1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም አበይት ክስተቶች በ2016 አጋማሽ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 17 2009

ዓለም ታዋቂ ሰዎቿን ተነጥቃለች፤ ሽብር በርካቶችን ጭዳ አድርጓል፤ ኃያላን ተፋጠዋል፤ በእጅ አዙርም ተጠዛጥዘዋል፤ የሶሪያዋ አሌፖ ከ5 ዓመታት ውጊያ በኋላ በበሽር አል አሳድ እጅ ወድቃለች፤ በጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት 2ኛ አጋማሽ። የከሸፈው የቱርክ መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራን ሰበብ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሌላ ሰበብ በኢትዮጵያም ተደግሟል።

https://p.dw.com/p/2Up3u
Kuba Fidel Castro
ምስል picture-alliance/dpa/A. Ernesto

ዓለም በ2016 ከሐምሌ እስከ ታኅሣሥ

ዓለም ታዋቂ ሰዎቿን ተነጥቃለች፤ ሽብር በርካቶችን ጭዳ አድርጓል፤ ኃያላን ተፋጠዋል፤ በእጅ አዙርም ተጠዛጥዘዋል፤ዶናልድ ትራምፕ ባልተጠበቀ መልኩ ተመራጭ ፕሬዚዳንትነታቸውም ጸድቋል። ባቱን ሩጅ፤ ዩናይትድ ስቴትስ የጥቁሮች ሞት በቃን ባሉ ጥቁር ሰልፈኞች የአደባባይ ተቃውሞ ተንጣለች። የኢትዮጵያውያን ባለውለታ፥ የኩባው መሪ፥ አብዮታዊው መሪ፥ ፊደል ካስትሮን ዓለም ተሰናብታለች።

የጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት ሐምሌ ወር እዚህም እዚያም የሽብር ጥቃት ጎልቶ የወጣበት ነበር። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» በአጭሩ አይሲስ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥቃት የተጠናከረበት ወር።

ሐምሌ፦ በባንግላዴሿ ዳካር አምስት ወጣቶች አንድ ምግብ ቤትን ተቆጣጥረው ስለት እና የጦር መሣሪያ በመጠቀም  ባደረሱት ግድያ 20 ታጋቾች ተገድለዋል። በኢራቅ መዲና ባግዳድ የገበያ ማእከል ከባድ ተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ባደረሰው ጥፋት 137 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሳዑዲ አረቢያ መዲና ከተማም አንድ አጥፍቶ ጠፊ አራት ሰዎችን አጥፎቶ ሌሎችን ማቁሰሉ የተሰማው በዚሁ ወር ነበር። ከሦስቱም ጥቃቶች ጀርባ ታዲያ አይሲስ እጁ እንዳለበት አስታወቋል።

Irak Selbstmordanschlag Autobombe südlich von Bagdad
ምስል Getty Images/AFP/H. Hamdani

አይሲስ በወርሃ ሕዳር ደቡብ ኢራቅ ውስጥ የሺዓ እስልምና ተከታዮች ላይ ባደረሰው በከባድ ተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ጥቃት 80 ሰዎች ተገድለዋል። ሦስት ወር ቀደም ብሎ ነሐሴ ላይ ግን አይሲስ የቡድኑ አመራር ሁለተኛው ሰው ሞሐመድ አል አድናኒ  መገደልን በመግለጥ የበቀል ርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቀበት ወር ነበር።

ሐምሌ ወር ከበርካታ ጉልኅ የሽብር ጥቃቶች ባሻገር የዩናይትድ ስቴትስ እና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ የጦዘበት ወር ነበር።  የዚያ ምክንያቱ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያን በሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ጭቆና በመክሰስ ማዕቀብ መጣልዋ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ዮንግ ኡን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ስትጥል፤ ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የነበራትን ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ መበጠሷን አሳውቃለች። ሁለቱ ሃገራት ቀደም ሲል ግንኙነታቸው ኒውዮርክ በሚገኙ በተባበሩት መንግሥታት ልዑካን በኩል ነበር።

ሐምሌ አጋማሽ የፈረንሳዩ ቱርክ ባልተሳካ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ስትታመስ ያደረችበት ምሽት ለብዙዎች አይረሳም። ሙከራውን ያደረጉት ባብዛኛው የቱርክ ወታደሮች ነበሩ። በቱርክ ሁለት ትልልቅ ከተሞች፦ በመዲናዋ አንካራ እና ኢስታንቡል የተኩስ ልውውጦች እና ፍንዳታዎች ተከስተው በዕለቱ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ተገደሉ።

የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራውን ዓለም በቀጥታ በቴሌቪዥን ሲከታተል የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኃን ካልታወቀ ስፍራ ሆነው ቱርካውያን  አደባባይ ወጥተው መፈንቅለ-መንግሥቱን እንዲታገሉ በእጅ ስልካቸው ጥሪ አስተላለፉ። ሕዝቡ ወደ ከተሞቹ ተመመ። ከወታደሮች ጋር ተጋጨ። ወታደሮች እጅ ሰጡ። ኤርዶኃን አንሰራሩ። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልድሪም የከሸፈውን መፈንቅለ-መንግሥት ጥቁር ዕድፍ አሉት።

«የተከበራችሁ ዜጎች እና የተወደድሽ አገሬ ሆይ የትናንት ምሽት ሐምሌ 15 ቀን ለቱርክ ዴሞክራሲ ጥቁር ዕድፍ ነው።»

Türkei Demonstranten verschiedener Parteien treffen in Istanbul auf dem Taksim Platz aufeinander
ምስል picture-alliance/AA/I. Yakut

«በጥቁር ዕድፍ» ሰበብ ወደ 6000 የሚጠጉ ሰዎች ወደ እስር ቤት ተጋዙ። ፕሬዚዳንቱ በመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው የተሳተፉ በሙሉ በሀገር ክህደት እንደሚወነጀሉ አስታወቁ። 250 ዳኞች እና 2,745 አቃብያነ ሕግ የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸው 1,684ቱ እስር ቤት ተወርውረዋል። 81 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል በቱርክ። ቻይና፣ ግብጽ፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያን አስከትላም ቱርክ በጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ የዓለማችን ቁጥር አንድ አሳሪ ተሰኝታለች። 8,000 የፖሊስ መኮንኖች በጥርጣሬ ከሥራቸው ታግደዋል። ቱርክ ጋዜጠኞችን በማሰር ስሟ እንደተነሳው ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ትገኛለች። የቱርክ መንግሥት የመፈንቅለ-መንግሥቱ ሙከራ አቀናባሪ ያላቸው በስደት ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ፌቱላህ ጉሌን  ተዛውረው እንዲሰጡት ጥያቄ ቢያቀርብም ውድቅ ሆኖበታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ጥቁሮች በነጭ ፖሊሶች በተደጋጋሚ መገደላቸው ያበሳጨው የቀድሞ ባሕር ኃይል ባልደረባ ሚካህ ዣቪየር ጆንሰን አምስት የአሜሪካ ፖሊሶችን ገደለ። ሰባት አቆሰለ። ከሮቦት በተወነጨፈ ፈንጂም መገደሉን ፖሊስ አስታወቀ። ከሚካህ ጥቃት በፊትም በኋላም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ጥቁሮች በተደጋጋሚ ተገድለዋል። ሐምሌ መንደርደሪያ ላይ ነው። ከሉዚያና ባቶን ሩዥ እስከ ሎስአንጀለስ፤ ከኒውዮርክ እስከ ቴክሳስ ጥቁሮች ለተቃውሞ አደባባዮችን አጨናንቀዋል። የተቀየረ ነገር ግን የለም።

USA Ermordung von Polizisten in Dallas Täter Micah Xavier Johnson
ምስል Reuters/Facebook

ታይላንድ ባኪያሄደችው ሕዝበ-ውሳኔ ወታደራዊ መሠረት ያለው ሕገ-መንግሥቷን በነሐሴ ወር ላይ ማጽደቋ ተሰምቷል።  በፓኪስታን ደቡብ ምዕራብ  የቄታ ከተማ  በአጥፍቶ ጠፊ የቦንብ ጥቃት 74 ሰዎች ተገድለዋል። በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር ሰሜን ምዕራብ የመን ውስጥ ሐኪም ቤት ላይ ባደረሰው የአየር ጥቃት 11 ሰዎች ሲገደሉ፤ 19 ቆስለዋል።

ሩስያ ከኢራን ዓየር ኃይል ማረፊያ በመንደርደር ሶሪያ ውስጥ በጦር ጄቶች ድብደባ ዘመቻ የከፈተችው በነሐሴ አጋማሽ ላይ ነው። በሶሪያው ግጭት፦ ከሶሪያ እና ኢራን ባሻገር ቱርክ እና ዩናይትድ ስቴትስም ተሳትፈዋል። ቱርክ ታንኮች፣ የጦር ጄቶች እና እግረኛ ወታደሮችን በሶሪያው ጦርነት አሳትፋለች። ሩስያ እና ቱርክ ለተለያየ ግብ ሶሪያ ውስጥ ሲዘምቱ፤ በታኅሳስ አጋማሽ የሩስያ አምባሳደር አንድሬ ካርሎቭ አንካራ በሚገኝ የስዕል አውደ-ርእይ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ከስራ ውጪ በሆነ ቱርካዊ ፖሊስ ከጀርባቸው ተተኩሶባቸው ተገድለዋል፤ ሦስት ሰዎች ቆስለዋል። ገዳዩ « አሌፖን አትርሱ» እያለ ሲጮህ በቴሌቪዥን ምስሉ ታይቷል። ቱርክ ግድያውን ከሩስያ ጋር ያላትን ግንኙነትን ለማጠልሸት የተደረገ ሴራ ነው ብላለች።

በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትረም አሸነፉ። «አመሠግናለሁ። በጣም አመሠግናለሁ። ሂላሪ በጣም ለረዥም ጊዜ  በአስቸጋሪ ኹኔታ ሠርተዋል። ለሀገራችን ለሰጡት አገልግሎት  ባለዕዳዎች ነን። ምሥጋና ይገባቸዋል።  ይህን የምለው  በትህትና ነው። አሁን በአሜሪካ ጊዜው በመከፋፈል ምክንያት የተፈጠረውን  ቁስልየምንጠግንበት ነው። በአንድ የምንቆምበት ነው። በመላው ሀገሪቱ ላሉ ሁሉም ዲሞክራቶች እና ሪፐብሊካን እንዲሁም ሌሎችም  የምለው አሁን ጊዜው እንደተባበረ ሕዝብ  በአንድ ላይ  የምንቆይበት ነው ጊዜው አሁን ነው።»

USA | 3. Präsidentschaftsdebatte 2016 in Las Vegas
ምስል Getty Images/W. McNamee

ዶናልድ ትረምፕ ሒላሪ ክሊንተንን ማሸነፋቸው ከተሰማ ብዙም ሳይቆይ በሩስያ የሚደገፈው የሶሪያ ጦር ከአምስት ዓመታት ውጊያ በኋላ አሌፖን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን አስታውቋል። ዶናልድ ትራምፕ ከሩስያ ጋር ወዳጅ የመሆናቸው ነገር እና ሩስያ በጦር ጄት ድብደባ ድጋፍ የምትሰጠው የበሽር አል አሳድ መንግሥት አሌፖን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩ መገጣጠም ብዙዎችን አስደምሟል። በጦርነቱ ግን ህጻናት በሕንጻ ፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው አልፈዋል።  አዋቂዎች በደም  አበላ እና በአዋራ የተዋጠ የሰቆቃ ገጻቸውን እያሳዩ ጣር አሰምተዋል። የሶሪያዋ አሌፖ በጦርነት እንዳልነበረች ኾናለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ ስቴፋን ኦብራይን።

«ለሰብአዊነት ስንል የጦርነቱ ተሳታፊዎች ሰላማዊ ሰዎችን እንዲጠብቁ ልመናችንን እና ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።  ምሥራቅ አሌፖ  ግዙፍ መካነ-መቃብር ከመኾኗ በፊት ተከበው የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች  መውጫ ቀዳዳ እንዲያገኙ እንማጸናለን።»

በ2016 መስከረም ወር የኡስቤኪስታኑ የ25 ዓመት ብቸኛ መሪ ኢስላም ካሪሞቭ መሞታቸው ተሰምቷል። የካቶሊክ ቤተክስርስቲያን ማዘር ቴሬዛን ቅድስት ሲል ሰይሟል። የሶሪያ መንግሥት በአሌፖ ነዋሪዎች ላይ መርዘኛውን ክሎሪን ቦንብ መወርወሩ ተጠርጥሯል። ሰሜን ኮሪያ ከባድ እና ቀላል ኒውክሌር ቦንቦችን ሙከራ ማድረጓን አስታውቃለች። ሩስያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ሶሪያ ውስጥ የገቡት የተኩስ አቁም ስምምነት አክትሞ 20 ሰዎች መገደላቸው እና ምግብ የጻኑ 31 ተሽከርካሪዎች መውደማቸው ተሰምቷል በዚሁ በመስከረም ወር።

Aleppo Syrien Rauchwolke
ምስል Reuters/O. Sanadiki

ጥቅምት ወር ላይ ቱርክ ከፖሊስ ሠራዊቷ 5 በመቶውን ማለትም 13,000  ፖሊሶችን ከመፈንቅለ-መንግሥት ጋር በተያያዘ አሰናብታለች። የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች በኖርዌይ ኦስሎ እና በስዊድን ስቶክሆልም ይፋ ተደርጓል።

የቬኔዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በመቃወም ሺህዎች አደባባይ ወጥተዋል። የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት ፓርክ ጊዩን ሂ ሥልጣን እንዲለቁ ለመጠየቅ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባዮችን አጥለቅልቀዋል። ፕሬዚዳንቷ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም ክስ ቀርቦባቸዋል።

ኅዳር ወር ላይ የኢራቅ መንግሥት ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ሞሱል ከተማን ከአይሲስ እጅ አስለቅቋል።  የኩባው የቀድሞ አብዮታዊ መሪ ፊደል ካስትሮ ኅልፈት የተነገረውም ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ነው። የፊደል ካስትሮ ወንድም የኩባው ፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ።

Letzte Ehrung zu Ehren des ehemaligen kubanischen Führers Castro in Santiago de Cuba
ምስል Reuters/C. Barria

«ውድ ኩባውያን፤ ጥልቅ በሆነ ሐዘን ተውጪ ለሕዝባችን፣ አሜሪካ ውስጥ ለሚገኙ ወዳጆቻችን እና ለመላው ዓለም የኩባ አብዮት መሪ በዛሬው እለት ምሽት 4 ሰአት ተኩል ላይ ማለፉን እገልጣለሁ። ፊደል ካስትሮ አርፏል።»

ከፊደል ካስትሮ በተጨማሪ በጎርጎሪዮሱ 2016 አጋማሽ  መስከረም መገባደጃ ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር እና ፕሬዚዳንት የበሩት ሺሞን ፔሬዝ ቴል አቪቭ ውስጥ ረቡዕ ቀን በ93 ዓመታቸው ማረፋቸው ተነግሯል።  ሺሞን ፔሬስ የኖቤል ተሸላሚ ነበሩ። ሺሞን ፔሬዝ ባረፉ ከ15 ቀናት በኋላ የታይላንዱ ንጉሥ ቡሚቦል አዱልያዴ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም መለየታቸው ተገልጧል። የዓለማችን የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ባለታሪክ መሐመድ ዓሊም ሰኔ መንደርደሪያ ላይ ይህችን ዓለም ተሰናብቶ ሄዷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ