1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዕርቀ-ሠላም ለኢትዮጵያ

እሑድ፣ ሚያዝያ 16 2008

ከፖለቲካ አልፎ እስከ ሃይማኖቱ፤ ከጎሳ ዘልሎ እስከ እድር ያሉ ማሕበራዊ ግንኙነቶችን በጅጉ የተጫነዉ ልምድ፤ ፈሊጥ ወይም ይትበሐልን ለማረቅ ወይም እርቀ-ሠላም ለማስፈን ጥቂት ወገኖች በተለያየ ጊዜ መሞከራቸዉ አልቀረም። አሁንም የሚሞክሩ አሉ።ሙከራዉ ምክንያት ሆኖን እኛም የዛሬ ርእሳችን አደረግነዉ።

https://p.dw.com/p/1Ib3I
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ዕቅርቀ-ሠላም ለኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከተቃዋሚዎቹ፤ ተቃዋሚዎች እርስ በርስ፤ ምሑራን አንዳቸዉ ከሌላቸዉ፤ ሌላዉ ቀርቶ የአንድ ሃይማኖት አባቶች፤ ጋዜጠኞችም እንኳን ባንድ ጉዳይ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ተቃራኒ አቋም መያዙን እንደ ጥሩ ፈለጥ ወይም ፋሽን እየተከተሉት ነዉ።

የደርግ ዉድቀት «አንድነትዋን ጠብቃ የኖረች» እየተባለ የሚነገርላት ሐገር ዜጎች ከአንድነት ይልቅ አንድ ርዕዮተ-ዓለም እናቀነቅናለን እያሉ በመደብ፤ በትዉልድ ቀየ፤ በሥልጣን፤ ተለያይተዉ የሚገዳደሉበት ዘመን የመሰናበቱ ምልክት መስሎ ነበር።ኢትዮጵያዉያን ግን ዛሬም በሐያ-አምስተኛ ዓመቱ፤ ዛሬም በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን፤ ከድሮዉ በባሰ መልኩ ዘር፤ የትዉልድ ቀየ፤ እድሜ ሳይቀር እየቆጠሩ እርስ በርስ እንደተወዛገቡ፤ እንደተጠላለፉ፤ እንደተደባደቡ፤ ሲችሉም እንደገዳደሉ፤ ይሕን ሁሉ ማድረግ ቢያቅታቸዉ እንደተኳረፉ ነዉ።

ኢትዮጵያዉን ሐገርም ዉስጥ ይሁኑ ዉጪ፤ ከመግባባት ይልቅ ለመጣላት፤ በጋራ ከመቆም ይልቅ ለመነጣጠል፤ ከሚያዉቁት ይብስ ከማያዉቁት ጋር ለመወዳጀት የመጣደፋቸዉ ሰበብ ምክንያት በርግጥ ብዙ አነጋጋሪ፤ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚጠይቅ ነዉ።

ከፖለቲካ አልፎ እድርና ሰንበቴን የመሳሰሉ ማሕበራዊ ግንኙነቶችን በጅጉ የተጫነዉ ልምድ፤ ፈሊጥ ወይም ይትበሐልን ለማረቅ ወይም እርቀ-ሠላም ለማስፈን ጥቂት ወገኖች በተለያየ ጊዜ መሞከራቸዉ አልቀረም። አሁንም የሚሞክሩ አሉ።ሙከራዉ ምክንያት ሆኖን እኛም የዛሬ ርእሳችን አደረግነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ