርጫዉን የተከታተሉት የሀገር ዉስጥ ታዛቢዎች ተዓማኒነት እንደሚጎለዉ ሲገልጹ፤ ምዕራቡ ዓለም ደግሞ ጥርጣሬዉን አመላክቷል። የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ ግን ለአንዳንድ የዚምባቡዌ ዜጎች እንግዳ አልሆነም፤

Simbabwe Wahlen Morgan Tsvangirai
ሞርጋን ቻንጊራይምስል Reuters

«የሚያስደንቅ ነገር የለም። የፍትህ አባላቱ አንደኛ የሙጋቤ ፓርቲ ታማኞች መሆናቸዉን ስለምናዉቅ በእዉነቱ ይህንኑ ጠብቀን ነበር። ገና የዛሬ 13ዓመት ነጭ ዳኞችን ጨምሮ ለፍርድ የሚሰየሙ ዳኞች ሲታደኑ አይተናል። አሁን ደግሞ ዳኛ ሁዉንጉዋ ሰለባ ሆነዋል። ስለዚህ ዳኞቻችን ከዛኑ PF ፓርቲ ፍላጎት ተቃራኒ መወሰን የሚችሉበት አማራጭ የለም። በተጨማሪ ጉዳዩ እንደገና ቢሮክራሲም አለበት፤ ቻንጊራይ ሙጋቤ ምርጫዉን አጭበርብረዋል ያሉትን ለማረጋገጥ መረጃ እንዳያገኙ ታግደዋል። እና ሕግን መመሪያዉ ያላደገ የይስሙላ ችሎት ከዚህ የተለየ ዉሳኔ ያሳልፋል ተብሎ አይጠበቅም።»

«እንደሚመስለኝ የተጠበቀ ነዉ። ዳኞቹን የሾሙት ሙጋቤ ናቸዉ። ባለፈዉ ሳምንትም የምርጫዉን ድል መቀልበስ እንደማይቻል ተናግረዋል። እናም ዉሳኔዉ ይህ እንደሚሆን ጠብቀናል።»

እናም አሁን ዚምባቡዌያዉያን የሙጋቤን ቃለ-መሃላ መፈጸም ሲጠባበቁ፤ ሞርጋን ቻንጊራይ ደግሞ ምናልባት ክስ ይጠብቃቸዋል። የሀገሪቱ ዝቅተኛ ፍርድ ቤት ለዚምባቡዌ ብሄራዊ የአቃቤ ሕግ ባለስልጣን በጻፈዉ ደብዳቤ፤ ቻንጊራይ ሰሞኑን በሰጧቸዉ መግለጫዎች የሀገሪቱን የፍትሕ ስርዓት የሚያጣጥል ነገር ተናግረዉ እንደሆን እንዲመረምር ጠይቋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ