1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም ዓቀፉ የሴቶች የፀረ-ግርዛት ቀን

ማክሰኞ፣ ጥር 29 2010

ዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት «WHO» በዛሬዉ ዕለት ታስቦ የዋለዉን ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ፀረ-ግርዛት ቀን አስመልክቶ ባወጣዉ መረጃ መሰረት በዓለም ላይ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የግርዛት ሰለባ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/2sCsd
Äthiopien Kampagne gegen weibliche Genitalverstümmelung
ምስል DW/G. Tedla HG

Female Genital Mutulation in Ethiopia - MP3-Stereo

በኢትዮጵያም የሴት ልጅ ግርዛት ከ 14 ዓመት እድሜ በታች ባሉ ልጆች ላይ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም፤  ከ14 ዓመት ዕድሜ በላይ ባሉ ሴቶች ግን በሚፈለገዉ መጠን አለመቀነሱ ነዉ የተገለጸዉ። 
በጎርጎሮሳዉያኑ የካቲት 6 ቀን በየዓመቱ የሚካሄደዉን «የሴት ልጅ ግርዛት ይቁም» ቀንን አስመልክቶ ድርጅቱ ባወጣዉ ዘገባ የሴት ልጅ ግርዛት አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት የሚያደርስ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ቢሆንም አሁንም ድረስ በ 30 የአፍሪቃ፣ የመካከለኛዉ ምስራቅና የእስያ ሀገራት ይፈፀማል።
ይህን ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ለመቀነስ ከጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር ከ 1997 ጀምሮ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትኩረት አግኝቶ ጥናቶችን በማካሄድ በህዝብ ፖሊሲወች ላይ መሻሻሎችና ለዉጦች መታየታቸዉን ዘገባዉ ጠቁሟል። በተለያዩ ሀገራትም የፖሊሲ ድጋፍ አግኝቶ በ 26 የአፍሪቃና ይህንን ድርጊት የሚፈፅሙ የማህበረሰብ አባላት በስደት በሚኖሩባቸዉ ሌሎች 33 ሀገራት የሴት ልጅ ግርዛትን የሚከለክሉ ሕጎች ወጥተዋል። ያም ሆኖ ግን  ከማህበረሰቡ ልማድና አስተሳሰብ ጋር በእጅጉ የተቆራኜ በመሆኑ አሁንም ድረስ ድርጊቱን ማስቆም አልተቻለም። እናም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ200 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሴቶች ይህ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ተፈፅሟል።
በኢትዮጵያም የሴትን ልጅ ግርዛት የሚከለክል ሕግ ቢኖርም አሁንም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ድርጊቱ እየተፈፀመ መሆኑን በኢትዮጵያ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ታደሰ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ አማካኝነት በየአምስት ዓመቱ በተደረጉ የሥነ-ሕዝብ ጤና ጥናቶች መሰረትም የሴት ልጅ ግርዛት ከ14 ዓመት እድሜ በታች ባሉ ልጆች አበረታች ለዉጥ ቢታይም ከዚያ በላይ ባሉ የዕድሜ ክልሎች ግን ለዉጡ ያን ያህል እንዳልሆነ ነዉ የገለጹት።
«እና በዚህ ጥናት መሰርት እንግዲህ ከ15 እስከ 49 ባሉት እድሜ ላይ ያሉት ስንመለከት እንግዲህ 65 ፐርሰንት ነዉ የሚለዉ።ከ 15 እስከ 49 ።ይህ እንግዲህ በ 2005 ላይ 80 % ነበር።ከዚያ ወደ 74 % አሁን ወደ 65 %፤ይህ እንግዲህ ከ 2000፣2005፣2016 ማለት ነዉ።ይህ እንግዲህ እስከ 49 እድሜ ያሉትን ነዉ የሚያካትተዉ።ከዚሮ እስከ 14 የዕድሜ ክልል ባሉት ሴቶች መካከል ድርጊቱ እየቀነሰ መሄዱን ያሳያል።ከ15 እስከ 19 ባለዉ የእድሜ ክልል 47%፣ከ ዚሮ እስከ 14 ዕድሜ ደግሞ 16% መሆኑን ነዉ የ «DHS»የ 2010 ጥናት የሚያሳየዉ።»ብለዋል አቶ ስለሺ።
ለዉጡ በታችኛዉ የዕድሜ ክልል ላይ የተሻለ ስራ በመሰራቱ የተገኘ ነዉም ይላሉ።

Äthiopien Kampagne gegen weibliche Genitalverstümmelung
ምስል DW/G. Tedla HG
Äthiopien Fotos von Mädchen verschont von Genitalverstümmelung Female Genital Mutilation / Cutting (FGM / C)
ምስል picture-alliance/dpa/Unicef/Holt

«እንግዲህ እድሜአቸዉ  ከፍተኛ የነበሩት «ፕራክቲሱ »በፊትም ሲፈፀም ነበር ።ነገር ግን አሁን ያሉትን እንግዲህ ከማህበረሰብ ግንዛቤ ጋር ሊያያዝ ይችላል።የተሰሩ የተለያዩ «ኢንተር ቬንሽኖች» ዉጤት ሊሆን ይችላል።በተለይ «ሌትሊ»የተሰሩ ስራወች ዉጤት እያሳዩ ማምጣታቸዉን ጋር የሚያያዝ ነዉ።በተለይ በታችኛዉ የዕድሜ ክልል ላይ።» 

እንደ ኃላፊዉ የሀገሪቱን የፀረ-ግርዛት ሕግ ከማስከበር በተጨማሪ መስሪያ ቤታቸዉ በአንድ ሦስተኛ የቀነሱ አካባቢወችን የመሸለም ዕቅድ አለዉ። በ2025 ድርጊቱን ለማስቆም የተያዘዉን እቅድ ለማሳካትም ከሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራም ጨምረዉ ገልፀዋል። 


ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ