1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘገምተኛው የአፍሪቃ ኢኮኖሚ

ረቡዕ፣ ግንቦት 3 2008

ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ኢኮኖሚ ከ15 አመታት በኋላ ዝቅተኛውን እድገት አስመዘግቧል። ባለፉት አመታት በፍጥነት እየሰፋ ነው የተባለለት ኢኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. የሚኖረው እድገት ከዓለም አማካኝ ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1Iloj
Shell Bonny Island Öl Umweltverschmutzung Niger River Delta in Nigeria
ምስል Getty Images

ዘገምተኛው የአፍሪቃ ኤኮኖሚ

ያለፈው ዓመት ከሰሐራ በርሐ በታች ለሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ኢኮኖሚ ፈታኝ ሆኖ አልፏል። ድንገተኛ የመገበያያ ገንዘብ ምጣኔ መዋዠቅ፤የነዳጅ ዘይት እና መዳብን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ ማሽቆልቆል እና እንደ ቻይና እና አውሮጳን ከመሰሉ ደንበኞች የግዢ ፍላጎት መቀነስ በቀጣናው ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። የቀጣናው ኢኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ከ5%በላይ እድገት ያስመዘግባል የሚለው ቅድመ-ትንበያም አልያዘም። የኢኮኖሚ እድገቱ 4½በመቶ ብቻ ነበር። የኢኮኖሚው ዘገምተኝነት ግን 2015ን ተሻግሮ በ2016ም የከፋ እንደሚሆን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረገው ዘገባ ይጠቁማል። በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. የአፍሪቃ ኢኮኖሚ እድገት 3% ብቻ እንደሚሆን ተቋሙ አስታውቋል። ለአመታት ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሽ የነበሩት አገሮች የዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ያሳደረባቸውን ጫና መቋቋም ተስኗቸዋል።

ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ በርካታ ለውጦች ተከስተዋል። ከሰኔ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በ50 በመቶ አሽቆልቁሏል። በመጪዎቹ አመታት የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማንሰራራት ሊያሳይ እንደሚችል ቢታመንም በቀደሙት አመታት የዋጋ ተመን ላይ ግን ሊደርስ አይችልም። ይህ ለስምንቱ የአፍሪቃ የነዳጅ ዘይት ላኪ አገራት ኢኮኖሚ መርዶ ነው። አንድ አራተኛ አፍሪቃውያን የሚኖሩባቸው እና ከአህጉሪቱ የግማሽ ያክሉ አመታዊ የምርት መጠን ባለቤት የሆኑት አገሮች በውጭ ምንዛሪ ክምችታቸውም ይሁን በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሮባቸዋል። ከእነዚህ አገራት መካከል ናይጄሪያ፤አንጎላ እና ካሜሩን ይጠቀሳሉ።

Malawi Lilongwe Menschen warten an Tankstelle
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ለዓለም ገበያ የሚቀርቧቸው የተፈጥሮ ጋዝ በ41%፤የአይረን ድፍድፍ (iron ore) በ44% የድንጋይ ከሰል 22 %፤ጥጥ 21%፤መዳብ በ7% እንዲሁም ፕላቲኒየም በ22% ዋጋቸው ቀንሷል። በዓለም አቀፍ ገበያ በተፈጠረው የፍላጎት መቀነስ የተጎዱ የአፍሪቃ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ክምችታቸውን ለመታደግ የምንዛሪ ለውጥ ለማድረግም ተገደዋል። ለውጡ ግን የአገራቱን ኢኮኖሚ ለመታደግ በቂ አይመስልም።እንደ ወርቅ እና መዳብ የመሰሉ የተፈጥሮ ሐብቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያቸውን የሚደጉሙት ጋና፤ደቡብ አፍሪቃ እና ዛምቢያን የመሳሰሉ አገሮች እድገታቸው ክፍኛ ተጎድቷል።

ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች መካከል 37ቱ የነዳጅ ዘይት ገዢ ናቸው። እነዚህ አገራት በዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል ተጠቃሚ መሆናቸውን የዓለም የገንዘብ ተቋም ያወጣው ዘገባ ያትታል። እነዚህ አገራት ለነዳጅ ዘይት የሚያወጡት ወጪ ከዓለም ገበያ ከሚሸምቱት ሸቀጥ የ20% ከአመታዊ የምርት መጠናቸው ደግሞ 7% ድርሻ አለው። የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከ50% በላይ መቀነሱ የቁጠባ መጠናቸው አመርቂ ላልሆነባቸው አገራት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መጠን ታድጎላቸዋል። ይሁንና ሁሉም የነዳጅ ዘይት ሸማቾች ተመሳሳይ የእድገት ምጣኔ አልነበራቸውም። አይኖራቸውምም። አይቮሪ ኮስት፤ኬንያ እና ሴኔጋል ከነዳጅ ዘይት ዋጋ መቀነስ ተጠቃሚ የሆኑ አገሮች ናቸው። አገራቱ የመሰረተ-ልማቶችን በማስፋፋት ላይ በማተኮራቸው እና የአገር ውስጥ ፍላጎትን በማሳደጋቸው በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ኢኮኖሚያቸው 5% ማሳደግ መቻላቸውን የዓለም የገንዘብ ተቋም ዘገባ ይጠቁማል።

Bildergalerie Großstädte aus dem Nichts Abuja
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

በደቡባዊ እና ምስራቃዊ አፍሪቃ የተከሰተው ድርቅ በቀጣናው አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፏል። የዓለም የገንዘብ ተቋም ዘገባ በድርቁ ምክንያት የለት ምግብ ፈላጊ ዜጎቻቸውን ለመመገብ የሚታገሉት ኢትዮጵያ፤ማላዊ እና ዚምባብዌ የኢኮኖሚ እድገት በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ዘገምተኛ እንደነበር ጠቁሟል። ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ለመመገብ የምትታትረው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷ ቀድሞ ከተተነበየው በታች እድገት ማስመዝገቡን የዓለም ገንዘብ ተቋም ዘገባ አትቷል። አሁን በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን የውጭ ምንዛሪ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለመሸመት አስገድዶታል።

ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገራት በተለይም ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ሐብቶችን ወደ ውጭ በመላክ ጥገኛ የሆኑት ናይጄሪያ እና አንጎላን መሰል አገሮች ከእንዲህ አይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ለማምለጥ ፖሊሲዎቻቸውን እንዲፈትሹ የዓለም የገንዘብ ተቋም አሳስቧል። የተቋሙ ምክር ግን ለአፍሪቃውያኑ አዲስ አይደለም። ከዚህ ቀደምም የአፍሪቃ አገራት በቻይና እና ህንድን ከመሰሉ አገራት ጋር ብቻ የተወሰነውን የግብይት ስርዓታቸውን እንዲፈትሹ ከነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ሐብት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ መሰረተ-ልማቶቻቸውን እንዲያስፋፉ እና አማራጮች እንዲያዘጋጁ ምክር ሲለግስ ቆይቷል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ